Get Mystery Box with random crypto!

[መጋቢት 29 ወልደ እግዚአብሔር በአመቤታችን ማሕፀን የተፀነሰበት ታላቅ በዓል] በመጋቤ ሐዲስ ዶ | ውዳሴ ማርያም/wdasemaryam

[መጋቢት 29 ወልደ እግዚአብሔር በአመቤታችን ማሕፀን የተፀነሰበት ታላቅ በዓል]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
ቅድስት ድንግል ማርያም በአረጋዊዉ በዮሴፍ ቤት እያለች ለትሩፋት አትገበዝም ነበርና ከዕለታት ባንዳቸው ውሃ ለመቅዳት በሀገራቸው ወደሚገኝ ወደ ውሃ ጒድጓድ ኼዳ ስትመለስ “ሑር አብሥራ ለማርያም ከመ እትወለድ እምኔሃ” (ከርሷ እንድወለድ ኼደኽ ለድንግል ማርያም ንገራት) ብሎ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን በስድስተኛው ወር ወደ ርሷ ላከው (ሉቃ ፩፥፳፮)።

ምን በኾነ በስድስተኛው ወር ተላከ ብሎ ሉቃስ ጻፈ ቢሉ? ለጊዜው ዮሐንስ በመስከረም ወር ተፀንሷል የጌታ ፅንስ ደግሞ በመጋቢት ፳፱ ነውና ከመስከረም አንሥቶ እስከ መጋቢት ቢቈጥሩ ስድስት ወር ይኾናልና “በስድስተኛው ወር” አለ፤ ፍጻሜው ግን በስድስተኛው ቀን (በዕለተ ዐርብ) የተፈጠረው አዳም በድሎ ነበርና ርሱን ለማዳን በርሱ ያጣነውን ልጅነት ለመመለስ እንደመጣ ለማጠየቅ።

ዳግመኛም ፭ሺሕ ፭፻ ዘመን ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዘመን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከጌታ ወደ እመቤታችን ተላከ ማለቱ እንደኾነ መተርጒማን ያስተምራሉ ፡፡

ከዚያም መልአኩ ተገልጾላት ብሥራትን አሰማት፤ ርሷም አይታው ኼደች፤ ኋላም ወደ ቤት ገብታ ማድጋዋን አሳርፋ ሳለ ረቂቅ ነውና ተሰውሮ “ትፀንሻለሽ” አላት፤ ርሷም “ይኽ ነገር ደጋገመኝ ደግ ነገርን በደግ ቦታ ኹነው ሊረዱት ይገባል” ብላ፤ ወደ ቤተ መቅደስ ኼዳ በዚያ ወራት ለቤተ መቅደስ መጋረጃ ለመፍተል ከደናግለ እስራኤል ጋራ የተካፈለችውን ሐርና ወርቀ እያስማማች ስትፈትል መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለሦስተኛ ጊዜ ተገልጾላታል፡፡

የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ሐርንና ወርቅን አስማምታ ስትፈትል ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ እንዳበሠራት ቅዱስ ያሬድም በድጓው ላይ፡-

“ቅዱስ ገብርኤል መልአከ ፍሥሓ በእሳት ሥዑል
ሰበካ ለድንግል ምጽአቶ ለቃል
ወርቀ ወሜላተ እንዘ ትፈትል”
(በእሳት የተቀረጸ የደስታ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ወርቅንና ሐርን ስትፈትል የቃል መምጣቱን (ሥጋ መኾኑን) ለድንግል አበሠራት) በማለት ገልጾታል ፡፡

አባ ጽጌ ድንግልም ሐርንና ወርቅን አስማምታ ስትፈትል መልአኩ እንደተገለጠላት በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፉ ላይ፡-

