Get Mystery Box with random crypto!

እውነት እብዱ ማነው? (እውነተኛ ታሪክ) #ክፍል አንድ እነሆ… እውነት እብዱ ማን ነው…? ልክ የ | ወግ ብቻ

እውነት እብዱ ማነው?
(እውነተኛ ታሪክ)
#ክፍል አንድ

እነሆ… እውነት እብዱ ማን ነው…? ልክ የዛሬ ሶስት ዓመት በዕለተ ባለወልድ አጥቢያ (ሐምሌ 28 ለሐምሌ 29) ከሌቱ ስምንት ሰዓት ገደማ ጥቂት ቀሳውስት ለቅዳሴና ማህሌት ወደ ቤተክርስቲያኒቷ እየገቡ ሳለ አንደኛው ቄስ ከቅፅሩ ባሻገር የትኩስ ውልድ ሕጻን ልቅሶ ድምፅ ሰምቶ ቆም አለ፡፡ ‹‹ይሰማችኋል የሕጻን ልጅ ልቅሶ…›› አለ፡፡ ሌሎቹም ጆሮአቸውን ቀስረው ይሰማል የተባለውን ድምፅ ለመጋራት ቆም አሉ፡፡ እንዳለውም ወዲያው የሕጻን ድምጽ ልቅሶ በድጋሜ ሲሰማ እውነትም ከቤተክርስቲያኑ ቅፅር ጀርባ ከወደ መቃብር ቤቶቹ አካባቢ የሚሰማው ድምጽ በጉልህ የትኩስ ውልድ ሕጻን እንደሆነ አረጋገጡ። የሐምሌው ዝናብ እኝኝኝ… ማለቱን ከጀመረ ቆይቷል… ይበርዳል…!
ከየት ነው…? የማን ነው…? ተጥሎ ነው…? የምን ጉድ ነው…? ወዘተ የመሳሰሉ ጥያቄ እያመላለሱ ሳለ ከመሃከላቸው አንደኛው ትንግርቱን የሚፈታ መላ መታ፡፡ ‹‹እናንተ… ያቺ እብድ እኮ ነፍሰ-ጡር ነበረች… እሷ ወልዳ መሆን አለበት…›› አላቸው፡፡ ሌሎቹም የተሰጠውን መላምት ከግምት በላይ እርግጠኛ ሆነውበት ምንም ሳይነጋገሩ በጥቆማው ተግባብተው ድምጹ ወደሚሰማበት የቤተክርስቲያኑ ቅፅር ጀርባ እየተጣደፉ ዘለቁ፡፡ "ያቺ እብድ" የተባለችው ይቺ ሴት ግን ማን ናት…? መጀመሪያ እሷን በጥቂቱ ላስተዋውቃችሁ፡፡ ስሟ በሀገሬው ሕዝብ ዘንድ “እብዷ” ይባላል፡፡ በቃ ይሄ ነው መጠሪያዋ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ምናልባትም ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ነው እዚህ ከተማ የተገኘችው፣ ወይም “አምጥተው የጣሏት” ይላሉ ነዋሪዎቹ፡፡ በነገራችን ላይ ለምን እንደሆነ ባይገባትም ከተማውን በደንብ የምታውቀው እህቴ እንደነገረችኝ ከሆነ ብዙ እብዶችን በመኪና እያመጡ እዚህ ከተማ መጣል የተለመደ ነገር ከሆነ ቆይቷል፡፡ “ለእብድ መኖሪያ የሚሆን ተመራጭ ከተማ…” የሚለው ግርምተ-ሃሳብ ውስጤ ተመላለሰ፡፡ አንዳች መልስ የማገኝለት ይመስል ሃሳቡ ለአፍታም ቢሆን ውስጤ መቆየቱ ለራሴ ፈገግ አሰኘኝና ተውኩት፡፡ ክረምት ይሁን በጋ፣ ቀን ይሁን ማታ፣ “እብዷ” እዚህ ከተማ ከታየችበት ቀን ጀምሮ እስካሁን እርቃኗን ነው የምትውለው፣ እርቃኗን ነው የምታድረው፡፡ አንዳንድ ደግ ሰዎች እንደምንም ብለው ልብስ ሲያለብሷት በደማቅ ፈገግታ ታጅባ ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ የለበሰችውን ልብስ እንደ አንዳች ትንግርት ዙሪያ ገባውን ትመለከተዋለች፡፡ ይገርማታል ያስቃታል…! ከዚያ ሰዎቹ ዘወር ካሉ በኋላ ወዲያው አውልቃ ትጥለውና የለመደችውን ነጻነት በድጋሜ ተጎናፅፋ መለ–መላዋን ትቀጥላለች፡፡ በየትኛውም ቋንቋ ቢያናግሯትና ቢጠይቋትም በጠያቂው ድምፅ ወይም ቋንቋ ወይም ንግግር ከመደመምና አጫ በረዶ የመሰለውን ጥርሷን ብልጭ እያደረገች ፈገግ ከማለት ውጪ መልስ የሚባል ነገር ሰጥታ አታውቅም፡፡ የማትናገረው በተፈጥሮዋ “መናገር የተሳናት” ሆና ይሁን ወይም “እብዷ” ካሰኛት
የአዕምሮ ጤና መታወክ የተነሳ አይታወቅም፡፡ በአጭሩ ከፈገግታ በቀር አትናገር አትጋገር አይነት ናት፡፡ “እብዷ” እዚህች ትንሽ የገጠር ከተማ ከመጣች ጀምሮ ሰው ተተናኩላ አታውቅም ይላሉ፡፡ የተወለደችበትን አካባቢ ወይም ነገደ-ቋንቋዋን የሚያውቅ የለም፡፡ የሚገምትም የለም፡፡ ቁመቷ ሎጋ፣ ቀለሟ ጥቁር የሚባል፣ ፀጉሯ ከርዳዳና አጭር፣ አፍንጫዋ ሰልከክ ያለ፣ ጥርሷ ድርድር ያለ ነጭ ነው፡፡ ይህ ነው ስጋዊ መገለጫዋ፡፡ ከዚህ ውጪ እሷ ማለት በቃ “እብዷ” ናት፡፡ እዚህች ትንሽ ከተማ “አምጥተው ከጣሏት” ጀምሮ እዚያችው ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ገባ እየዋለች፣ በመረጠችው መቃብር ቤት እያደረች፣ ቀንም ሆነ ማታ እርቃኗን በመሆን በራሷ ዓለም መኖር ጀምራለች፡፡
አንድ ክፉ ቀን “ጤነኛ” የሚባል/የሚባሉ የሆነ አካባቢ ሰው/ሰዎች ነው/ናቸው
አሉ እስኪደፍራት/እስኪደፍሯት ድረስ…
በዚያም ሰበብ እስክትፀንስ ድረስ…
ለሐምሌ ባለወልድ አጥቢያ በድቅድቁ ጨለማ ራሷ ሽሏን እስከምትገላገል ድረስ…
÷÷÷
ቄሶቹ የሚሰሙትን የአራስ ሕጻን ልጅ ልቅሶ አቅጣጫ እየተከተሉ፣ ድምጹ ከሚመጣበት ቦታ አካባቢ ሲደርሱ እውነትም “እብዷ” እንደማንኛውም ውሎ
አዳሯ ሁሉ በዚያ በሐምሌ ጨለማ በሐምሌ ቁር… በሐምሌ ዝናብ… እርቃኗን በድቅድቁ ጨለማ ውስጥ ቆማለች፡፡ አይናቸውን አጥብበው በጣም ተጠግተው ሲመለከቷት ደግሞ ከደቂቃዎች በፊት እዚያው እመቃብር ቤቶች አካባቢ አምጣ የወለደቻትን ልጅ ለፈጣሪ መስዋዕትነት የምታቀርብ ይመስል፣ ሕጻኗን በአንድ እጇ ወደላይ ከፍ አድርጋ ይዛ እንደተለመደው ፈገግ ትላለች፡፡ የሕጻኗ እትብት ከሕጻኗ ሆድ ጀምሮ ወደታች እስከ እናትየው እግሮች መሃል ድረስ ይወዛወዛል፡፡ ከእናትየው መዳፍ ብዙም የማትተልቀው ሕጻን በዚያ ሐምሌ ቁር እና ዝናብ እየተቀጠቀጠች በእሪታ ትነዝራለች፡፡ [ቄሶቹ የፈጣሪን እና የቅዱሳንን ስም እየጠሩ ማማተባቸውና ማነብነባቸውን መገመት ቀላል ነው፡፡]
