Get Mystery Box with random crypto!

ያስጥለው ነበር፡፡ “እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር ከመንጋውም | ውዳሴ ማርያም/wdasemaryam

ያስጥለው ነበር፡፡
“እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር ከመንጋውም ጠቦት ይወሰድ ነበር በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር ከአፉም አስጥለው ነበር በተነሳብኝም ጊዜ ጉረሮውን አንቄ እመታውና እገድለው ነበር፡፡ ይህም ፍልስጥኤማዊ ከነዚያ እንደ አንዱ ይሆናል እንግዲህ እገድለው ዘንድ ከእስራኤል ተግዳሮትን አስወግድ ዘንድ ዛሬ አልሄድምን? የሕያው አምላክ ጭፍሮችን ይገዳደር ዘንድ ይህ ቆላፍ ምንድን ነው? ከአንበሳና ከድብ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል” አለ 1ሳሙ.17፥34፡፡
ዛሬስ ቢሆን በእስራኤል ዘነፍስ በምዕመናን ላይ የሚገዳደሩ ብዙ ፍልስኤማውያን ተሰልፈዋል እነዚህን ድል የሚነሣ በጎቹን ምዕመናን ከተኩላ ከአንበሳና፣ ከድብ አፍ የሚታደግ ታማኝ አገልጋይ ማነው ከምእመናን ተግዳሮት የሚያርቅ ፈጣሪዬ ከመከራ ያድነኛል ብሎ የሚታመን የኢአማንያን ብዛት የማያስፈራው ማን ነው? ከትንሽነቱ እስከ ታላቅነቱ የታመነ አገልጋይ ማነው? ለተሾመበት ሓላፊነት ታማኝ ማነው? አሁንም ዓለማችን ከሥጋውያን ባለ ሥልጣናትም ሆነ ከመንፈሳዊያን መሪዎች የምትሻው ታማኝ ሰው ነው በሙስና ያልተዘፈቀ ጉቦ አይኑን ያላጨለመበት ለመንጋው አርአያና ምሳሌ የሚሆን ሰው ታማኝ አገልጋይ ማለት ያ ነው፡፡ በመኀላ የተቀበለውን የአገልግሎት ሓላፊነት የማይዘነጋ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ መምህር፣ ሐኪም፣ ዳኛ፣ ነጋዴ፣ ተማሪ፣ ወታደር፣ የቤት ሠራተኛ፣ የቢሮ ሠራተኛ ታማኝ መሆን አለበት፡፡
መንጋው በክህደት ሲጠፋ ዝም ብሎ የሚያይ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ መምህር፣ ሰባኪ፣ ታማኝ አይደለም ታማሚው እየተሰቃየ የሚዝናና ቆይ ሻይ ልጠጣና የሚል ሐኪም ታማኝ አይደለም፡፡ ፍርድ የሚያጎድል ድሆችን የሚበድል ለደሃ አደጎች የማይፈርድ ዳኛ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡
ቅቤ በሙዝ እና በድንች ቀላቅሎ በርበሬ በገል ጨምሮ ሌሎችን አጭበርብሮ የሚሸጥ ነጋዴ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡ እየነገደ ያለው በሰው ሕይወት መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ እንደእየ አቅሙ በተሰጠው የአገልግሎት ዘርፍ ታማኝ መሆን አለበት፡፡
3. ታማኝ አገልጋይ ማን ነው? ዮሴፍ ነው፡፡
ዮሴፍ ለወንድሞቹ ምግባቸውን ተሸክሞ የእርሱ ስንቅ ቢያልቅ የወንድሞቹን ስንቅ ያልበላ በትንሽ የታመነ ሰው ነበር፡፡ ወንድሞቹ ሸጠውት በቤተ ጴጥፋራ በሚያገለግልበት ጊዜም ታማኝ ነበር፡፡ ታማኝነቱ በጲጥፋራ ቤት ጌታ አድርጎታል፡፡
“ዮሴፍ ተሸጠ አገልጋይም ሆነ እግሮቹ በእግር ብረት ስለሰሉ ሰውነቱም ከብረት አመለጠች ቃሉ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው ንጉሥ ላከ ፈታውም የሕዝብ አለቃ አድርጎ ሾመው የቤቱም ጌታ አደረገው በገንዘቡ ሁሉ ላይ ገዢ አደረገው፡፡ አለቆቹን እንደ እርሱ ይገስጽ ዘንድ ሽማግሌዎችን እንደ እርሱ ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ” መዝ.104፥17፡ በዚህ ሁኔታ የነበረው ዮሴፍ የጌታው ሚስት ሲወጣ ባቱን ሲገባ ደረቱን እያየች ዐይኗን ጣለችበት በዝሙት አይን ተመለከተችው፡፡
