Get Mystery Box with random crypto!

አትዩኝ አለቅም! በአሁኑ ወቀት ካለው የኑሮ ደረጃ በመካከለኛ የኑሮ ዘዬ ውስጥ እንደ ሚኖር አለ | ወግ ብቻ

አትዩኝ አለቅም!


በአሁኑ ወቀት ካለው የኑሮ ደረጃ በመካከለኛ የኑሮ ዘዬ ውስጥ እንደ ሚኖር አለባበሱ ያመለክታል። በግምት 24 ዓመት ይሆነዋል። ጠይምነቱ ኢትዮጵያዊነቱን ያበራል፤ እንደከሰል የጠቆረ ጂንስ ሱሪ ሃጫ በረዶ በመሰለ ነጭ ሸሚዝ ለብሷል፤ ቡኒ ጫማ እንደ ተጫማ አይኔ አይክድም፤ ለዝነጣ ልበለው ለፀሀይ ጠቆር ያለ መነፅር አጥልቋል፤ በክንዱ ላይ ያንጠለጠለውን ሰማያዊ ሹራብ ሲለብስ ከቅጥነቱ ደርባባነቱ ጎላ። የስራ መውጫ ሰዓት ስለሆነ ሰዉ ወደ ጎጆው ለመገስገስ ወደ ትራንስፖርት ሰልፍ እንጂ ማን ምን ይሁን እያየ አይደለም፤ ይህን ወጣትም ያየሁት የባስ ሰልፍ ላይ ነው። አንድ ወዳጁ"ይስሀቅ እንዴት ነህ" ብሎ ሰላምታውን ከፊቱ ፈገግታ ጋር ለገሰው፤ ከተሰለፈ እንኳንስ ለመሳቅ ፈገግም ያላለው ሰልፈኛ ከወዳጁ ሲገናኝ ከንፈሩ ተላቆ ጥርሶቹን ማስቆጠር ጀመረ። ሲመስለኝ ከተገናኙ ሰነባብተዋል የባጡንም የቆጡንም እያወጉ ሰዓታቸውን ገፉ፤ ባሲቷ ሰዓቷ ሲደርስ እያጋፈረች መጣች። ይስሀቅ በሰልፉ 3ኛ ላይ ስለሆነ ሲያወጋው የነበረውን ወዳጁን ተሰናበተው። አዛውንቶች በቦታው ነበሩ አብዛኛዎቹ ለማምነው ለመግባት ቢሞክሩም ሰዉ ፍቃደኛ ስላልሆነ መግባት አልቻሉም። ታዲያ የሁሉም አይን ግን እንደተማክሮ እሱ ላይ አርፏል፤ እሱም ፊቱን ሲጨፈግገው "ይቺ ጠጋ ጠጋ....." ሳይል አልቀረም። ትኬተሯ መጥታ እንደየአመጣጣችን ትቆርጥልን ጀመር ባሱ ሞልቶ በሞተሩ እያጓራ ጭሱን እንደ እጣን ወደ ሌላ መስመር የተሰለፉትን ተሰላፊዎች እያጠነ ጉዞአችንን ጀመርን። እኔ ለትዝብት ይመቸኝ ዘንድ ከመጨረሻው ወንበር ተስፈንጥሬ ሁኔታውን እየተከታተልኩ ነው። አዛውንቶቹም ገብተው ከልጁ አካባቢ ያንዣብቡ ጀመር፤ አይናቸውን ከሱ መንቀል ተሳናቸው። እኔም በተመስጦ መከታተልን በጀ ብዬ ዘልቄበታለ። ለካስ ይስሀቅ በጥቁሩ መነፅር ውስጥ ሁኔታውን እየቃኘ ነበር፤ ለእነዚህ እይታዎች መልስ መስጠት አለብኝ ብሎ አስቀድሞ ፈገግ አለና በጎርናና ድምፁ "እባካችሁ አትዩኝ! የእናንተ እይታ አያስለቅቀኝም፤
ይችን ወንበር ለማግኘት ብዙ ለፍቻለሁ፣
ደም ባላፈስም ፀሀይ ተግቻለሁ፣
እጄን ጨብጬ ሌላውን ባልጨብጥም ተራዬን ጠብቂያለሁ። አሁን እኔን ከምታዩኝ በጊዜ አትሮጡም፤ ከማጭበርበር ይልቅ ህግን አትጠብቁም፤ እንደ አብርሃም ብላቴና ይስሀቅ በጊዜዬ በመታዘዜ ይኸው ለዚህ ዙፋን ታጭቻለሁ። ብታዩኝ ባታዩኝ እኔን አያገባኝ። ያገኘሁት በሀቄ፤ የተቀመጥኩት በልፋቴ ነው። እናም "አትዩኝ አለቅም!" በድጋሚ አትዩኝ ወንበሬን አለቅም! " በማለት እሱ ፈገግ እያለ የሰውን ሁሉ አይን ወደ ፊት ከማንጋጠጥ ወደ ቁልቁል ሰበረው። እኔም በንግግሩ ቅኔውን ለፈቺ ብዬ እንደተረዳሁት ተረድቼ በንግግሩ ተደምሜ ጉዞዬን ቋጨሁ።


ተፃፈ በኢማን አብዲ(ረዱ)


ታኅሳስ 7,2015ዓ.ም
@redu_30

@wegoch
@wegoch
@paappii