Get Mystery Box with random crypto!

#ለምን_ነጭ_ነጠላ_እንለብሳለን? አንዳንዶች ባለማወቅም ይሁን በቅናት «ክርስትና ነጠላ ለብሶ ቤ | ዋልድባ ገዳም

#ለምን_ነጭ_ነጠላ_እንለብሳለን?
አንዳንዶች ባለማወቅም ይሁን በቅናት «ክርስትና ነጠላ ለብሶ ቤተክርስቲያን መሄድ አይደለም!» ሲሉ ይደመጣሉ። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ግን መጽሐፍ ቅዱስን ምክንያት አድርጋ ምሥጢሩን ከተግባር ጋር ትገልጻለች። ወደ ቤተ መቅደስ ስንሄድ ነጭ መልበሳችን የተገባ ነው። ነጭ ነጠላ ጋቢ አደግድገን ወይም በትእምርተ መስቀል ለብሰን ቤተመቅደስ ስንቆም የምናስባቸው ምስጢራት አሉ።

✥ ለምን በትእምርተ መስቀል እንለብሳለን?
የክርስቶስን መከራ ለማሰብ፣ ነጠላው ወደ ግራና ቀኝ በትእምርተ መስቀል አምሳል ይጣፋል። በዚህ ጊዜ ጌታችን በዕለተ አርብ የተቀበላቸው ጸዋትወ መከራ እንዲሁም በቀራንዮ በምልዕልተ መስቀል መሰቀሉን ያስታውሰናል። ይኼንን የተመሳቀለ ነጠላ የሚመለከትም ሁሉ የጌታችንን መከራ መስቀል መቀበሉን ያስባል።

✥ የምናጣፋው ነጠላ ነጭ የሆነባቸው ምክንያቶችስ?
☞ ጌታችንን አብነት በማድረግ
☞ ቅዱሳንን አብነት በማድረግ
☞ ቅዱሳን መላእክትን አብነት በማድረግ
☞ ሰማያዊ ተስፋችንን በማሰብ
☞ @negeretewahido

✥†✥ ማስረጃ፦

፩ኛ. ጌታን አብነት በማድረግና ከጌታችን ጋር እንዳለን በማሰብ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል የምሥጢር ሐዋርያት የሚባሉትን ቅ.ጴጥሮስን፣ ቅ.ዮሐንስንና ቅ.ያዕቆብን ወደ ደብረ ታቦር ይዟቸው ወጥቶ እየተመለከቱት ተለወጠ፤ ፊቱም ማየት እንደ ፀሐይ ልብሱም አጣቢ ሊያነጣው እስከማይችል ነጭ ሆኖ ብርሃነ መለኮቱን ገልጦላቸው ነበር።

ወንጌላዊው ሐዋርያ ቅዱስ ማቴዎስ፦ “ወእምድኅረ ስሱ መዋዕል ነሥኦሙ እግዚእ ኢየሱስ ለጴጥሮስ ወለያዕቆብ ወለዮሐንስ እኁሁ ወአዕረጎሙ ውስተ ደብር ነዋኅ እንተ ባሕቲቶሙ። ወተወለጠ ራእዩ በቅድሜሆሙ ወአብርሀ ገጹ ከመ ፀሓይ ወአልባሲሁኒ ኮነ ጸዐዳ ከመ ብርሃን። - ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ (ደብረ ታቦር) ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ።” ማቴ ፲፯፥ ፩- ፪ እንዳለ።

ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስም፦ “ወአመ ሰዱስ ዕለት ነሥኦሙ እግዚእ ኢየሱስ ለጴጥሮስ ወለያዕቆብ ወለዮሐንስ ወአዕረጎሙ ደብረ ነዋኀ በባሕቲቶሙ ወተወለጠ ራእዩ በቅድሜሆሙ። ወአልባሲሁኒ በረቀ ወጻዕደወ ጥቀ ዘኢይክል መሃፔል ከማሁ አጻዕድዎቶ በዲበ ምድር። - ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ልብሱም አንጸባረቀ፤ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ።” ማር ፱፥ ፪- ፫ ብሏልና።

