Get Mystery Box with random crypto!

[የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚኽ የፍልሰታ ሱባኤ ለምእመናን መገለጥ] በመጋቤ ሐዲስ | ዋልድባ ገዳም

[የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚኽ የፍልሰታ ሱባኤ ለምእመናን መገለጥ]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝ ፵፬፥፲፪ ላይ “ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኲሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር” (የምድር ባለጠጎች አሕዛብ ኹሉ በፊትሽ ይማለላሉ) በማለት ትንቢትን እንደተናገረላት ብዙዎች ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያምን ተገልጻላቸው ለማየት ተመኝተዋል፤ ብዙዎቹም ልመናቸው ተሰምቶላቸው የአምላክ እናት ተገልጻላቸው እጅግ አስደናቂ ውበቷን አይተዋል፡፡

ከነዚኽ አባቶች ውስጥ ቅዱስ ኤፍሬም፣ ቅዱስ ያሬድ፤ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ አባ ይሥሐቅ፣ አባ ቴዎፍሎስ እና በደብረ ምጥማቅ የነበሩ ምእመናን ሌሎችም ብዙዎች ንጹሓን ክርስቲያኖች ይገኙበታል፡፡

የመልክአ ማርያም ደራሲም የአምላኩን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን ፊቷን ለማየት ሽቶ በናፍቆት ኾኖ፡-
“ሰላም ለመልክእኪ ዘተሠርገወ አሜረ
ዘያበርህ ወትረ
ፍቅርትየ አንቲ እንተ ታበድሪ ፍቅረ
አርእዪኒ ገጸ ዚኣኪ ማርያም ምዕረ
ዘኢይሰምዖ ካልእ እንግርኪ ነገረ”
(ኹልጊዜ (ዘወትር) የሚያበራ ፀሓይን ጌጥ ላደረገ መልክሽ ሰላምታ ይገባል፤ ፍቅርን የምትመርጪ (የምታስቀድሚ) አንቺ ፍቅረኛዬ ማርያም ሌላ የማይሰማው ነገርን እነግርሽ ዘንድ አንድ ጊዜ ያንቺን ፊት ግለጪልኝ) በማለት ተማፅኗታል፡፡

ቅዱስ ያሬድ አባታችንም በማይ ኪራሕ ሳለ እመቤታችን ተገልጻለት ፊቷን ለማየት ታድሏልና ይኽነን በዐይኑ ያየውን ውበቷን በድጓው ላይ እንዲኽ ሲል ጽፎታል፡-

“አይ ይእቲ ዛቲ እንተ ትወርድ እምሰማይ፤ ብርህት ከመ ፀሓይ፤ አዳም ቆማ ወክሣዳ ከመ አርማስቆስ፤ መዐዛ አፉሃ ከመ ኮል” (ከሰማይ የምትወርደው እንደ ፀሐይም የምታበራው ርሷ ማን ናት! አንገቷ እንደ ግንብ ቀጥ ያለ ነው፤ የአፏም መዐዛ እንደ እንኮይ ነው) በማለት በተመስጦ የተመለከተውን ውበቷን ተናገረ፡፡

ይኽ የቤተ ክርስቲያን ጌጥ ቅዱስ ያሬድ በዚኽ ሳያበቃ በመላእክት እየተመሰገነች ስለተገለጸችለት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ያየውን የውበቷን ነገር ሲናገር፦
“እምኀበ መላእክት ትሴባሕ አዳም ሥና፤ መዐርዒር ቃላ ወኲሉ ነገራ በሰላም … እምወርኅ ወእምፀሓይ ይሤኒ ላሕያ …ከመ ፍሕሶ ቀይሕ ከናፍሪሃ ወከመ ኮል መዐዛ አፉሃ ወከመ ሮማን ቂሐተ መላትሒሃ … (በመላእክት ትመሰገናለች፤ ደም ግባቷ ያማረ ነው፤ ቃሏ እንደ ማር የጣፈጠ፤ ነገሯ ኹሉ በሰላም የተመላ ነው … ውበቷ ደም ግባቷ ከጨረቃና ከፀሓይ ይልቅ ያምራል፤ ከንፈሮቿ ፍሕሶ እንደሚባል አበባ ቀይ ናቸው፤ የጒንጯ ቅላትም እንደ ሮማን ቅርፍት ነው) እያለ ሊቁ ማሕሌታይ በመንፈስ ተቃኝቶ ይመሰክርላታል፤ አይ መታደል! አይ መባረክ!

ውዳሴዋ በእጅጉ የበዛለት ስለ ርሷ ኆኅተ ብርሃን፣ እንዚራ ስብሐት፣ መዐዛ ቅዳሴ፣ አርጋኖን፣ ሰላምታ፣ መዝሙረ ድንግል እና ሌሎችም ብዙ ብዙ ለመሰከረላት ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ብዙ ጊዜ እየተገለጸችለት በዐይኑ ተመልክቷታልና የመልኳን ውበት በአርጋኖን ዘቀዳሚት ላይም፡-
“አልቦ ዘይሤንዮ ለላሕይኪ ኢ ጎሕ ወኢበርህ ኢ ፀሓይ ወኢወርኅ ኢ ዋካ ወኢጸዳል አልቦ ዘይበርህ እምጸዳለ ዐይንኪ ኢ ቤዝ ዘያንበለብል በገጸ ሰማይ ወኢባሕርይ ዘያንጸበርቅ ዲበ ርእሰ ነገሥት ወአልቦ ዘይምዕዝ እምጼና አንፍኪ ወእምጼና አልባስኪ ኢከልበኔ ወኢሐንክሶ ወኢአስጰዳቶስ ወኢናርዱ ቅድው ዘዕጹብ ሤጡ ወመዐድም ኲለንታኪ ወክሉል በጸጋ መንፈስ ቅዱስ”

(ደም ግባትሽን የሚያምረው (የሚበልጠው) የለም፤ የንጋት ውጋገንም ቢኾን! ብርሃንም ቢኾን! ፀሓይም ቢኾን! ጨረቃም ቢኾን! ወዝሽን ለዛሽን የሚመስለው የለም፤ ከዐይንሽ ብርሃን ይልቅ የሚበራ የለም፤ በሰማይ ፊት የሚንቦገቦግ ኮከብም ቢኾን! በነገሥታት ራስ ላይ የሚያንጸባርቅ ዕንቊም ቢኾን! ከአፍንጫሽም መዐዛ ከልብሶችሽም ሽታ የበለጠ የሚሸት የለም፤ ከልበኔም ቢኾን! ሐንክሶም ቢኾን! አስጰዳቶስም ቢኾን! ዋጋው ውድ የኾነ ናርዱ የሚባል ሽቱም ቢኾን! ኹለንተናሽ ያማረ ነው በመንፈስ ቅዱስ ጸጋም የተጋረደ ነው) ብሏታል፡፡

ልክ እንደ ርሱ የአምላክን እናት ፊቷን ለማየት የተመኙ ብዙዎች ቅዱሳን ነበሩ፤ ለምሳሌም ያኽል ከቅዱሳን አበው መኻከል አባ ይሥሐቅ እመቤታችንን በፍጹም ልቡናው ከመውደዱ የተነሣ ከሠርክ ጸሎት በኋላ ሌሎች መነኮሳት ለመኝታ ወደ የበኣታቸው ሲኼዱ ርሱ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመኼድ በቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ፊት ቆሞ በፊቷ እየተማለለ ሦስት መቶ ስግደትን እየሰገደ፤ በእያንዳንዱ ስግደቱ ላይ “ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ አርእየኒ እመከ አሐተ ሰዓተ” (ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለአንዲት ሰዓት እናትኽን አሳየኝ) እያለ በመጸለይ ለሰባት ዓመት ቆየ።