ቄሶቹ በወቅቱ ምን አስበው ይሁን መረጃው ባይኖርም፣ በወቅቱ የወሰኑት ውሳኔ ከቤተክርስቲያኗ ፊትለፊት የሚገኝ አንድ ግቢ አስገብተውና የግቢውን በር
ዘግተው መሄድ ነበር፡፡ ግቢው ደግሞ አንድ ደግ የአካባቢው ሰው ደካማ
አዛውንቶችን የሚያኖሩበትና የሚረዱበት ነው አሉ፡፡ ለማንኛውም ቄሶቹ እዚያ
ግቢ አስገብው ወደ ቅዳሴአቸው ሄደዋል፡፡ (እዚህ ጋር ቄሶቹ ያደረጉት ነገር መልካም ነው ብዬ ለማሰብ ተቸግሬአለሁ…)
÷÷÷
የሐምሌው ዝናብ ሌቱም አልበቃ ብሎት ንጋትም እንዲሁ ሲንዛዛ ስለ ነበር፣በግቢው ውስጥ የሚኖርና በጠዋት የተነሳ ማንም ሰው አልነበረም፡፡ ከጠዋቱ ወደ ሶስት ሰዓት ገደማ በግቢው ውስጥ ከሚኖሩት ተረጂ አዛውንቶች መካከል አንዳቸውን ለመጠየቅ መጀመሪያ ወደ ግቢው የዘለቀችው አንዲት ወጣት ልጅ
ነበረች፡፡ ልጅት ወደ ግቢው ስትገባ ዙሪያ ገባ ከሚገኙት ክፍሎች መካከል ከኩሽና
ያልተናነሰውና ክፍት ከነበረው አንደኛው ክፍል ደጃፍ ላይ "እብዷ" አንዳች በጭቃ ተጨማልቆ የተድበለበለ ነገር ይዛ ወደላይ እየወረወረችና እየቀለበች ስትጫወትበት ተመለከተች፡፡ ልጅት ያየችው ነገር ትንንሽ እጆችና እግሮች
ስላሉትና ከሆዱ ደግሞ አንዲት ትንሽዬ ቁራጭ የምትወዛወዝ ነገር ስላየች በጣም ደንግጣ ጩኸቷን አቀለጠችው፡፡
የተኛም ያልተኛም ከየቤቱ ወጥቶ ምን ሆንሽ ቢሏት…‹‹እብዷ… እብዷ… እብዷ…. የሆነ አውሬ መሰለኝ… የሆነ አውሬ ነገር ይዛ እየተጫወተችበት ነው…›› ብላ እየተንቀጠቀጠች በጣቷ ወደ “እብዷ”
ትጠቁማለች፡፡ ሰዎቹም እየተጣደፉ ቢጠጉ “እብዷ” አሁንም ፈገግታዋን እያጀበች ሌት በ8:00 ገደማ በወለደቻትና በጭቃ ስታንደባልላት ባደረችው ልጇ አሁንም ትጫወታለች፡፡ አሁን የሕጻኗ እትብት ከእናትየው ተለያይቶ ትንሽዬ የእትብት ቅሪት በሕጻኗ ሆድ ላይ ተንጠልጥላለች፡፡ ራሷ ነች አሉ በጥሳ የለየችው፡፡ በጭቃ ተለውሳ ከተጨማለቀችው ልጅ ምንም አይነት ድምፅ የለም፡፡ በግቢው የነበሩት ሰዎች ተረባርበው ልጅቷን ከእናትየው ነጥቀው መሬት ላይ አስተኝተው ይተረማመሳሉ፡፡
ግንባሯ ላይ ድፍት ያለው ፀጉሯ ፈረንጅ የሚያሰኛት… ከአንድ መዳፍ በላይ
የማትተልቅ አንዲት እፍኝ ሴት ሕጻን ልጅ ትኑር ትሙት ለማወቅ የሚሞክር
ጠፍቶ ሁሉም እርስበርሱ እንደተፈራራ የሆነች እራፊ ጨርቅ ላይ አስተኝተዋት
አሁንም ወዲህ ወዲያ ይዋዥቃሉ… ይጮሃሉ… ይንጫጫሉ… አንዱ ይገባል…
የሚያየውን ማመን አቅቶትና ዘግንኖት እየሮጠ ይወጣል… ሌላው የተፈጠረውን
ለመመልከት ወደ ግቢው እየሮጠ ይገባል… ሁሉም ወዲህ ወዲያ ይላል…
ዝናቡም እኝኝኝ… ይላል…
÷÷÷
አባዬ፣ አለወትሮዋ የጠዋቱ ብርድ እና ዝ