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስም፦ “ወእምድኅረ ዝንቱ ነገር አመ ሳምንት ነሥኦሙ እግዚእ ኢየሱስ ለጴጥሮስ ወለያዕቆብ ወለዮሐንስ ወዐርገ ደብረ ይጸሊ። ወእንዘ ይጼሊ ተወለጠ ርእየተ ገጹ ወጻዕደወ አልባሲሁኒ ወይበርቅ። - ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ።” ሉቃ ፱፥ ፳፰- ፳፱ እንዲል።

እኛም ሊያድነንና አርአያ ሆኖ ሊያስተምረን ሰዉ የሆነዉን ጌታችንን አብነት አድርገን ነጭ ነጨላን ለብሰን የደብረ ታቦር ምሳሌ ወደ ሆነችዉ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን እንሰበሰባለን።

፪ኛ. ቅዱሳንን አብነት አድርገን የቅዱሳን የቃልኪዳን ልጆች መሆናችንንና በምልጃ ቅዱሳን መጠለላችንን በማሰብ

ወንጌላዊው ሐዋርያ ቅ.ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ በራእዩ፦ “አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው።” ራእይ ፮፥ ፱- ፲፩ እንዳለ።

አንድም፦ “ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤” ራእይ ፯፥ ፱ ብሏልና

እኛም ቅዱሳኑን አብነት በማድረግና በፍርድ ቀን በበጉ ከተመሰለው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቀኝ ነጭ ለብሰን የመቆም ተስፋን በመሰነቅ ነጭ ነጠላን እንለብሳለን።

፫ኛ. ቅዱሳን መላእክትን አብነት በማድረግና ቅዱሳን መላእክት ከእኛ ጋር መሆናቸውን ማሰብ

፬ቱም ወንጌላዊያን ስለነገረ ትንሣዔው ሲገልጡ፦
ሐዋርያው ቅ.ማቴዎስ፦ “ወሰርከ ሰንበተ ለጸቢሐ እሑድ መጽአት ማርያ መግደላዊት ወካልእታኒ ማርያ ይርአያ መቃብረ። ወናሁ ኮነ ድልቅልቅ ዓቢይ እስመ መልአከ እግዚአብሔር ወረደ እምሰማይ ወቀርበ ወአንኰርኰራ ለእብን ወነበረ ዲቤሃ። ወራእዩ ከመ ዘመብረቅ ወልብሱ ጻዕዳ ከመ ዘበረድ። - በሰንበትም መጨረሻ መጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ።” ማቴ ፳፰፥ ፩- ፫

ወንጌላዊው ቅ.ማርቆስ፦ “ወረዊጾን ርእያሃ ለእብን ኀበ አንኰርኰረት ወዓባይ ይእቲ ጥቀ። ወበዊኦን ውስተ መቃብር ረከባ አሐደ ወሬዛ እንዘ ይነብር መንገለ የማን ወይለብስ አልባሰ ንጹሐ ወደንገፃ። - ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደ ነበር ተመለከቱ። ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ።” ማር ፲፮፥ ፬ - ፭

ወንጌላዊው ቅ.ሉቃስ፦ “ወቦኣ ወኢረከባ ሥጋሁ ለእግዚእነ እግዚእ ኢየሱስ። ወእንዘ ይናፍቃ ወየኀጥኣ በእንተ ዝንቱ አስተርአይዎን ክልኤቱ ዕደው ወቆሙ ኀቤሆን ወይበርቅ አልባሲሆሙ። - ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤” ሉቃ ፳፬፥ ፫- ፬

ሐዋርያው ቅ.ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፦ “ወማርያምሰ ቆመት ኀበ መቃብር አፍኣ ወትበኪ ወእንዘ ትበኪ ሐወጸት ውስተ መቃብር። ወርእየት ክልኤት መላእክተ በጸዓድው አልባስ ወይነብሩ አሐዱ ትርኣሰ ወአሐዱ ትርጋፀ ኀበ ነበረ ሥጋሁ ለእግዚእ ኢየሱስ። - ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች።” ብሏልና። ዮሐ ፳፥ ፲፩- ፲፪ ብለው ገልጠውታል።

እኛም ቅዱሳን መላእክትን አብነት በማድረግ ነጭ ለብሰን የትንሣኤያችን ማዕከል በሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያናችን እንሰበሰባለን። ታድያ እንደ ቅዱሳን መላእክት ለብሶ በቤተክርስቲያን ማገልገልስ ምኑ ነው የሚያስወቅሰውና የሚያሳፍረው? ያኮራል እንጂ!