Get Mystery Box with random crypto!

በቻይና በተካሄደ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል ቀናቸው ሰኔ 5/2015 (ዋልታ) | AddisWalta - AW

በቻይና በተካሄደ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል ቀናቸው

ሰኔ 5/2015 (ዋልታ) በቻይና የላንዡ ከተማ በተካሄደ የወንዶች ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ተከታትለው በመግባት አሸነፉ።

በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የዓለም አገራት በተደረጉ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል።

ከእነዚህ የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል በ2023 የላንዡ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ በበላይነት የጨረሱ ሲሆን በተለይ በወንዶች መካከል በተደረገው ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 7ኛ ተከታትለው በመግባት ማሸነፍ ችለዋል።

በውድድሩ አትሌት ኃይለማርያም ኪሮስ በአንደኝነት ያጠናቀቀ ሲሆን አፈወርቅ መስፍን፣ ሃይማኖት አለው፣ ሃይሌ ለሚ፣ አባይነህ ደጉ፣ ዮሐንስ መካሻ፣ ዱበር አብዲሻ እንደየቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በሴቶች ደግሞ አትሌት ለተብርሃን ሃይላይ በአንደኝነት ስታጠናቅቅ አትሌት ታደለች በቀለ ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች።

በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ የማራቶን ውድድር የተካሄደ ሲሆን በሴቶች አትሌት ዝናሽ ደበበ በአንደኝነት ማጠናቀቋ ተመላክቷል።

በኔዘርላንድ በተካሄደ ግማሽ ማራቶን ውድድር ንግስቲ ሃፍቱ በአንደኝነት ስትጨርስ በዚህ ውድድር በወንዶቹ አትሌት ሃፍቱ ተክሉና አሸናፊ ኪሮስ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በአሜሪካ ኒዮርክ በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ የቦታውን ሰዓት በማሻሻል ጭምር አሸንፋለች።

በፈረንሳይ በተካሄደ 5 ሺሕ ሜትር ውድድር ደግሞ አትሌት መዲና ኢሳ የቦታውን ክብረ ወሰን ሰዓት በማሻሻል ጭምር ማሸነፉ ተገልጿል።