Get Mystery Box with random crypto!

የዓለም ባንክ ሃገራት ቢያንስ የ15 ከመቶ የግብር ገቢ ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት (GDP) ምጣኔ ቢኖ | The Ethiopian Economist View

የዓለም ባንክ ሃገራት ቢያንስ የ15 ከመቶ የግብር ገቢ ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት (GDP) ምጣኔ ቢኖራቸው ጥሩ ነው ይላል!


ግብር ከጠቅላላው ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ በዓመት ውስጥ የሚሰበሰብ የግብር መጠን በዓመት ውስጥ ለሚመዘገበው ጠቅላላ ኢኮኖሚ ምርት መጠን (GDP) በማካፈል የሚገኝ ስሌት ነው፡፡


#ለምሳሌ:- በኢትዮጲያ በ2016 ዓ/ም 440 ቢሊየን ብር ከግብር ቢሰበሰብ እና ለጠቅላላ ሃገራዊ ምርት 7 ትሪሊየን ብር ቢካፈል (ማለትም 130 ቢሊየን ዶላር* በ54ብር ምንዛሬ ተባዝቶ 7 ትሪሊየን ብር ቢመጣ) ግብር ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት (GDP) 6.2 ከመቶ ሊመጣ ይችላል (በ2016 ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ 520 ቢሊየን ብር ተገማች ገቢ ውስጥ 440 ቢሊየን ብሩ ማለትም 84.6 ከመቶውን ከግብር ነው!)፡፡


#ለምሳሌ፡- የአውሮፓ ሃገራት ከፍተኛ የግብር ከጠቅላላ ኢኮኖሚ ምጣኔ አላቸው (ሲዊድን (42 ከመቶ)፤ ዴንማርክ (35 ከመቶ)፤ ፈረንሳይ 45 ከመቶ፤ ወዘተ የደረሰ ሽፋን ሲይዙ)፤ አሜሪካ (26 ከመቶ)፤ ቻይና (4.6 ከመቶ (የትልልቅ ተቋማት ባለቤት መንግስት ከመሆኑ ጋር ሊገናኝ ይችላል)፤ ህንድ (11 ከመቶ)፤ ግብጽ እና ኬኒያ (13 ከመቶ)፤ ናይጄሪያ (10.8 ከመቶ)፤ ወዘተ፡፡


ግብር ብቸኛ የኢኮኖሚ የገቢ ዋስትና ላይሆን ይችላል! በዓለም ላይ 14 ሀገራት ምንም የገቢ ግብር ከኢኮኖሚው የማይሰበስቡ ሲሆን ከነሱ ውስጥም የተባበሩት አረብ ኢሚሬት፤ ባህማስ፤ ሶማሊያ፤ ባህሬን፤ ኪዌት፤ ኳታር፤ ወዘተ፡፡ ምክንያታቸው የተለያየ ቢሆንም ገቢን ከሌሎች ሴክተሮች ለመሰብሰብ፤ በግብር ቅነሳ አምራች እና ሸማች ክፍሉ ከጫና ተላቆ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ፤ ሀገራቸውን ለዜጎቻቸው መኖሪያነት ምቹ ለማድረግ፤ የውጪ ኢንቨስትመንት ወደ ሃገራቸው ለመሳብ፤ ወዘተ ሲሉ ነው፡፡


የስትራቴጂ ትግሉ፡- ከአምራች ክፍሉ ግብርን በመቀነስ የካፒታል እጥረት ሳይገጥመው በመንቀሳቀስ ከፍተኛ የስራ እድል እንዲፈጥር እና ከፍተኛ ምርት እንዲያመርት መፍቀድ በሚለው እና ከሚጣል ከፍተኛ ግብር የሚገኘውን ገቢ ለኢኮኖሚው የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን እና ድጎማዎችን ለማቅረብ ማሰብ መካከል ነው፡፡


ነገር ግን እንደ ኢትዮጲያ ከግብር ማዕቀፍ ውጪ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተሳታፊዎችን በማስቀመጥ እና የግብር አሰባሰብ ህግ እና አሰራር ደካማ በመሆኑ የሚነሳ ግብር ከጠቅላላው ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ ማነስ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተቋማት ድክመት እንጂ እና ስትራቴጂ መሆን አይችልም፡፡