“ፈትለ ወርቅ ወፈትለ ሜላት አመ በአጽባእትኪ ተባየጹ
አምሳለ መለኮት ወትስብእት እንዘ ኢየሐፁ
ተአምረ ብርሃን ማርያም ለፀሓየ ጽድቅ አንቀጹ
ጸገይኪዮ እንበለ አብ በሰሚዐ ቃሉ ወድምፁ
ለገብርኤል መልአክኪ ዘፍሡሕ ገጹ”
(የእውነት ፀሓይ መውጫ የብርሃን ምልክት ማርያም የትስብእትና የመለኮት ተዋሕዶ አምሳል ሳያጐድሉ የሐርንና የወርቅን ፈትሎች በጣቶችሽ በሚፈተሉበት ጊዜ ፊቱን ደስ ያለው የተላከልሽ የገብርኤል ድምፁን በመስማት ጌታን ያለ አባት ፀነስሺው) በማለት ገልጾታል፡፡

መልአኩ ስለምን ሦስት ጊዜ ታያት ቢሉ? ለጊዜው ሰይጣን የኾነ እንደኾነ አንድ ጊዜ ታይቶ ይጠፋ ነበርና ብርሃናዊ መልአክ እንደኾነ ለማጠየቅ ሲኾን ፍጻሜው ግን የሥላሴ ማደሪያ መኾኗን ሲያስረዳት ነው (ሉቃ ፩፥፴፫፤ ማቴ ፲፰፥፲፮)፡፡

ወደ እመቤታችንን ለማብሠር ብዙ መላእክት ሳሉ ቅዱስ ገብርኤል ለምን ከመላእክት ተመረጠ? ቢሉ ቀደምት መተርጒማን ምስጢሩን ጽፈዋል ይኸውም፡-

1ኛ. ቅዱስ ገብርኤልን “እስመ አብሣሬ ፅንስ ውእቱ” እንዲለው በብሉይ ኪዳን ታሪኮች ፅንስን በማብሠር የታወቀ መልአክ ነውና፤ ለምሳሌ የሶምሶንን እናትና አባትን፣ እነ ዘካርያስን ልጅ እንደሚያገኙ ያበሠረ መልአክ ነውና ጥንት በለመደው ይኹን ሲል ርሱን ልኮታል (መሳ ፲፫፥፳፩፤ ሉቃ ፩፥፲፱)፡፡

፪ኛ. የስሙ ትርጓሜ ተልእኮውን ያመለክታልና ይኸውም ሚካኤል ማለት የቃሉ ትርጉም “መኑ ከመ አምላክ” (ማን እንደ አምላክ) ማለት እንደኾነ ኹሉ ገብርኤል ማለት ሲተነተን “ገብር” ወይም “ጋቦር” የሚለው የዕብራይስጥ ትርጓሜ ሰው ወይም ጠንካራ የሚለውን ፍቺ ሲያመጣ “ኤል” ማለት ደግሞ አምላክ ማለት ነውና ባንድ ላይ “አምላክ ወሰብእ” (አምላክም ሰውም) ማለት ነው፤ ስለኾነም የአምላክ ሰው የመኾን ምስጢርን በስሙ የያዘ መልአክ ነውና እግዚአብሔር ባወቀ ሥጋዌዉን እንዲያበሥር ልኮታል፡፡

፫ኛ. የሥነ ፍጥረት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ መላእክት ተፈጥረው ሳጥናኤል ባወካቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል “ንቁም በበህላዌነ እስከ ነአምሮ ለአምላክነ” (የፈጠረን ይኽ አይደለምና ፈጣሪያችንን እስክናውቀው ድረስ በያለንበት እንጽና) በማለት በተናገረ ጊዜ ፺፱ኙ ነገደ መላእክት በቅዱስ ገብርኤል ቃል ጸንተው ቆመዋል፤ በዚኽ ዓለም ሳለ ጦርን ያረጋጋ መልካም ዐርበኛ ወደ ንጉሡ ዘንድ ደርሶ እንደሚሸለም ኹሉ “ወበእንተዝ ደለዎ ለገብርኤል ከመ ይጹር ዜናሃ ለማርያም” እንዲለው ቅዱስ ገብርኤልም ይኽነን በተናገረበት አንደበቱ የአምላክን ሥጋዌ ለመንገር ለእመቤታችን ባለምሥራች ለመኾን አብቅቶታል፡፡

