Get Mystery Box with random crypto!

#የመኖር አካፋይ ፣ የመ ፤ ሞ ፣ ት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ አምስት) (ሜሪ | ወግ ብቻ

#የመኖር አካፋይ ፣ የመ ፤ ሞ ፣ ት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ አምስት)
(ሜሪ ፈለቀ)

በአትኩሮት ቢያየኝ እኮ በአፌ ልትወጣ የደረሰች ልቤ ስትደልቅ የለበስኩትን ሸሚዝ እያርገበገበችው ነው። በጀርባዬ የሚንቆረቆር ላቤ ለአፍታ ሌሎች ድምፆች ረጭ ቢሉ፤ ከማጅራቴ ወደ መቀመጫዬ ሲወርድ እንደ ዝናብ <ጠብ> ሲል ይሰማ ነበር። ስክሪኑ ላይ ያለውን የራሴን ምስል ሳየው ለመኮሳተር (የማላስታውሳትን የድሮዋን ሜላት ለመምሰል) በታገልኩ ቁጥር የዞረበት ፊት እያሳየሁ እንደሆነ ገባኝ። እጄን የያዘው የጎንጥ እጅ (ገባቶት ነው መሰለኝ) እንደመጭመቅ ሲያደርገኝ ትኩረቴን ከራሴ ፊት ላይ ወደ ኪዳን መለስኩ። መስሎኝ የነበረው ከወንበር ጋር ታስሮ እየተሰቃየ የማየው ወይም ያ ድምፁን የሰማሁት ሰውዬ ግንባሩ ላይ ሽጉጥ ደግኖበት አልያም ፊቱ በድብደባ ብዛት አባብጦ እና በደም ተለውሶ ነገር የማየው ነበር የመሰለኝ። የሆነው ግን ሌላ ነው። ኪዳንና ሰውየው እየተዝናኑ እንጂ አጋች እና ታጋች በማይመስል ሁኔታ አጠገብ ላጠገብ ተቀምጠዋል። ኪዳንን ለመለየት አልተቸገርኩም። የስልኬ ስክሪን ላይ ካለው መልኩ ምንም ለውጥ የለውም። አስቀድሞም በግራ መጋባት የጦዘውን ጭንቅላቴን ልክነት ያጠራጠረኝ የኪዳን መረጋጋት ነው። የሆነ ልክ ሰላም ልንባባል የተደዋወልን አስመስሎ

«ሜልዬ! ደህና ነሽልኝኣ?» አለ። ምንድነው እየሆነ ያለው? ኪዳን አይደለም ይሆን? ሰውየው ቅድም 12 ቦታ ቀነጣጥሼ እልክልሻለሁ ሲለኝ አልሰማም ማለት ነው? አሁንም የጎንጥ እጅ አነቃኝ።

«እኔ ደህና ነኝ! አንተስ?» ይባላል ቆይ? ከአጋቹ ጋር የተቀመጠ ሰው ደህና እንደማይሆን ግልፅ አይደል? እሱ ዝንቡ እንኳን እሽ እንዳልተባለ ሰው ዘና እያለ ታዲያ ምን ልበል? ምናልባት ለእኔ ብሎ ይሆን? እኔን ለማረጋጋት?

«አታስቢ ደህና ነኝ! ከልቤ ደህና ነኝ።» እያለ ምንም ያለመጎዳቱን ሊያሳየኝ ስልኩን እያራቀ ከተቀመጠበት ተነስቶ መላ አካላቱን አሳየኝ። እያባበለኝ ነገር መሰለኝ።

«እንዴት ነው የማላስበው? መዝናኛ ቦታ …… » እኔ ባልገባኝ  ምክንያት  ለእርሱ ግን ልክ በመሰለ እንድናገር አልፈለገም። ወዲያው አቋርጦኝ

