Get Mystery Box with random crypto!

[መደነቃቀፋችን ዳንስ መስሎን ነበረ] የስልኬ ሙዚቃ ማጫዎቻ ላይ ሙሉ ቀን እየተደጋገመ ሲዘፍን የዋ | ወግ ብቻ

[መደነቃቀፋችን ዳንስ መስሎን ነበረ]
የስልኬ ሙዚቃ ማጫዎቻ ላይ ሙሉ ቀን እየተደጋገመ ሲዘፍን የዋለው የBen E.King 'stand by me' የሚል ዘፈን ነው። ሁልጊዜ ለምን እንደዛ እንደማደርግ አይገባኝም ፤ አንድ ሙዚቃ ደጋግሜ አደምጣለሁ። አንዳንዴ ለተከታታይ ቀናት ሌላ ዘፈን ሳልቀላቅል ካለማቋረጥ የምሰማቸው ዘፈኖች አሉ፤ ከወደድኩት ነገር ላይ ቶሎ መላቀቅ የሚከብደኝ ለዛ ነው በቃ ከያዝኩ እንደዚ ነኝ ስወድ አፍናለሁ ስወድ አስጨንቃለሁ፤ ለራሴ ራሱ የሚረብሸኝ ባህርዬ ነው እና አዲስ ለሚተዋወቁኝ ሁሉ መጀመሪያ የምናገረው ነገር "ስወድ አስጨንቃለሁ.....ስወድ ችግር አለብኝ"ን ነው። ዘፈኑ ደግሞ አሁን እንዲህ እየተስረቀረቀ ሩቅ ልውሰድሽ ይለኛል፤ ረስቼዋለሁ ትቼዋለሁ ወዳልኩት ትናንት አጅቤሽ ካልሄድን እያለ ያባብለኛል ....
"አሻቅበን ያየነው ሰማዩ ተገምሶ ላያችን ቢደፋ ፣ ወይ ደግሞ _ ግዙፍ ተራራ ተንዶ ከውቅያኖስ ገብቶ ቢጠፋ፣
ማልቀስ እርም ነው ለኔ _አንዲት ዘለላ እንባ እንኳ 'ካይኔ ጠብ አትል አትፈስ፣
አንተ አጠገቤ እስቆምክ ከጎኔ እስካለህ ድረስ፣" አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው በአብሮነታችን ውስጥ የነበሩ እንደቀልድ ያለፍናቸው ፤ በእብደታችን ያሸበረቁ በሳቅ ያከበብናቸው በኩርፊያ ያጀብናቸው አያንዳንዱ ቅፅበታት እጅግ ውብ ቢሆኑም ልክ ናቸው ብዬ የማስብበት ዘመን አልፏልና ድጋሚ በጨረፍታም ላስባቸው አልፈልግም። በርግጥ አንዳንዴ ከነዚህ ቀናቶቻችን ጥቂት የእብደት ስራችን የጎላባቸውን
እያነሳሁ ለወዳጆቼ ስነግራቸው ( በትንሹ፤ ስለ ምሽት ባሌት ዳንሳንችን፣ ፀጉሬን ሰብስቦ በስርአት ስለሚያያይዝበት ሻጤ። በአብዛኛው ደግሞ ስለ ፍትወት፤ የቃምነው ጫት ገረባ ላይ ስለምንፈፅመው ሩካቤ፣ ማዕዳችንን ገፍተን ስላጧጧፍነው ወሲብ፣ ዝናብ እየዘነበ ጭቃ ላይ ስላደረግነው ፣ ምናምን) ወይ 'ያማችኋል ግን?' ወይም 'እብድ ናችሁ? ' ካልሆነ ደግሞ 'ይሄ ልክ አይደለም ! '
ይሉኛል። የምንወደው እብደት ውስጥ አብረን እንዋኝ እንደነበር፤ ነፃነት እና እውነት ከሰሩት እብደት በላይ ልክነት እንደሌለ ጨምሬ ልነግራቸው ፈልጌ በቸልታ ትከሻዬን ሰብቄ እተወዋለሁ። ግን እንደዛ ያሉኝ ዕለት አመሻሽ ላይ ናፍቆኛል ልቤ እስኪርድ ናፍቆኛል አለ አይደል የኔና የእርሱ አለም በራሳችን ህግ ተከልሎ በእብደታችን የቆመ ፍፁም ሌላ ፕላኔት ነበርና ማንም የሰራነውን አለም ልክ አይደለም ቢለን የምንሰማ አይነት አልነበርንም፤ አንዳችን ላንዳችን እስካለን
ድረስ የምንፈራው ምንም ነገር አልነበረም። "ምሽቱ በመጣ ጊዜ፤ ምድር ፅልመት ስትለብስ፣ ድቅድቅ ጨለማው መሃል ጨረቃ ብቻ ተግታ ብርሃኗን ለእኛ ስትለግስ፣ ፍፁም ልፈራ አልችልም _
