2022-06-14 16:50:58
[በሰኔ 8 የጌታችን በምድረ ግብጽ ውሃን ማፍለቅ]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
ሰብአ ሰገልም ጌታን ከእናቱ ጋር አይተው ወድቀው በመስገድ እጅ መንሻውን አቅርበውለት ከሄዱ በኋላ መልአኩ ለዮሴፍ በሕልሙ ተገልጾ “ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘኽ ወደ ግብጽ ሽሽ እስክነግርኽም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” ባለው ጊዜ ቅዱስ ዮሴፍ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ኼዷል፤ ይኽ የቅዱስ ገብርኤል መልእክት የሚያስረዳን እኛም ልክ እንደ አረጋዊዉ ቅዱስ ዮሴፍ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን በኑሯችን ኹሉ በልቡናችን በአንድነት ይዘን እንድንጓዝ ነው (ማቴ 2:1--11)፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈሰ እግዚአብሔር እየተቃኘ ቅድስት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ዐማኑኤልን ይዛ ወደ ግብጽ የመሰደዷን ነገር አስቀድሞ ተገልጾለት በምዕ ፲፱፥፩ ላይ፡-
"እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ" በማለት ከገነት የተሰደድነውን እኛን ወደ ቀደመ ርስታችን ሊመልሰን እንደመጣ ለማጠየቅ።
ጠላታችን ዲያብሎስን ከሰዎች ልብ አውጥቶ ለመስደድ፤ ክብር ይግባውና ወልደ እግዚአብሔር ልመናዋ ፈጥኖ በሚሰማላት "ደመና መፍጠኒት" በተባለች በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ ወደ ግብጽ የመሰደዱን ነገር አስቀድሞ ገልጾታል፡፡
ይኸውም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈ ንጉሡ ሄሮድስ ክርስቶስን ለመግደል በፈለገ ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል ለአረጋዊዉ ለዮሴፍ በሕልሙ ተገልጾለት "ተንሥእ ወንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወጒየይ ውስተ ብሔረ ግብጽ" (ሕፃኑንና እናቱን ይዘኽ ወደ ግብጽ ሽሽ) ባለው ጊዜ ይኽ ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ሊፈጸም ምልጃዋ ፈጥኖ በሚደርስ "ደመና መፍጠኒት" በተባለች በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ ወደ ግብጽ በኼደ ጊዜ የግብጽ ጣዖታት ኹሉ እየተሰባበሩ ሲወድቁ፤ በነርሱ ዐድረው ያስቱ የነበሩ አጋንንት ኹሉ ሸሽተዋል፤ በመኾኑም በዚኽ የነገረ ማርያም አስተምህሮ እመቤታችን "ደመና መፍጠኒት" ወይም "ደመና ኢሳይያስ" ተብላ ተጠርታለች፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በስደቷ ወቅት ልጇን እንዳይገድሉባት በረሓ በረሓውን እንኺድ ስትል ዮሴፍና ሰሎሜ ለልመና እንዲመቻቸው ከተማ ከተማውን መኼድ ፈለጉ ያን ጊዜ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ተገልጸው ዮሴፍን “እመቤትኽ አይደለች ያለችኽን አትሰማም” ብለውታል።
ጌታም “ኢትትናገራ ለእምየ” (በኾነ ባልኾነው እናቴን አትናገራት!) ብሎታል፤ ወዲያው ከከተማ አጠገብ ስትደርስ ዮሴፍና ሰሎሜን ጓዝ አስጠብቃ ርሷ ጌታን ዐዝላ እኽል ውሃ ለመጠየቅ ከተማ ብትገባ ሰይጣን በሰዎቹ ልብ በማደር የሰውን ልቡና ኹሉ አጽንቶባት የሚዘከራት አጥታ በሐዘን ተመልሳለች፡፡
ሊቁም ስለዚኽ ነገር የስደቷን ነገር በሚያነሣው በሰቈቃወ ድንግል መጽሐፉ ላይ በሐዘን ኾኖ፡-
“ተንሥዒ ወንዒ ሌዋዊት ሐና
ትጼውዓኪ ወለትኪ ከመ ትርአዪ ሐዘና
እምርስትኪ ወጽአት ወተሰደት በድክትምና
ትበኪ እምዋዕየ ሐጋይ ኃጢኣ በፍና
ሕፍነ ማይ ዘታሰትዮ ለጽሙዕ ሕጻና”
(ከሌዊ ወገን የኾንሽ ሐና! ልጅሽ ከቦታሽ ወጥታ በድኅነት ተሰድዳ ከበጋ ሙቀት የተነሣ ለተጠማ ልጇ የምታጠጣው ዕፍኝ ውሃን በመንገድ ዐጥታ ታለቅሳለችና ዐዘኗን ታይላት ዘንድ ልጅሽ ትጠራሻለችና ፈጥነሽ ነዪ) በማለት ገልጾታል፡፡
