Get Mystery Box with random crypto!

#ጥንታዊው_ቅድስት_መስቀል_ክብራ_ገዳም በትግራይ ክልል ሽሬ አውራጃ ከሽረ ከተማ 24 ኪ.ሜ ርቀት | ዋልድባ ገዳም

#ጥንታዊው_ቅድስት_መስቀል_ክብራ_ገዳም
በትግራይ ክልል ሽሬ አውራጃ ከሽረ ከተማ 24 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ዞማ መዳባይ ታብር በሚባል አካባቢ ውብ በሆኑ በሰንሰለታማ ትላልቅ ድንጋዮች መካከል የሚገኝና በመሠላል የሚወጣ ድንቅ ገዳም ነው። ወደ ገዳሙ ለመሄድ ከሽረ እንዳ ሥላሴ በሞተር መጓዝ አለበለዚያ ግን በእግር ከ4:30 በላይ መጓዝ ግድ ይላል።

እናታችን ቅድስት መስቀል ክብራ ትውልዷ ሰሜን ወሎ ላስታ ቡግና ሲሆን የቅዱስ ላሊበላ ባለቤት ናት። ቅዱስ ላልይበላን እና ቅድስት መስቀል ክብራን ያጋባቸው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል እንደሆነ የሁለቱ ቅዱሳን ዜና ሕይወት (መጽሐፈ ገድላቸው) ይገልጣል። በፈቃደ እግዚአብሔር በተፈጸመው በዚህ ቅዱስ ጋብቻቸውም ከቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ቀጥሎ በላስታ ላይ የነገሠውን ደገኛውን ንጉሥ ይትባረክን ወልደዋል፡፡

መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶ የሚያንጻቸውን የሕንጻ ዲዛይኖችና ሌሎችንም ብዙ ምሥጢራትን ካሳየውና ወደ ምድር ከመለሰው በኋላ ድጋሚ ተገልጦለት፦ "እንዳንተ የተመረጠች ናት፤ እንደ ልብህም ትሆናለች፤ ሥራዋም ከሥራህ አያንስም፤ እርሷ የተመረጠች የእግዚአብሔር አገልጋይ ናትና።" በማለት መልአኩ የቅድስት መስቀል ክብራን ንጽሕናና ቅድስና መስክሮላታል፡፡

ቅዱስ ላሊባላ 11 እጅግ አስደናቂ የሆኑ ፍልፍል ቤተ መቅደሶቹን ከመላእክት ጋር ሲያንጽ ብታየው ልቧ በመንፈሳዊ ተመስጦ ተመልቶ እርሷም እግዚአብሔር ፈቅዶላት አስደናቂውን የአባ ሊባኖስን ቤተመቅደስ ራሷ እንዳነጸችው መጽሐፈ ገድሏና ገድለ ቅዱስ ላሊበላ ያስረዳል፡፡

ቅድስት መስቀል ክብራን ወደ ትግራይ እየመራ የወሰዳት ራሱ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ እርሷን በትግራይ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል እንዲጠብቃት ከተዋት በኋላ ቅዱስ ላሊበላን ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ መንግሥተ ሰማያት አውጥቶታል፡፡ ቅድስት መስቀል ክብራም በትግራይ ሆና መልአኩ እየጠበቃት ከሰው ተለይታ በታላቅ ተጋድሎ ኖረች፡፡ በቀን እልፍ እልፍ እየሰገደች በታላቅ ተጋድሎ ስትኖር ጌታችን ተገልጦ ክብሯ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ጋር እኩል መሆኑን ነግሯታል፡፡

ይህቺም ቅድስት እናት ብዙ ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽማለች፡፡ ለምሳሌ በመስቀል ጦርነት ጊዜ እስላሞች ከባሕር ማዶ እየፈለሱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በፍቅር እየተቀበለችና እያስተናገደች ሃይማኖትንና ሕገ እግዚአብሔርን እያስተማረች ወደ ክርስትና እንዲገቡና እንዲጠመቁ አድርጋለች። የጻድቋ ረድኤት አይለየን፤ አምላከ መስቀል ክብራ በየዓመቱ ሐምሌ 27 ቀን ከሚከበረው በዓለ ዕረፍቷ የቃልኪዳን በረከቷን ያድለን፤ በጸሎት ልመናዋ ይማረን። አሜን!!!

ገዳሙን በምስልና ድምጽ ለመመልከት የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ (Link) ይክፈቱ፤ ለተጨማሪ ቪዲዮዎች የዩቲዩብ ቻናላችንን (መኮሬታ Mekoreta Tubeን) ይቀላቀሉ።