Get Mystery Box with random crypto!

እንኳን_ለበዓለ_ሆሳዕና_በሰላም_አደረሳችሁ !!! የሆሳዕና በዓል | ውዳሴ ማርያም/wdasemaryam

እንኳን_ለበዓለ_ሆሳዕና_በሰላም_አደረሳችሁ !!!



የሆሳዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩስአሌም ሲገባ የሚቀድሙት እና የሚከተሉት ህዝብ በተለይም አእሩግ እና ህጻናት “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም ሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሳዕና በአርያም “ በማለት ጌታችንን መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው።
ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራው ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ነው።
ሆሣዕና ከረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተክርስቲያን የበዓል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። ይህ በዚሁ በዓለ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‘ሆሣዕና በአርያም’’ ‘ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት’’ ‘ዕለተ ሆሣዕናሁ አርአየ… ‘ ወዘተ. በማለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድና ሌሎችም አባቶች በየቦታው እየጠቀሱና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሣዕና በአርአያም እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው።
አስቀድሞም በነቢየ እግዚአብሔር ዘካሪያስ እንደተነገረው ‘አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበለሽ ፣አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያያቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል… ሰላምን ይናገራል’’ 《ዘካ.9፣9》። በማለት እንደሚመጣና የሠላምንም ብሥራት እንደሚያበሥር ተናገሮ ነበር።
ሲመጣም ‘ሁሉም ፈጥነው ልብሳቸውን ወሰዱ በሰገነቱም መሰላል እርከን ላይ ከእግሩ በታች አነጠፉት።’’ በማለት ሊደረግለት የሚገባውን ገልጿል። 《2ኛ ነገ. 9፣13》 ።
የሆሣዕና በዓል በቤተክርስቲያን ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ፀበርት ወይም ዘንባባ በመያዝ ‘ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር - በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው።’’ 《መዝ.117፣26》 በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብና በማድረግ ቤተክርስቲያናችን ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታድላለች።
በቤተክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ይህን በዓል የሚመለከቱ
የቅዱስ ማቴዎስ 《ማቴ. 21፣1-17》፤
የቅዱስ ማርቆስ《ማር.11፣1-10》፤
የቅዱስ ሉቃስና 《ሉቃ.19፣29-38》፤
የቅዱስ ዮሐንስ 《ዮሐ.12፣12-15》ወንጌላት ይነበባሉ
እንኳን ለበዓለ ሆሳዕና በሰላም አደረሳችሁ ።