ከዚያም ዮሴፍና ሰሎሜ ወዳሉበት ብትመለስ አረጋዊ ዮሴፍና ሰሎሜ በመንገድ ስለደከሙ እንቅልፍ ወስዷቸው ሰብአ ሰገል የገበሩለትን የወርቅ ጫማ ለሌቦች አስወስደው ቆይዋት፤ ርሷም “ከተማ ቢገቡ ልጅ የሚሸነግሉበት ትንሽ ቊራሽ ጥሩ ውሃ ማጣት እዚኽ ቢመጡ የወርቅ ጫማ ማጥፋት” ምርር ብላ አልቅሳለች ዕንባዋም በፊቱ ወርዷል፡፡
ሊቁም ይኽነን ይዞ በሰቈወ ድንግል መጽሐፉ ላይ ፡-
“መለኮት ዕጓላ ሶበ ጸምዐ ከመ ደቂቅ
ዘይሰፍሮ በኅፍኑ ለማየ ባሕር ዕሙቅ
በከየት ወትቤ ማርያም ማዕነቅ
አልቦ እምሰብአ ሀገር ዘየአምራ ለጽድቅ
ሶበ ሰአልክዎሙ ማየ ኢወሀቡኒ በሕቅ
ወአኅጐልኩ ለወልድየ አሣዕኖ ዘወርቅ”
(ጥልቅ የኾነ የባሕር ውሃን በእጁ የሚሠፍረውና የማይመረመር መለኮት የተባለ የባሕርይ አምላክ ልጇ በተጠማ ጊዜ ከዚች ሀገር ሰዎች ቸርነትን የሚያውቃት የለም፤ ውሃን በእጅጉ ለመንኋቸው አልሰጡኝም የልጄ የወርቅ ጫማውን አስጠፋኊ እያለች ዋኖስ ማርያም አለቀሰች) በማለት መሪር ዕንባዋን ጽፏል፡፡
ልጇም ዕንባዋን አይቶ ሰኔ 8 ቀን ከማር ከወተት ይልቅ የምትጣፍጥ ውሃ አፍልቆ አጠጥቷቸዋል፤ በዚኽም ውሃ የተጠመቀውን ከሕመሙ እንዲፈወስ ቃል ኪዳን ሲሰጣት፤ ሰይጣን ልቡናቸውን ላጸናባቸው ለዚያች ሀገር ሰዎች ግን መሪር እንደምትኾንባቸው ነግሯታል፡፡ ይኽችም ደገኛ ተአምር የተሠራችባት ሰኔ 8 ከቅድስት ድንግል ማርያም 33ቱ በዓላቷ እንዳንዱ በመቈጠር በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዓለም እስኪያልፍ ድረስ ትታሰባለች፡፡
ሊቁም በሰቈቃወ ድንግል ይኽነን ይዞ፡-
“ሰሚኦ ሕፃን ለእሙ ገዐራ
ባረከ ኰኲሐ ወአንቅዐ ማየ እምታሕተ እግራ
ወእምኔሁ ለጽምዐ ትስተይ አመራ
ከመ ኢይስተይዋ እምሰብአ ሀገር ለይእቲ ማይ አምረራ
ወለርኁቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ”
(የእናቱን ጭንቅ ልጇ ሰምቶ ዐለቱን ባርኮ ውሃን ከእግሯ በታች አፈለቀ፤ ከዚኹም ውሃ ለጥማቷ ትጠጣ ዘንድ አመለከታት የዚች ሀገር ሰዎችም ይቺን ውሃ እንዳይጠጧት መራራ ለሩቅ ሰዎች ግን የጣፈጠች የፈውስ ውሃ አደረጋት) በማለት የጌታን ተአምር መስክሯል፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስም ይኽነን ታሪክ ይዞ በሰዓታቱ ላይ
“ወጽአት በፍርሃት እምሀገረ ዳዊት ዘይሁዳ
በብሥራተ መልአክ እንግዳ
ኢረከበት ማየ በፍኖት ዘታሰትዮ ለወልዳ”
(በእንግዳ መልአክ ብሥራት የይሁዳ ክፍል ከምትኾን ከዳዊት ከተማ ከይሁዳ በፍርሀት በወጣች ጊዜ ለልጇ የምታጠጣው ውሃ በመንገድ አላገኘችም) በማለት ገልጾታል፡፡
ድንግል ሆይ የሕይወት ውሃ ከተባለ ልጅሽ ምሕረትን ለምኚልን፡፡ አሜን!
☞ @negeretewahido
እጅግ ታሪካዊ ወደሆነው ምሥጢራዊው መንዝ
#እመጓ_ደብረ_ቆጵሮስ_ቅዱስ_ዑራኤል_ገዳም
የሚኖረን ፫ኛው ዙር መንፈሳዊ ጉዞ እንደተጠበቀ ነው።
* መነሻ ዐርብ ሰኔ 10* መመለሻ እሑድ ሰኔ 12
* የጉዞ ዋጋ ቦታው ላይ ምግብና ማረፊያ ጨምሮ 1000 ብር
★ በማኅበራችን የጉዞ መርሐ ግብራት መሳተፍ ከፈለጉ ሳያመነቱ ይደውሉልንና አብረን እንጓዝ!!! ውስን ወንበሮች ብቻ ስለቀሩን ይህንን ቅዱስ ቦታ ለመሳለም የምትሹ ያልተመዘገባችሁ የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ልጆች ሁሉ ቀድማችሁ ደውሉልንና አብረን በረከት እናግኝ! ለበለጠ መረጃ፦
→ 0911289877
→ 0901070707
#ማኅበረ_ቅዱስ_ፊልጶስ_ወአቡነ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ
✥✞✥ ጽሑፉን ሌሎች እንዲያነቡትም Like እና Share ያድርጉ፤ በዚህ መንፈሳዊ Page ላይ የሚተላለፉ መንፈሳዊ ጦማሮች ለእርስዎም ለሌሎችም እንዲደርሱ ፔጁን Like / Follow ሌሎችንም ወደ ፔጃችን ይጋብዙ።
በቴሌግራም ይቀላቀሉን
@waldiba
@waldiba
@waldiba
የዩቲዩብ ቻናላችንን « መኮሬታ Mekoreta Tube »ን በሚከተለው ሊንክ ከፍተው Subscribe & Join ያድርጉ።
https://m.youtube.com/channel/UCUBStsekCniQtATyZDdFqQQ
2.3K viewsአንተነህ ውብሸት, edited 13:50