Get Mystery Box with random crypto!

#ብዝሃ_ዋና_ከተሞች! በቀላሉ አዲስ አበባ እና የክልል ከተሞች እንዲሁም አዲስ አበባ እና በዙ | The Ethiopian Economist View

#ብዝሃ_ዋና_ከተሞች!

በቀላሉ አዲስ አበባ እና የክልል ከተሞች እንዲሁም አዲስ አበባ እና በዙሪያዋ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚኖሩ መንደሮች፤ የክልል ዋና ከተሞች እና ሌሎች የዞን ከተሞች መካከል ያለውን የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ልዩነት ተመልከቱ!

ኢትዮጲያ ለአዲስ አበባ አቻ ተቀራራቢ #ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ያለው ከተማ የላትም! ኦሮሚያ ውስጥ የአዳማ አቻ ከተማ ለማግኘት ከባድ ነው፤ ባህርዳር ከተማ ላይ ለመድረስ የክልሉ ከተሞች ገና ብዙ ይቀራቸዋል፤ ድሬዳዋ እና ሀረርም አይቀራረቡም፤ ደቡብ ክልል ከተሞች በጥቂቱ ነው ነባሪያዊ የእድገት ቅርርብ ያላቸው፤ በትግራይ ክልል ከተሞች የመቀሌን ያህል አይደሉም፤ አፋርም ሶማሌም ከክልል መቀመጫ ከተሞቹ ውጪ ያሉ ከተሞቻቸው የተፎካካሪነት አቅማቸው ገና ነው (በተለያየ አጋጣሚ አብዛኛዎቹን ክልል እና ከተሞች የመመልከት እድል ነበረኝ)፡

የወረዳ ነዋሪ ወደ ዞን፤ የዞን ነዋሪ ወደ ክልል መቀመጫ፤ የክፍለ ሀገር ነዋሪ ወደ አዲስ አበባ ለመዘዋወር ከሚቀመጡ መሰረታዊ ምክንያቶች መካከል አንዱ ከተሞች ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድሎቻቸው የተራራቀ በመሆኑ ነው፡፡

የሀገራት ኢኮኖሚ በተለይ በታዳጊ ሀገራት ሁለት መልክ አለው (Dual Economy)! አንደኛው ገጠሩ (Traditional Sector)፤ በግብርና ዘርፍ የሚተዳደረው፤ ደካማ የተቋማት እና የቴክኖሎጂ ለውጥ የሌለው ሲሆን ሁለተኛው ከተሜው (Modern Sector)፤ ኢንዱስትሪ መዳረሻ ያለበት እና የቴክኖሎጂ እገዛ ተጋሪ የሆነው ማለት ነው፡፡ የኢኮኖሚ እድገት በፍጥነት መሄድ ካስፈለገው የገጠሩ ክፍለ ኢኮኖሚ ከምርታማነት ሳይቀንስ ከተሜነትን በማስፋፋት እድገትን ማስቀጠል ይገባል/ይቻላል፡፡

ከተሜነት በተወሰኑ ቦታዎች በሚስፋፉበት ወቅት የገጠሩ የሰው ሃይል ወደ ከተሞች ሲፈልስ በአብዛኛው በጉልበት ስራ ላይ ስለሚሰማሩ ኢኮኖሚው በፈጠራ ከመሞላት ይልቅ ነዋሪዎች የከተሞችን ማህበራዊ አገልግሎት ወደ ማጣበብ/መሻማት ይሄዳሉ፡፡

በሀገራችን የትልልቅ ከተሞች አሁናዊ ሁኔታ ከዚህ ሃሳብ የተለየ አይደለም! ገጠሩ ክፍለ ኢኮኖሚ የመሬት ባለቤትነት፤ የመሰረተ ልማት አቅርቦት፤ የምርታማነት መቀነስ፤ የሰዎች ጉልበት መባከን (የመሬት መጠን ማነስ ብዙ የቤተሰብ አባላት አነስተኛ መሬት ላይ እንዲሰሩ ስለሚያደርግ ከአቅም በታች መስራት መገለጫው ነው)፡፡