በሰባተኛው ዓመት በታላቅ ግርማ ተገልጻለት የአምላክን እናት ፊት ለማየት በቅቷል፤ ርሷም ምን እንደሚሻ ብትጠይቀው በታላቅ መንፈሳዊ ደስታ በመኾን የንግሥተ ሰማይ ወምድር የርሷን ገጽ ያዩ ዐይኖቹ ሌላ ነገርን ማየት እንደማይፈልጉና ከልጇ እንድታማልደው ብቻ እንደሚፈልግ ነግሯት፤ ርሷም ከሦስት ቀን በኋላ እንደሚያርፍ ክፍሉም ከርሷ ጋር መኾኑን ገልጻለት ባርካው ዐርጋ፤ መልኳን አይቶ በሦስተኛው ቀን ይኽ ቅዱስ አባት ዐርፏል፡፡

የእመቤታችን ፍቅር በእጅጉ የበዛለት አባ ጽጌ ድንግልም በደብረ ምጥማቅ በታላቅ ክብር ተገልጻ ለምእመናን የታየችው የአምላክ እናት ለርሱም ትገለጽለት ዘንድ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፉ ላይ፡-
“አመ ትበርቂ በደብረ ምጥማቅ ኀምሰ ዕለታተ
ትእምርተ ገጽኪ ይርአይ እስከ ይትነሣእ ዘሞተ
ሚ መጠነ ማርያም ታሥተፌሥሒ ትፍሥሕተ
ኅድጊሰ ጽጌ ፍቅርኪ በጊዜ ንቃሑ መዓልተ
ብፁዕ ዘርእየኪ በሕልሙ ሌሊተ”
(የፊትሽን መልክ ያይ ዘንድ የሞተ ሰው እስኪነሣ ድረስ በደብረ ምጥማቅ ለዐምስት ቀናት ያኽል በተገለጽሽ ጊዜ ማርያም ምን ያኽል ደስ ታሰኚ ኖሯል! በቀን የታየው የፍቅርሽ አበባ ይቅርና ሌሊት በሕልሙ ያየሽ ምስጉን ነው) በማለት ተማፅኗታል፡፡

የእመቤታችን ታማኝ ወዳጅ አባ ጽጌ ድንግል በተመስጦ በመኾን እጅግ ድንቅ የኾነችውን የአምላክን እናት ሥዕል ካየ በኋላ ይኽነን የምስጋና ቃላት ለርሷ ያቀርባል፡-
“ሥዕልኪ ጽግይተ ላሕይ ዘከመዝ ትኤድም በዓለም
እፎ ይሤኒ በሰማይ ላሕየ ገጽኪ ማርያም
ሐሤተ ትእምርትኪ እጽገብ አስተርእዪኒ በሕልም
እስመ አውዐየኒ ነደ ፍቅርኪ ፍሕም
አጥፍኦቶ ዘኢይክል ዝናም”
(ማርያም ሥዕልሽ በዓለም እንዲኽ የምታበራ ከኾነ በሰማይ የፊትሽ መልክ ምን ያምር! አንቺን ከማየት የሚገኘውን ደስታ እጠግብ ዘንድ በሕልም ተገለጪልኝ፤ ዝናብ ሊያጠፋው የማይቻለው የፍቅርሽ እሳት አንድዶኛልና) ብሏል፡፡

በመኾኑም በዚኽ ሱባኤ ሐዋርያት የአምላክን እናት አይተው እንደተደሰቱ፤ ዛሬም ለእኛ ለልጆቿ በረድኤት ትገለጽልን ዘንድ አበው ካህናት ሌሊቱን በሰዓታት ምስጋና “ንዒ ኀቤየ ኦ ድንግል ምስለ ወልድኪ ፍቁርኪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ትባርኪ ላዕሌነ” (ድንግል ሆይ ከተወዳጅ ልጅሽ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋራ ወደ እኔ ነዪ እኛን ትባርኪ ዘንድ (በእኛ ላይ በረከትን እንድታሳድሪ) በማለት ይማፀኗታል፤ እኛም የማይጠገበው ውዳሴዋን ቅዳሴዋን በመተርጐም የቅዱስ ኤፍሬም የአባ ሕርያቆስ እመቤት ትባርከን ዘንድ እንለምናታለን፡፡