Get Mystery Box with random crypto!

መቼም ጊዜ የማያሳየን ጉድ የለም። ዛሬ የ you tube ከርስ ውስጥ ገብቼ አንጀቱን ሳማስል ቆየሁ | ወግ ብቻ

መቼም ጊዜ የማያሳየን ጉድ የለም።
ዛሬ የ you tube ከርስ ውስጥ ገብቼ አንጀቱን ሳማስል ቆየሁ። ከሁሉም ከሁሉም ግርምቴን የወሰደው የ 90 ዎቹ ሙዚቃ ነበር ። ሙዚቀኛ አቤል ነይ ማታ ማታ የሚለውን ሙዚቃ መለስ ብላችሁ እዩት እስቲ?
አቤሎ ያደረገው ከርፋፋ ሱፍ አነስ ያለ ዩንቨርስቲ ተምረው ለመመረቅ የተዘጋጁ 5 ተማሪዎችን ጥንቅቅ አድርጎ ያስመርቅ ነበር ... አቤት የሱፍ ግፍ! ጓዶች በ 90 ዎቹ ጊዜማ የሱፍ ጨርቅ ላይ ግፍ አቆይተናል። እዛ የሰራነው ግፍ ነው ዛሬ ሱፍ ልብስንም የሱፍ ቆሎንም ያስወደደብን
ወደ አቤሎ ሱሪ አዘቅዝቄ ተመለከትኩ።
ሱፍ ዑመር ዋሻማ ምን ይሰፋል? እንዝርት ለምታክል ቅልጥም የደብረ ብርሀን ብርድ ልብስ የሚያህል ጨርቅ ሱሪ ገድግዶበታል።
ወያኔ ምሽግ ሳይሰራ የቀረው እሱ ሱሪ ውስጥ ብቻ ነበር
ደግሞ ሁሌ ሁሌ የሚል የሀይልዬ ክሊፕ አለ። በሰዓቱ ብዙ እይታ አድርጎ የሰቀለው ቪድዮ ላይ የሚደንሱ ሴቶች ሁለቴ ራመድ.. .ሶስቴ ወደ ኋላ መለስ እያሉ ይጨፍራሉ ። ደግሞ አሰላለፋቸው የኮንሶ ወረዳ ካዘጋጃቸው እርከኖች ፈፅሞ አይለይም።
ወደ ሌላ ሙዚቃ ተሸበለልኩ።
አሸንፈን...አሸንፈን...በማራቶን
ወይኔ ወንድሜ ጆሲ !
የራሱ ትልቀትና የሰውነቱ ቅጥነት የሚመጠጠውን ከረሜላ ቁጭ!
ጀላቲም እንደመምሰል ይላል ። ፈረንጆች ይሄን አይተው ኖሯል ለካ እናንተ ጠኔያሞች ብለው የሚሞሸልቁን።
ነይ በክረምት የሚለው የመስፍኔ ሙዚቃ ለጥቆ መጣ ። የዳሎል ጨው !
ጭው ያለ ፊት ... የኢትዮጵያን መከራ የተሸከመ ፊት...ጦርነት ፊት ። ንግድ ባንክ ፊት ... ከዚህ እስከዛ ፊት ...ከዛ እስከዚህ ፊት ይሄም ቢሆን ግን የእናት አሜሪካ ውለታ ን መዘንጋት የለብንም። የማክዶናንድ በርገር አጋርነትን መርሳት የለብንም። መስፍኔ እንደገና ተወለደ ! መስፍኔ እንደገና አበበ ። መስፍኔ ከጨው ፊት ወደ ፓሎኒ ኳስ ፊት ያሸጋገርክልን ጌታ ክሪሺና ምስጋናህን ውሰድ
ትንሽ ቆየት ያለ የፍቅራዲስ ሙዚቃ ደግሞ ዠመረ ። ብትን ጨርቋ ብትንትን ብሎ መሬት ላይ ፍስስ.. .ስጋ ያልያዘ ፀጉራም ፍየል ቁጭ! ዛሬ እድሜ ለጊዜ ይሁንና የፍቅርዬ ቻፓ ወንዱን ሁሉ እያማለለው ይገኛል /አበበ ብርሀኔ አፉ ይበለኝና ቻፓዋ ግን ይመስጣል! /
ቴዲ አፍሮን ብነካ ጀማው ይነክሰኛል እንጅ የሆነ ዳፍንታም መነጥር አድርጎ ለማን ልማሽ እያለ መሞዘቁን ላሽ ልል አልፈልግም። ለዛ ክሊፕ ሳይሆን ለብረት ቤት ብየዳ አገልግሎት ነበር ያ መነጥር መዋል የነበረበት ።
ከአፍታ በኋላ ቴድዮ ከተፍ አለች ። ጡት ከጣለ ሳምንት ያልሞላው ምስኪን ራፐር ። የጉራጌ ቶን ምናምን ክሊፑ ላይ ሲደንስ ሳየው እንደ ወፍ እንዳይበር እንዴት እንደፈራሁለት ብታዩ!
በሰው ይሄን ያህል ስቄ ከ አራት ዓመታት በፊት የተነሳሁትን የራሴን ፎቶ አየሁት ።
በዛን ጊዜ ሉሲን አገኘኋት ያለው አንትሮፖሎጂስት እኔ አይቶ መሆንማ አለበት !
እህል ከቀመሰ ዓመታት ያስቆጠረ ነብይ ይሄን ያህል አይሞግግም። ስማር ነበር ወይስ ተማሪዎችን ፉጨት ሳስተምር ነበር ? በሚል ጥያቄ ትንሽ እንደተወዛገብኩ.. . የመሰረት መብራቴ ድራማ ሰተት ብሎ ላፕቶፔ ስክሪን ላይ ተገሰጠ ። መሲ የኔ Philps ከጥንት እስከ ጠዋት አንድ አይነት ፊት።
አባቴ በጋን ቁልፍ ጠርቅሞ ሲጠቀምበት የኖረው Philips ካውያ ዛሬም ድረስ አዲስ መሆኑን አስቤ ፈገግ አልኩኝ።
አባዬ ካውያውን ዝም ብሎ ሲያየው ይቆይና አይ የድሮ እቃ! ይላል በግርምት ። በነገራችን ላይ እሷን ካውያ የነካ አይደለም የቁም ሳጥኗን ቁልፍ በእጁ የያዘ የቤተሰቡ አባልን አባዬ በርግጫ እንደ ኳስ ያነጥረው ነበር ። ቀልቃላዋ ታናሽ እህቴ ስንት ጊዜ በረንዳውን ተሻግራ የግቢው አበባ ላይ እንዳረፈች እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው !
ሸሚዙን ጠረጴዛ ላይ ጥሎ ካውያውን ከወዲህ ወድያ ሲያንገላታው መሲዬ ን ያሰቃያት እየመሰለኝ በልቤ አዝንበት ነበር :)

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Mikael aschenaki