ጌታም ቅዱስ ገብርኤልን ሳይልክ በእመቤታችን ማሕፀን ማደር ይችላል ግን አስቀድሞ መልአኩን የላከበት ምክንያት ስለምን ነው? ቢሉ፤ ትንቢቱን ለመፈጸም ነው ይኸውም አስቀድሞ በነቢዩ ሚልክያስ ዐድሮ በምዕ ፫፥፩ ላይ፡-
“እነሆ መልእክተኛዬን እልካለኊ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይወጣል” በማለት መላው የሰው ዘር በተስፋ ይጠባበቀው የነበረው፤ ቀደምት አበው ነቢያት ሊያዩት ይፈልጉት የነበረው የአምላክ ሥጋዌን ለማብሠር ቅዱስ ገብርኤልን አስቀድሞ ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ለብሥራት በመላክ፤ በአማናዊት መቅደስ በማሕፀነ ማርያም ፱ወር ከ፭ ቀን የማደሩን ነገር አስቀድሞ በነቢዩ ትንቢትን አናግሯል፡፡

ልዑል እግዚአብሔር ባወቀ ስለ ብሥራቷ ትንቢቱን አስቀድሞ አናግሯል፤ ምስጢሩስ ቢሉ? እነሆ ንጉሥ ወደ አዳራሹ ሊገባ ሲል አንጥፉ አሰናዱ ለማለት መልእክተኛውን አስቀድሞ እንደሚልክ ኹሉ፤ ጌታም የሰማይ የምድር ንጉሥ ነውና፤ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምም ንጽሕት መቅደሱ ናትና፤ ነገሩን አስቀድማ ጠንቅቃ ዐውቃ ተቀብላ ትቆየኝ ሲል ቅዱስ ገብርኤልን ልኮታል (ሉቃ ፩፥፳፮‐፳፰)፡፡

ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስም በዚኽች ዕለት ስለተከናወነው አስደናቂ ምስጢር ሲገልጽ፦ “Today is the beginning of our salvation…,” (ዛሬ የድኅነታችን መጀመሪያና እና የዘላለማዊ ምስጢር መገለጽ ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የድንግል ልጅ ኾነ፤ ቅዱስ ገብርኤል ሊመጣ ያለውን የስጦታውን ነገር እንደተናገረ፤ እኛም ከርሱ ጋር ኾነን ወደ አምላክ እናት በመጮኽ “ጸጋን የተመላሽ ደስተኛዪቱ ደስ ይበልሽ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና” እንበል) በማለት በጥልቀት አስተምሯል።

ከዚኹ ጋራ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፈ ድጓው ላይ “ሰማይ ወምድር ዘኢያገምሮ እፎ እንጋ ማሕፀነ ድንግል ጾሮ” (ሰማይና ምድር የማይችሉትን አምላክ እንደምን የድንግል ማሕፀን ቻለው?) በማለት የጠየቀውን ጥያቄ ሊቃውንት በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በጥልቀት አስተምረዋል፤ ይኸውም እመቤታችን በሰው መጠን ሦስት ክንድ ከስንዝር ስትኾን ርሷ ግን ከጽርሐ አርያም በላይ ርዝመቱ ከበርባሮስ በታች ጥልቀቱ ከአድማስ እስከ ናጌብ ስፋቱ ተብሎ የማይመረመር በኹሉ የመላውን አካላዊ ቃል በማሕፀኗ የተሸከመች በመኾኗ “የእግዚአብሔር ሀገር” መባሏ በጉልሕ ታውቋል፡-