«ሜል እንዲሁ ተጨነቂ ስልሽ ነው። እኔኮ ደህና ነኝ አልኩሽ። » ሲለኝ ጎንጥ ምን እንዳናደደው ሳይገባኝ ተበሳጭቶ ጥርሱን ነክሶ እኔን ባልያዘው እጁ አየሩን በቦክስ ጠለዘው። እየሆነ ያለው ነገር አፍና ጭራው የጠፋኝ እኔን ብቻ ነው? እኔ ሳይገባኝ እሱ የገባው አብረን ከሰማነው የደህና ነኝ መልእክት ውጪ ውስጠ ወይራ አለው? « በኋላ እንገናኝ የለ? እስከዛ ደህና ሁኚልኝ! ደግሞ አምላክን በልመና አታድክሚ!!! የምትችውዪውን አድርጊና በተረፈው አመስግኚው። ያመሰገንሽው አምላክ የጎደለውን ይሞላልሻል።» አለኝ ጭራሽ። የድሮዋ ሜላት ፀሎተኛ እንዳልነበረች ጠፍቶት ነው? ይሄንኑ ዓረፍተ ነገር ግን ከዚህ በፊት የሆነ ሰው ብሎት ሰምቻለሁ!! የት ነው የሰማሁት?

እስካሁን ድምፁ ያልተሰማው ሰውዬ ስልኩን ተቀበለውና በአይኑ እንደመጥቀስ አድርጎኝ ዘጋው!!  አፌን እንደከፈትኩ ስልኩ ላይ አፍጥጬ ቀረሁ።

«ይሄ የውሻ ልጅ አውቆታል!» አለ ጎንጥ። መኪና ውስጥ ሆነ እንጂ ሜዳ ላይ ቢሆን <ዘራፍ> የሚል ነው የሚመስለው።
«ምኑን?» አልኩኝ ከድንዛዜዬ ሳልወጣ

«እየቀረፅሽው እንደሆን !» ብሎ ስልኩን እንድሰጠው እጁን ዘረጋልኝ። ስሰጠው ስልኩ ስክሪኑ ቆልፎ ስለነበር እንድከፍትለት መልሶ ሰጠኝ። ያለኝን የምከውነው ምኑም ገብቶኝ አይደለም። ያለውም የገባኝ ነገር የለውም።

«ማን ነበርኩ? ከምን ጋር የተቆላለፈ ህይወት ነው የነበረኝ? የምን ቪዲዮ ነው የምወስድለት? ስልኬ ውስጥ ያለ ነገር ይሆን?»

«ህም! ስልክሽ ውስጥ ልታኖሪው አትችዪም!» ሲለኝ አፌን ከፍቼ ቀረሁ። ስለቪዲዮው ያውቃል!!

«ምን ይመስልሃል ቪዲዮው?»

«እሱን በምን አውቄው! ብቻ ቅሌቱን የተሸከመ ነገር ነው የሚሆን»

ድንዝዝ እንዳልኩ አይኔ ብቻ ሲንቀዋለል ስልኩ ላይ ቅድም የተጫናት ምልክት ስክሪኑን መቅጃ መሆኗን እና ሰውየው እንደመረጃ እንዳንይዝበት ኪዳንን ምንም የተለየ ምልክት እንዳይሰጥ አስጠንቅቆት እንደሆነ እርግጠኛ ሆኖ ከነገረኝ በኋላ እኔን ረስቶ የተቀዳውን ቪዲዮ እየደጋገመ ወደፊት ወደኋላ ቅርብ …. ራቅ እያደረገ ያያል። እኔ ደግሞ ዝም ብዬ እሱን አየዋለሁ።

«በስተመጨረሻ ልመና አታብዥ ያለው ነገር ያላስፈላጊ ቦታ የተዶለ አይመስልሽም? ላንቺ የሚያስታውስሽ ነገር አለ?» አለኝ አሁንም ከስክሪኑ አይኑን ሳይነቅል።

«የሆነ ሰው ሲለው የሰማው ይመስለኛል። አላውቅም!! ራሴም እለው የነበረ ነገር ይመስለኛል። ምንም መጨበጥ አልቻልኩም።» ስለው እንባዬ ዓይኔን ሞልቶታልኮ እሱ ግን አላየኝም። ቪዲዮውን ኪዳን ስለምስጋና ያነሳበት ጋር አቁሞ

