Get Mystery Box with random crypto!

+ ገብር ኄር ++ እንኩዋን ለአብይ ፆም 6ተኛ ሳምንት ገብረ ሄር በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ | ውዳሴ ማርያም/wdasemaryam

+ ገብር ኄር ++
እንኩዋን ለአብይ ፆም 6ተኛ ሳምንት
ገብረ ሄር በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ
“መኑ ውእቱ ገብር ኄር” “ታማኝ አገልጋይ ማነው”? ማቴ.24፥45

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስያሜ የዐቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ ወይም ሳምንት ገብር ኄር ይባላል፡፡ ሰያሜውን የሰጠውም ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ጾመ ድጓ በተባለው ከአምስቱ መጻሕፍቶቹ አንዱ በሆነው ጾመ ድጓ መጽሐፍ ሳምንቱን የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜዎች ከነሥርዓተ ማኅሌቱ አዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህ በስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ከዋዜማው ቅዳሜ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን፡- የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት ገብርኄርን የሚያወሳ ነው፡፡ በማቴ.25፥14-25 የተገለጸውና በዕለቱ የሚነበበው ወንጌልም የሚነግረን ይህን ነው፡፡
“አንድ ባዕለ ጸጋ ሰው ባሪያዎችን ጠርቶ ለአንዱ አምስት መክሊት ሰጠው፣ ሁለት መክሊት የሰጠውም አለ፣ አንድ መክሊትም የሰጠው አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደሩቅ አገር ሄደ፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት አትርፎ አስር አደረገ፡፡ ሁለት የተቀበለውም አትርፎ አራት አደረገ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ መሬቱን ቆፍሮ በሻሽ ጠቅልሎ የጌታውን መክሊት ቀበራት፡፡
ከብዙ ጊዜ በኋላ ጌታቸው መጥቶ ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ አምስት አተረፍኩ አለው፡፡ “ገብርኄር ወምዕመን ዘበሁድ ምዕምነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እሰይመከ ባዕ ውስተ ፍስሐሁ ለእግዚእከ” “አንተ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው፡፡ ሁለት የተቀበለውም ቀርቦ ጌታዬ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ ወጥቼ ወርጄ ሌላ ሁለት አትርፌ አራት አድርጌአለሁ፡፡ “አንተ ታማኝ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው፡፡
አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ቀርቦ “ጌታዬ አንተ ክፉና ጨካኝ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበት የምትሰበስብ እንደሆንክ ስለአወቅሁ መሬቱን ቆፍሬ ቀበርኋት እነኋት መክሊትህ” አለው፡፡ “አንተ ሰነፍ ባሪያ መክሊቴን በጊዜ ልትሰጠኝ በተገባህ ነበር እኔም ወጥቶ ወርዶ ለሚያተርፍ በሰጠሁት ነበር”፡፡
ንዑ የዚህን ሀኬተኛ መክሊት ውሰዱና አስር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ይሰጡታል ይጨመርለታል ለሌለው ግን ያለውን ይቀሙታል፡፡ ንዑ ይህን ሰነፍና ሃኬተኛ ባሪያ እጅ እግሩን አሥራችሁ ጽኑዕ ጨለማ ወደአለበት ውሰዱት ጩኸትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨምሩት” አለ ማቴ.25፥14-25፡፡
ባዕለ ጸጋ የተባለው ጌታ ነው፡፡ መክሊት የተባለው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ ነው፡፡ ያተረፉት በሚገባ በታማኝነት ያገለገሉ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው መክሊቱን የቀበረው ደግሞ በታማኝነት በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ሲገባው ያላገለገለ ነው፡፡ ጌታቸው ሊቆጣጠራቸው መጣ ማለት በዕለተ ምጽአት ለሁሉም በአገለገለው አገልግሎት ዋጋ ለመስጠት እንደሚመጣ ያሳየናል፡፡
ያገለገሉትን ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አላቸው ማለት ታማኝ አገልጋዮች መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉና፡፡ ሰነፎች ደግሞ ጥርስ ማፋጨት ስቃይ ጽኑዕ ጨለማ ባለበት ሲዖል መግባታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