አንተ አጠገቤ እስቆምክ ከጎኔ እስካለህ ድረስ፣" ከሆነ ጊዜ በፊት ወደ ኋላ ተመልሼ አመሻሻችን እንዴት እንደነበር ሳጤን ከሰርክ እለት ዑደታችን ( ስንራኮት ከዋልንበት ከእርሱ ቤት ወደ ቤቴ ሲሸኘኝ) በመንገዳችን አሳብረን የምናልፈው የኡሪዎች ኳስ ሜዳ ነበር፤ ልክ እዛ ስንደርስ ከላያችን የምታበራ ጨረቃ ጥላችንን ፍንትው አድርጋ ስታሳየን ከጥላዎቻችን ጋር የደነስንበት በምሽት ከደመቀ ውበቷ ላይ ቅርፁን ቀይሮ ብርሃኗ ዜማ ሆኖ በጆሮዎቻችን ተንቆርቁሮ እንደነበር አስቤ አውቃለሁ።
በፊት ላይ ሲናፍቀኝ ከሁሉ ከሁሉ በግድግዳው እና በአልጋው ክፍተት መካከል ከፀጉሬ ሾልካ የወደቀች የአንዲት የሻጤ ነገር ያሳስበኝ ነበር። ስለ እርሷ ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝና ባገኘውና ብጠይቀው እወድ ነበር። ከኔ በኋላ ቤቱን እና ገላውን የጎበኘች እንስት ከአልጋ ተንሸራቶ በዚያ በኩል መሬት ያረፈ የውስጥ ሱሪዋን እጇን ሰዳ ስታስስ የፀጉሬ ሁለት ዘለላ
የተተበተበበት ያን ሻጤ ያገኘች እለት ምንድነው የሚሰማት? ምንስ ነው
የምታስበው? እርሱም ከእኔ ጋር እንደለመደው ፍቅር ሲሰሩ የተንጨፋረረ ፀጉሯን ከጉዳያቸው በኋላ ሰብስቦ ሊያስይዝላት አልጋቸው ላይ የተበታተ የፀጉሯን ማያያዣ ሲያስስ አንዱን ተሳስቶ ገፍቶ በቀደመው ክፍተት ቢልከው፤ አልጋ ስር የተገናኙ ሁለት ሻጤዎች እንደ ባለቤቶቻቸው በጣውንትነት ስም ይጠራሩ ይሆን? የየራሳቸውን የውድቀት ታሪክ እና የሴቶቹን እንዝህላልነት እያነሱ ይወያዩ ይሆን? ወይስ... ለየባለቤታቸው ወግነው ቀጫጫ ሽቦ አካላቸውን ለድብድብ ያነሳሉ? ወይስ... እዛው ባሉበት ብዙ ቀናትን አሳልፈው ቤት አፀዳለሁ በሚል ሰበብ አልጋ በምትጎትት ሶስተኛ ሴት እጅ ከወዳደቁበት ተነስተው የወረሳቸው ትቢያ እፍፍ ተብሎላቸው ድጋሚ አናት ላይ ይወጣሉ? እና የናፈቀኝ እለት ወይስ ...... ወይስ ... ወይስ እያልኩ ስለ ጥቃቅኗ ነገር ሁሉ በጥልቅ የማስበው እና የምብከነከነው ከእለታት ድሮ ቀን በወጣች ደንጋዛ እና ፈዛዛ ጨረቃ ደነስን ያልነው መደነቃቀፍ፣ በሌላ ጥንት በሚመስል ቀን ከፀጉሬ የወደቀ ወልጋዳ ሽቦ ምናምን የገዘፈ ጥቅም ኖሯቸው ሳይሆን ከእርሱ ጋር የነበሩኝን ቅንጣቶች በሙሉ ከቋጥኝ አግዝፌ ስለማይ ነበር።
አሁን ላይ ዛሬን በአሁን መለካት ሳይሆን በነገ መስፈር ስለለመድኩ እንደ ጥንቱ
ስወድ አላስጨንቅም፣ አሁን Ben E.King ሳምንት ሙሉ ልብ በሚበላ ብሉዝ ቢለምነኝ እንኳ የሚያንኳኳውን የትዝታ በር ለመክፈት የምጥር አይነት
አይደለሁም። ዘንድሮ ከተረት እና ከኩሸት የቻልኩትን ያህል ተምሪያለሁና ይሄ ይሄ ትዝ ሲለኝ የምለው "የሁሉንም ነገር ዋጋ በሰአቱ መረዳት ብንችል ህይወት እንዴት ውብ ይሆን ነበር" ነው። የማዝነው የማይገባቸውን ዋጋ ሰጥተን ላጡን እና ላጣናቸው ስናላዘን ስለተላለፉን ቀናት ነው።

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Elssa Mulugeta