«ተመልከች እዚህ!!» ብሎ ሰውየውን ጠቆመኝ « ልክ ኪዳን ሲናገር ፊቱ አንድ አፍታ ይቀየራል። ተመልከች! ያ ማለት ይህ መስመር እንዲናገር ከተፈቀደለት ውጪ ነው ማለት ነው! ሊገልጥልሽ የፈለገው አንድ መልእክት ቢኖረው ነው።»


«ጎንጥ?» አልኩት ፍስስ ባለ ድምፅ

«ወይ!» አለ አይኑን እዛው እንደሰነቀረ

«ማ ነ ህ? » አልኩት እንባዬ አብሮ ከቃላቱ ጋር ዱብ ዱብ እያለ። እዛ ነጥብ ላይ ጎንጥ ዘበኛዬ ብቻ እንዳልሆነ ገብቶኛል። የሚያስለቅሰኝ በትክክል ምን እንደሆነ እንጃ።

«ኸረ በመድሀንያለም?! » አለ ደንግጦ የሚያደርገው ጠፍቶት ። እጄን ሊይዘኝ እጁን ሲሰድ መንጭቄ ቀማሁት

«እንዳትነካኝ! ሁሉንም ነገር ታውቃለህ! ይሄን ሁሉ ጊዜ ስሰቃይ እያወቅክ ምንም እንደማያውቅ አብረህ ስታፋልገኝ ነበር። ሰውየው ያወራው ሁሉ ነገር ገብቶሃል። ንገረኝ አንተም የእነሱ ወገን ነህ? ምን ፈልገህ ነው?» እንባዬ ባይቆምልኝም ሰውነቴ ሲቆጣ ፣ ደሜ ሲሞቅ ይታወቀኛል።

«መድሀንያለም በሚያውቀው እንደሱ አይደለም!! አንች ያሰብሽውና የእኔ ድርጊት ለየቅል ነው!! ሀሳቤ ጠላትነት ከነበር ምን እጠብቅ ነበር? ከጠዋት እስከማታ እጀ ላይ አልነበርሽ?»

«አላውቅም! የሆነ የምትፈልገው ነገር ይኖራላ!!» ተነስቼ ከመኪናው ወረድኩ። ትንፋሽ እስኪያጥረኝ ድረስ ንዴቴ ያጨሰኝ ጀመር። የመኪናውን ጎማ በሃይል መጠለዜን ያወቅኩት የእግሬን አውራ ጣት ሲያመኝ ነው። የሆነ ውስጤ ተኝቶ የነበረ አውሬ የነቃ ይመስል የምቦጫጭቀው ነገር ፣ ቁጣዬን የምወጣበት ነገር ፈለግኩ። እሪሪሪ ብዬ መጮህም ፈለግኩ። የመኪናውን ኮፈን በቡጢ እየነረትኩ ማቆም እፈልጋለሁ ግን እጄን የምሰነዝርበት ቁጥር በጨመረ ልክ ሰውነቴ እየረገበ ፣ ቁጣዬ እየበረደ ስለተሰማኝ አላቆምኩም። ከመኪናው ወርዶ መምጣቱን ያወቅኩት አጠገቤ መጥቶ ሁለቱን እጄን ለቀም አድርጎ ሲያስቆመኝ ነው።

«አትንካኝ አልኩኮ!! » ብዬ ከመጮሄ እኩል በምን ቅፅበት እንደሰነዘርኩት ያልተቆጣጠርኩት ለቡጢ የተጨበጠ እጄ ጉንጩ ላይ አርፏል። ያደረግኩትን ሳውቅ ደንግጬ የመታሁበትን እጄን እንደበዓድ እጅ አየሁት። ከመኪናው ኮፈን ድብደባ ይሆን ከእርሱ ጉንጭ እጄ በልዟል። ወደኋላ ዞሮ አፉ ውስጥ የሞላውን ደም ከተፋ በኋላ ወደ እኔ እየዞረ በሱ ብሶ ይጮህ ጀመር