ከላይ ያነሳነው የቅዱስ ወንጌል ቃል፡- “ታማኝ አገልጋይ ማነው”? ይህ እያንዳንዱ በአርዓያ እግዚአብሔር የተፈጠረ የሰው ልጅ ጥያቄ ነው የዚህን አምላካዊ ጥያቄ መልስ መስጠት ከሰው ልጆች ይጠበቃል፡፡
1. ታማኝ አገልጋይ ማነው? ሙሴ ነው፡፡
ሙሴ ታማኝ አገልጋይ ነበር ታማኝ አገልጋይ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሠክራሉ፡፡ “በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ ወይም በህልም አናግረዋለሁ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው” ዘኁ.12፥6፡፡ ይህ የፍጡር ምስክርነት ሳይሆን በፈጣሪው የተሰጠ ምስክርነት ነው፡፡ በዕውኑ በዘመናችን እንኳን ፈጣሪ ፍጡራን ታማኝነቱን የሚመሰክሩለት አጋልጋይ ይኖር ይሆን? እንጃ የሙሴን ታማኝ አገልጋይነት በረሃ፣ ስደት፣ መከራ፣ የፈርዖን ግርማ እና ቁጣ ያልበገረው አርባ ዓመት ስለ ወንድሞቹ በመሰደድ አርባ ዓመት ደግሞ የተሰደደላቸው ወንድሞቹን በመምራት ባሕር በመክፈል፣ ጠላት በመግደል፣ መና በማውረድ ደመና በመጋረድ ውኃ ከዓለት አፍልቆ በማጠጣት መከራውን ከወገኖቹ ጋር በመቀበል የቀኑ ሀሩር የሌሊቱን ቁር/ ብርድ/ ታግሶ በታማኝነት አገልግሏል፡፡ ታማኝነቱ እስከሞት ነበር፡፡
“ሙሴም ወደ እግዚብሔር ተመልሶ ወዮ እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኀጢአት ሠርተዋል፡፡ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አሁን ይህን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ ከባለሟልነትህ አውጣኝ /ዘጸ.32፥31፡፡ አያችሁ ታማኝ አገልጋይ እኔ ልሙት ሌሎች ይዳኑ የሚል ነው አሁን የምናየው ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሰዎች ይሙቱ እኔ ልኑር ሰዎች ጦም ይደሩ እኔ ልብላ ሰዎች ይራቆቱ እኔ ልልበስ ሰዎች ይዘኑ እኔ ልደሰት ነው፡፡ ይህ ታማኝ አገልጋይ ያለመሆን መገለጫ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ለሚያገለግላቸው ሰዎች ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ እንጂ የራሱን ጥቅም የሚያስቀድም አይደለም፡፡ ዛሬ በዓለማችን የምንመለከተው ግን “ጩኸት ለአሞራ መብል ለጅግራ” የሚባለውን መሰል ነው፡፡ በታማኝ አገልጋዮች ድካም የሚሸለሙ ታማኝ አገልጋዮች በሠሩት ሪፖርት የሚያቀርቡ፣ የሚወደሱ ከጥቅሙ እንጂ ከድካሙ መክፈል የማይሹ እንቅፋት የሚመታው እግርን ነው፡፡ አክሊል የሚቀዳጀው ግን ራስ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ማለት እንደራስ አክሊል ዘውድ የሚጸፋ ብቻ ሳይሆን እንደ እግር እንቅፋቱን፣ እሾሁን፣ መከራውን ውጣ ውረዱን ድካሙን የሚቀበል ነው፡፡ በጥቅም ጊዜ ለራሱ በአካፋ የሚዝቅ ሌሎች በጭልፋ የሚቆነጥር አይደለም፡፡ ሙሴ ባሕር የከፈለው መና ያወረደው ደመና የጋረደው ውኃ ያፈለቀው ለራሱ አልነበረም ለሚመራቸው ሕዝብ ነበር እንጂ፡፡ ታማኝ አገልጋይ ያሰኘውም ይኸው ነው፡፡ በዚህ ከብሮበታል ተመስግኖበታልም፡፡
2. ታማኝ አገልጋይ ማነው? ዳዊት ነው፡፡
ዳዊት ዘመነ መሳፍንት አልፎ ዘመነ ነገሥት ሲተካ እስራኤልን በንጉሥነት እንዲያገለግል እግዚአብሔር ከበግ ጥበቃ መርጦ በተሰጠው ሥልጣን ያልተመነ የሳዖልን በትረ መንግሥት በሳሙኤል እጅ ተቀብቶ ተቀብሏል፡፡
በተሰጠው ሥልጣን በታማኝነት ሕዝበ እስራኤልን መርቷል፡፡ ታማኝነቱንም እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ መሰከረለት ለእርሱም መስክሮለታል፡፡
“እግዚአብሔር እንደልቡ የሆነ ሰው መርጧልና” የዘይቱን ቀንድ ሞልተህ በልጆቹ መካከል ለእኔ ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተልሔም እልክሃለሁ” 1ሳሙ.13፥13፣ 16፥2፡፡
“ወረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ወቀባዕክዎ ቅብዐ ቅዱስ” እንዲል መዝ.88፥20፡፡ “ባሪያዬ ዳዊትን አገኘሁት የተቀደሰ ዘይትንም ቀባሁት” ይህን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሰዓታት በተባለው ድርሰቱ፡- “ረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ብዕሴ ምዕመነ ዘከመልብየ” አገልጋዬ ዳዊትን እንደ ልቤ የታመነ ሰውን ሆኖ አገኘሁት ሲል ተርጉሞታል፡፡ የተገኘው በታማኝነት ነበር ከነገሠ በኋላም ታማኝ ነበር አሁን በዚህ ዓለም የምንኖር እኛ ግን በድኅነት ታማኝ እንሆንና ሀብት ሹመት ሥልጣን ሲመጣ ታማኝነትን እናጣለን፤ እንዲያውም ታማኝነትን እንንቀዋለን፡፡ መስረቅ ጀግንነት ይመስለናል፡፡ መዋሸት ሥልጣኔ ይሆንልናል፡፡ ዳዊት ሳይሾም በጎቹን በመጠበቅ ታማኝ ነበር፡፡ በጎቹን የሚነጥቅ ተኩላ አንበሳ ቢመጣ በኋላው ተከትሎ ነብሩን በጡጫ አንበሳውን በእርግጫ ብሎ በጎቹን