Get Mystery Box with random crypto!

የጂቡቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ሸገር ከተማ ገባ ሰኔ 27/2015(ዋልታ) በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር | AddisWalta - AW

የጂቡቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ሸገር ከተማ ገባ

ሰኔ 27/2015(ዋልታ) በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የተጓዘው የጂቡቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ሸገር ከተማ ገብቷል።

በጅቡቲ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ዴኤታ ሲራጅ ዑመር የተመራው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ሸገር ከተማ በሚገኘው ፉሪ-ለቡ የባቡር ጣቢያ ሲደርስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል።

የጅቡቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ በባቡር ተጉዞ ነው ወደ ኢትዮጵያ የገባው።

ጉብኝቱ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ መስክ የኢትዮ-ጅቡቲ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ይበልጥ ለማጠናከር ታሳቢ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል።

የልዑክ ቡድኑ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ሲሆን 112 አባላትን ያካተተ መሆኑም ተጠቅሷል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ አባላት በፉሪ ለቡ ባቡር ጣቢያ ውስጥ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ወንድማማችነት ማጠናከርን ዓላማ ያደረገ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አካሂደዋል።

የቡድኑ አባላት በትላንትናው እለት በድሬዳዋ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ላይ የተሳተፉ ሲሆን አሮጌውን የኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡርን ጨምሮ ሌሎች ስፍራዎችን ጎብኝተዋል።

ዛሬም ወደ ፉሪ-ለቡ የባቡር ጠቢያ ከመምጣታቸው አስቀደሞ በአዳማ ከተማ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።

የቡድኑ አባላት በነገው ዕለት በአዲስ አበባ የተለያዩ የህዝብ ለህዝብ ዝግጅቶች ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