Get Mystery Box with random crypto!

“ባሕረ ወመስዐ አንተ ፈጠርከ፤ ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ ወይሴብሑ ለስምከ። - ሰሜ | ዋልድባ ገዳም

“ባሕረ ወመስዐ አንተ ፈጠርከ፤ ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ ወይሴብሑ ለስምከ። - ሰሜንንና ደቡብን አንተ ፈጠርህ ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል። እጅህ በረታች ቀኝህም ከፍ ከፍ አለች።” መዝ ፹፰፥ ፲፪
እንቋዕ ለበዓለ ደብረ ታቦር ፩ዱ እም፱ቱ ዐበይት በዓላት ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ አብጽሓነ አብጻሕክሙ!

ከጌታችን ዘጠኙ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ የሆነው በዓለ ደብረ ታቦር ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ታላቁ የታቦር ተራራ ይዟቸው ሄዶ የምሥጢር ሐዋርያት የተባሉ ፫ አዕማድ ሐዋርያትን ቅዱስ ጴጥሮስን፣ ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ያዕቆብን በርእሰ ደብር ላይ ሌሎቹን በእግረ ደብር አድርጓቸው ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ድንቅ በዓል ነው። በዚህ ጊዜ አማኒያን ሁሉ ሙሴ ነው እንዳይሉ ሞተ ሥጋን ከቀመሱ ቅዱሳን ሊቀ ነቢያት ሙሴን፣ ኤልያስ ነው ብለው እንዳይስቱም እስከ ሐሳዊው መሲህ መነሣት ድረስ ሕያዋን ሆነው ከሚኖሩት (ከብሔረ ሕያዋን) ነቢዩ ኤልያስን አምጥቶ የሙሴና የኤልያስ አምላክ መሆኑን አስረግጦ ገልጦ ጥያቄያቸውን መልሷል። ማቴ ፲፯፥ ፩- ፲፫፣ ማር ፱፥ ፩- ፲፫፣ ሉቃ ፱፥ ፳፰- ፴፮

ደብረ ታቦር በዘመነ ኦሪትም ባርቅና ሰራዊቱ በአምልኮተ እግዚአብሔር በመኖራቸውና በነቢይቱ ዲቦራ ጸሎት ኃይለ እግዚአብሔርን ተጎናጽፈው ለ፳ ዓመታት ያሰቃያቸውን ሲሳራን ከብዙ ሰራዊቱ ጋር ድል ያደረጉበት ቦታ ነው። መሳ ፬፥ ፩- ፳፬

ስለዚህ ታላቅ ተራራ ክብር ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር፦ “እኔ ሕያው ነኝና በተራሮች መካከል እንዳለ እንደ ታቦር፥ በባሕርም አጠገብ እንዳለ እንደ ቀርሜሎስ፥ እንዲሁ በእውነት ይመጣል፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የተባለው ንጉሥ።” ኤር ፵፮፥ ፲፰