Get Mystery Box with random crypto!

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በአርጋኖን መጽሐፉ ላይ፡- “ከርሠ ድንግል ሰፍሐ እምሠረገላ ብርሃን ዘመልዕ | ውዳሴ ማርያም/wdasemaryam

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በአርጋኖን መጽሐፉ ላይ፡-
“ከርሠ ድንግል ሰፍሐ እምሠረገላ ብርሃን ዘመልዕልተ ጌልጌል…” (የድንግል ማሕፀን በሰማይ ካለው የብርሃን ሠረገላ ሰፋ፤ የድንግል ማሕፀን ከአየራት በለጠ፤ በሱራፌልና በኪሩቤል ዘንድም ተመሰገነ፤ የድንግል ማሕፀን የሰማይ ደጃፍ ኾነ፤ ሳይከፈትም የፀሓይ መውጪያና መግቢያ ኾነ፤ የድንግል ማሕፀን ለአማናዊ የጽድቅ ገንዘብ ሣጥን ኾነ፤ የድንግል ማሕፀን አዶናይ በመባል ለሚጠራ እግዚአብሔር ማደሪያን ኾነ) በማለት “ሀገረ እግዚአብሔርነቷን በጥልቀት በማሕፀኗ ከተከናወነው ከተዋሕዶ ምስጢር በመነሣት አስተምሯል፡፡

በተጨማሪም በእንዚራ ስብሐት የነገረ ማርያም መጽሐፉ ላይ ምስጢሩን እንደ ወርቅ አንከብልሎ እንደ ሸማ ጠቅልሎ፦

“ኦ እግዝእትየ ማርያም ርግበ ተደንግሎ
እዌድሰኪ በአዕብዮ ወእባርከኪ በአልዕሎ
እስመ ኮንኪዮ እሞ ለዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ
ዘኢያገምሮ ሰማይ ወስፍሐ ምድር ኢየአክሎ”
ጽበተ ከርሥኪ ጾረ ወአግመረ ኀይሎ”

(የድንግልና ርግብ እመቤቴ ማርያም ሆይ በማግነን አመሰግንሻለኊ ከፍ ከፍ በማድረግም አመሰግንሻለኊ ከዓለም አስቀድሞ ለነበረ አካላዊ ቃል እናቱን ኾነሻልና ሰማይ የማይችለውንና የምድር ስፋትም የማይበቃውን ጠባብ ማሕፀንሽ ተሸከመው ኀይሉንም ቻለ) በማለት ተመሳሳይ የአድናቆት ምስጋናን አመስግኗል፡፡

ሊቁ አባ ሕርያቆስም ስለዚኽ ምስጢር በቅዳሴ ማርያም መጽሐፉ በቊ ፵፭ ላይ ሲገልጽ፡- “ወሶበ ርእየ ንጽሕናኪ ለሊሁ እግዚአብሔር አብ …” (ርሱ ቅሉ እግዚአብሔር አብ ንጽሕናሽን ባየ ጊዜ ስሙ ገብርኤል የሚባል ብርሃናዊ መልአኩን ወደ አንቺ ላከ፤ መንፈስ ቅዱስ በላይሽ ይመጣል የልዑል ኀይልም ይጋርድሻል አለሽ፤ ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ፤ ሳይወሰን ፀነስሺው በላይ ሳይጐድል በታችም ሳይጨመር በማሕፀንሽ ተወሰነ፤ መጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መለኮት በማሕፀንሽ ዐደረ) በማለት መልእክተኛው ቅዱስ ገብርኤል አስቀድሞ ተልኮ ቅድስት ድንግል ማርያምን ሲያበሥራት፤ ርሷም ቃሉን በእምነት በተቀበለች ጊዜ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የአብ የባሕርይ ልጅ በማሕፀኗ የማደሩን ነገር አስተምሯል፡፡

ይኽ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት አምላክ በማሕፀነ ማርያም ያደረበትን የፅንሰቱን በዓል ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በታላቅ ድምቀት በምስጋና፣ በቅዳሴ፣ በትምህርት መጋቢት ፳፱ ቀን ስታስብ ከጌታችን ዘጠኙ ዐበይት በዓላት ውስጥ አንደኛውና የመጀመሪያው አድርጋ ታስበዋለች፡፡
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