Get Mystery Box with random crypto!

« ለቅሶ አለብኝ... ልብስ ምረጥልኝ» ብላ የተከፈተ ቁምሳጥኗ ፊት ለፊት አቆመችኝ። የተጠቀጠቀ | ወግ ብቻ

« ለቅሶ አለብኝ... ልብስ ምረጥልኝ» ብላ የተከፈተ ቁምሳጥኗ ፊት ለፊት አቆመችኝ። የተጠቀጠቀ የጥቁር ልብስ መአአአአአት።

'ይጥቆር እንጂ ደግሞ ለለቅሶ ልብስ መረጣ የምን ቅብጠት ነው። ' አልኩ በሆዴ ... ታዝቤያት። እጄን በግዴለሽነት ሰድጄ አንዱን ጥቁር ጎተትኩትና ፊቷ ዘረጋሁት። ቀሚስ ነበር።

“ ውይ ... ይሄንን ቀሚስማ ሰዓሊው ወዳጄ ሲሞት ለቅሶ ደርሼበታለሁ ፤ አልለብስም።»

«ለለቅሶ የለበስሽውን ቀሚስ አትደግሚም? »

«ሀዘን ይደገማል? » ጥያቄዬን በጥያቄ። «በል ሌላ ምረጥ!»

ምን አከራከረኝ፤ ያነሳሁትን ወለል ላይ ጥዬ ሌላ ጥቁር መዘዝኩ። ባለአንገት ሹራብ።

«ዘፋኙ ጓደኛዬን ቀብሬበታለሁ እሱን። ቀይር»

ሆሆ... ጥዬ ሌላ መዘዝኩ። ሸሚዝ

« የጋዜጠኛ እህቴን አስከሬን በሱ ነበር የሸኘሁት። »

ጣልኩ። አነሳሁ። አንዱን ቀብራበታለች።
ጣልኩ.. አነሳሁ። ለአንዷ አንብታበታለች።
ወለሉ በጥቁር ልብስ፣ ጆሮዬ በሙታን ፕሮፋይል ተሞላ።

እንደ ድንገት አንዷን ሳብኳት። የምታምር ጥቁር ሱሪ። አማረችኝ።

«አታምርም? »

«በጣም ታምራለች። ለምን ይህቺን አትለብሻትም? »

«ቆጥቤያት ነውኮ። በጣም የምወደው ሰው ሲሞት ነው የምለብሳት። »

«ማን ሲሞት?»

«አንተ ነሃ የኔ ፍቅር!»

« ያድኅነነ ከመዓቱ ይሰውረነ ! ምነው በናትሽ»

«ከልቤ ነውኮ። የዛሬ ወር ሾፒንግ ወጥቼ ተሰቅላ ሳያት ትዝ ያልከኝ አንተ ነህ። እንዴት እንደምወድህም ያወቅኩት ያኔ ነው። »

« እርፍ!»

« እርፍ ስትል ነውኮ እለብሳታለሁ ያልኩህ! በዛ ላይ ሰሞኑን እያሳለህ ነው... »

«ምን በወጣኝ ነው የምትወጂኝ በማርያም? ካልጠፋ ሰው እኔን ለምን ወደድሽኝ በሩፋኤል?! »

« ኧረ አንተ ብቻ አይደለህም ውዴ። ያንተን እንደውም ከገዛሁት ቆየሁ። ቁም ሳጥን ውስጥ አልከተትኳቸውም እንጂ... አባቴ... መምህሬ... ክርስትና እናቴ ፣ የእህቴ ባል ፣ ያ ደሞ አቀናባሪው... በየተራቸው ሲታመሙ ጊዜ... “ድንገት ከሞቱ ብዬ” የምለብሰው ገዝቼ አስቀምጫለሁ። እኛ የኪዳነምሕረቱ ቄስ... እኚያ ሰባኪው አወቅካቸው? የምወዳቸው ? ቄሱ... ? ከሰሞኑ ታመዋል ሲሉ ሰምቻለሁ። ከዛሬው ቀብር መልስ... ለሳቸው ለቅሶ የሚሆን ነገር ታጋዛኛለህ »

አሃ... !
ለካ አልቃሾች አዲስ ጥቁር ሲሸምቱ..፣ አዲስ ድንኳን ሲጎትቱ፣ አዲስ ሙሾ ሲሸመድዱ፣ አዲስ አለቃቀስ ሲለማመዱ... መደንገጥ ነበረብን?

ለካ የሞት መላዕኮቻችንን ከምንጠብቅ ፣ አልቃሾቻችን አዲስ ጥቁር ልብስ እስኪገዙ ብንጠብቅ፣ መች እንደምንሞት ይገለጥልን ኖሯል !?

አሳዘነችኝ።
ቁም ሳጥን ሙሉ ልብስ አገላብጣም፣ ለዛሬው ለቅሶ የምትለብሰው ጥቁር አላገኘችም። በርግጥ... እኔ ጋር ገና ያልለበስኩት ጥቁር ካፖርት አለ። «ልስጥሽ?» አልላት ነገር ፈራኋት።

«ሲያምር! እኔ ስሞት ለብሰኸው ትቀብረኛለህ!»
ብትለኝስ?

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Rediet aseffa