#ለምሳሌ፦ አንድ አባወራ ከቤተሰቡ 1 ሄክታር ወርሶ ይኖር ከነበረ እና በሂደት 8 ልጆች ወልዶ እድሜያቸው በደረሱ ቁጥር ከመሬቱ እየቀነሰ ቢሰጥ አልያም ብቻውን ያርሰው የነበረ መሬት ከልጆቹ ጋር 9 ሆነው ቢያርሱት የ8ቱ ሰዎቹ ጉልበት በማሳው ላይ ሚናው (Marginal effect) ዜሮ ነው! ስለዚህ ልጆቹ ስራ ፍለጋ ወደ ከተሞች/ኢንዱስትሪ አካባቢዎች መጓዛቸው አይቀርም (የገጠሩ ነዋሪ በአብዛኛው ለከፍተኛ ትምህርት ሩቅ በመሆኑ ከተሜው ለገጠሬው የሚያቀርበው ስራ የጉልበት ስራ/ የቤት ሰራተኝነት የመሆን እድሉ ሰፊ ነው)፡፡

የተመጣጠነ የኢኮኖሚ እድገት መንገዶችን በገጠር እና ከተማ ለመፍጠር የመቶ ዓመታት ጊዜ ሊወስድም ይችላል! አንዳንድ ሀገራት በኢኮኖሚ ሚናቸው የፈረጠሙ ከተሞችን በመፍጠር ኢኮኖሚያቸው ወጥ እንዲሆን ማድረግ እየቻሉ ነው። #ለምሳሌ፦ 3 ዓመት በሞላው አንድ ጥናት ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ክልሎች በሙሉ 50% GDP ድርሻ የላቸውም።

በከተሞች እና ገጠር መካከል ያለው የተለያየ የኢኮኖሚ እድገት ሁኔታ ገጠሩን በሴክተር ተዋፅዎ ወደ ከተሜነት በማሳደግ፤ የምርታማነት ደረጃን የሚያሻሽሉ ስራዎችን በመስራት፤ የሃብት ክፍፍልን ጤናማ በማድረግ፤ ወዘተ ዘላቂ ሁኔታው የተስተካከል እንዲሆን የፖሊሲ እገዛ ያስፈልገዋል፡፡

ትምህርት ለሁሉም በሚለው ፖሊሲ የአርሶ አደሩ ልጆች እንዲማሩ ጥረት ሲደረግ በመርህ ደረጃ የሚያገኙትን ከፍተኛ ትምህርት በመጠቀም አዳዲስ አሰራሮች እና ግብዓቶችን በመጠቀም በቤተሰቦቻቸው ማሳ ላይ ምርታማነት ደረጃዎችን ያሳድጋሉ የሚል ነው (ምክንያቱም የግሉም የመንግስትም ሴክተር በቋሚነት ቀጥሮ የሚጨርሰው ሃይል ስለማይሆን፣ የሀብት መሰረት የሆነው መሬት ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ግድ ነው፡፡

ነገር ግን በዋናነት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ የአርሶ አደሩ ልጆች ዘመናዊ የትምህርት ማስረጃ ይዘው ግብርናው ላይ ከሚሳተፉ የወረዳ፤ ዞን፤ ክልል እና ፌደራል ከተሞች ላይ ዝቅተኛ ደሞዝ እያገኙ ተቀጥረው ለመስራት ከገጠር ወደ ከተማ ስደትን ይመርጣሉ (ይህ ጉዳይ በአጭሩ የሚቆም አይደለም!)፡፡ ስለዚህ የገጠር ክፍለ ኢኮኖሚው የሚታይበት መነጽር እና የከተሜነት መስፋፋት ስትራቴጂ የተናበበ አንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ለከተሞች ማደግ ከሚነረዱ መንገዶች አንዱ የመንግስት አስተዳደር መቀመጫ መሆን እና የመሰረተ ልማት መስፋፋት በመሆኑ የመንግስት መቀመጫዎችን የነዋሪን እንግልት በማይፈጥር መልኩ የተለያዩ ከተሞች ላይ በማድረግ ተመጣጣኝ እንዲሆኑ እና አንዱ ከተማ በሌሎች ከተሞች ጫና ሳይፈጠርበት እንዲኖር በማድረግ የተሻለ ፖለቲካል እና ኢኮኖሚካል ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