“የጌታውም ሚስት በዮሴፍ ላይ ዐይኗን ጣለችበት ከእኔም ጋር ተኛ አለችው እርሱም እምቢ አለ፡፡ ለጌታው ሚስቱ እንዲህ አላት እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ሁሉ ለእኔ በእጄ አስረክቦኛል፡፡ በቤቱ ያለውን ምንም የሚያውቀው የለም በዚህ ቤት ከአኔ የሚበልጥ ሰው የለም፡፡ ሚስት ስለሆንሽ ከአንቺ በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? እንዴትስ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአትን እሠራለሁ ይህን ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር” ዘፍ.39፥7፡፡
በዮሴፍ ታማኝነት የጌታው ቤት ተባርኳል፡፡ ሀብቱ በዝቷል፡፡ በታማኝነቱ በቤቱ ያለውን ሁሉ ተረክቦ ነበር የቀረበለት ፈተና ግን ከባድ ነበር፤ ይህን በታማኝነቱ ማለፍ ችሏል፡፡ ዛሬ በእየአንዳንዱ ጓዳ እንደ እሳት የሚያቃጥሉ አገልጋዮች ናቸው ያሉት ልጅ በፈላ ውኃ የሚቀቅሉ ናቸው የሚበዙት እንኳን በሁሉ ገንዘብ ለመሾም አይደለም፡፡ በጥቃቅን ዕቃዎች እንኳን የሚታመን ጠፍቷል፡፡ ዮሴፍ ግን በታማኝ አገልጋይነቱ በመጣበት መከራ ቢታሰር እንኳ ያለ ሹመት አላደረም የእስረኞች አለቃ ነበር፡፡ ከእስር ቤት ሲወጣም ግብፅን በሙሉ መርቷታል፡፡ በግብፃውያን በሙሉ ተሾሟል በጥቂቱ ታምኗልና፡፡ “በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል” እንዲል ማቴ.25፥24፡፡
ጌታውም መልካም አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለሆንህ በብዙ እሾምሀለሁ” ከነዚህ ሦስት ታማኝ አገልጋዮች ሕይወት ሁሉም የሰው ልጅ ታማኝ አገልጋይነት የሚያሰጠውን ክብርና ጸጋ ተመልክቶ በታማኝነት ማገልገል ይገባዋል፡፡ ታማኝ መሆን መጀመሪያ የሚጠቅመው ለራስ ነው ከዚያ በኋላ ለሀገር ለወገን ለቤተ ክርስቲያን ላመኑት ላላመኑት ሁሉ ይጠቅማል፡፡ በመጨረሻም የጽድቅ አክሊልን ያቀዳጃል መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳል፡፡ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ያስከብራል፡፡
ጻድቃን ሠማዕታት ቅዱሳን በታማኝ አገልግሎታቸው ፈጣሪያቸውን ደስ አሰኝተው ከብረዋል፡፡ በሓላፊው ገንዘብ ያልታመኑት ይሁዳ፣ ሐናንያ፣ ሰጲራ፣ የደረሰባቸውን ጉዳት አይተናል፡፡ በአካን ወልደ ከርሚንም ተመሳሳይ ቅጣት ደርሶበታል ሐዋ.5፥1፣ 1፥25፡፡
ለዚህ ነበር ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ አድነኝ ደግ ሰው አልቋልና ከሰው ልጆችም መተማመን ጎድሏልና” መዝ.11፥1፡፡ ስለዚህ ሁሉም በአለበት ያአገልግሎት መስክ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ “አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሀለሁ” የሚለውን የጌታውን የምስጋና ቃል መስማት ይገባዋል፡፡
ታአማኝ አገልጋይ ሁነን እንድንገኝ እግዚአብሔር ይረርዳን
ለዚች ቀን ያደረሰን አምላክ የትንሳኤውንም ብርሀን ያሳየን አሜን፤፤