Get Mystery Box with random crypto!

እንኳን ለዳግሚያ ትንሣኤ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††በስመ አብ ወወልድ ወ | ውዳሴ ማርያም/wdasemaryam

እንኳን ለዳግሚያ ትንሣኤ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ለስም አጠራሩ ጌትነት ይድረሰውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ በጉባኤ ሦስት ጊዜ ተገልጦላቸዋል።
፩.በዕለተ ትንሣኤ ምሽት በፍርሃት ሳሉ
፪.ያላመነ ቶማስን ለማሳመን በተነሣ በስምንተኛው ቀን (ማለትም ዛሬ)
፫.ከተነሣ ከሃያ ሦስት ቀናት በኋላ በጥብርያዶስ ባሕር ዳርቻ ላይ ነው።

ጌታ አርባውን ቀን ለአንዱም ለሁለቱም በግል ይገለጥላቸው ነበር። እመቤታችንን ግን ፈጽሞ አይለያትም ነበር።

ጌታችን ከተነሣ በኋላ ለሳምንት ተለይቷቸው ስለ ነበር በቤተ ክርስቲያን ውዳሴ ማርያም እንጂ መልክአ ኢየሱስ በማኅበር አይደገምም።

በዚህች ዕለት ደቀ መዛሙርቱ በጽርሐ ጽዮን ሳሉ ጌታችን "ሰላም ለእናንተ ይሁን።" ብሏቸዋል። ቶማስንም "ና ዳስሰኝ።" ብሎታል። ሐዋርያው እጁን ከተወጋ ጐኑ ላይ ቢያሳርፍ በመቃጠሉ "ጌታዬ አምላኬም" ሲል ጮሆ ምሥጢረ ተዋሕዶውን መስክሯል።

ጌታም ቶማስን "እስመ ርኢከኒሁ አመንከኒ - ስላየኸኝ አመንከኝ!
ብጹዐንሰ እለ እንዘ ኢይሬእዩኒ የአምኑኒ - ሳያዩ የሚያምኑ ግን ብጹዐን (ንዑዳን ክቡራን) ናቸው።" ብሎታል።
(ዮሐ. ፳፥፳፬)

ጌታችን ከትንሣኤው እና ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከትን ያድለን።

"ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ። በመካከላቸውም ቆሞ 'ሰላም ለእናንተ ይሁን።' አላቸው። ከዚያም በኋላ ቶማስን 'ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ። እጅህንም አምጣና በጐኔ አግባው። ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን።' አለው። ቶማስም 'ጌታዬ አምላኬም' ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም 'ስላየኸኝ አምነሃል። ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው።' አለው።"
(ዮሐ ፳፥፳፮-፳፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር