Get Mystery Box with random crypto!

ሥላሴአዊ ቅጥፈት በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው። 4፥171 «ሦስት | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

ሥላሴአዊ ቅጥፈት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

4፥171 «ሦስት ነው» አትበሉ! ተከልከሉ! ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አሏህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ وَلَا تَقُولُوا ثَلَاثَةٌ ۚ انتَهُوا خَيْرًا لَّكُمْ ۚ إِنَّمَا اللَّهُ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ

ከ 260 እስከ 339 ድኅረ ልደት ይኖር የነበረው የቂሳሪያው ኤጲስ ቆጶስ አውሳብዮስ የቤተክርስቲያን ታሪክ"Church History" በሚል መጽሐፉ ሐዋርያው ማቴዎስ ለዕብራውያን በዕብራይስጥ ቋንቋ ደብዳቤ እንደጻፈላቸው ተናግሯል፦
፨፦ "ስለዚህ ማቴዎስ በዕብራይስጥ ቋንቋ ደብዳቤ ጽፏል"።
(አውሳቢዮስ የቤተክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍ 3 ምዕራፍ 39 ቁጥር 16)

፨፦ "እርሱ ማቴዎስ በመጀመሪያ ለዕብራውያን የሰበከው ነው"።
(አውሳቢዮስ የቤተክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍ 3 ምዕራፍ 39 ቁጥር 16)

ማቴዎስ ይህንን ደብዳቤአዊ ወንጌል ከ 45 እስከ 55 ድኅረ ልደት እንደጻፈ ይገመታል፥ የመጀመሪያ መቶ ክፍለ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ኢቦናይት የሚባሉ አይሁዳውያን የኢየሱስ ተከታዮች ማቴዎስ ለዕብራውያን የጻፈውን ይህንን ወንጌል ብቻ ይቀበሉ እንደነበር አውሳብዮስ ይናገራል፦
"እና ለዕብራውያን ተደረሰ የተባለውን ወንጌል ብቻ ይጠቀሙ ነበር"።
(አውሳቢዮስ የቤተክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍ 3 ምዕራፍ 25 ቁጥር 4)

የቂሳሪያው አውሳብዮስ "የወንጌል ማረጋገጫ"Proof of the Gospel" በሚል መጽሐፉ ላይ ማቴዎስ በዕብራይስጥ በጻፈው ወንጌል ላይ ኢየሱስ ለሐዋርያት ያላቸው፦ "እንግዲህ ሂዱ እና አሕዛብን ሁሉ በስሜ ደቀ መዛሙርት አድርጉ! ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተማሯቸው" በማለት እንዳዘዛቸው ተናግሯል፦
፨፦ "ከአንድ ቃል እና ድምፅ ጋር እርሱም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦ "እንግዲህ ሂዱ እና አሕዛብን ሁሉ በስሜ ደቀ መዛሙርት አድርጉ! ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተማሯቸው"።
(አውሳቢዮስ የወንጌል ማረጋገጫ ቅጽ 1 መጽሐፍ 3 ምዕራፍ 6 ቁጥር 132 ገጽ 152)

፨፦ "እርሱም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦ "እንግዲህ ሂዱ እና አሕዛብን ሁሉ በስሜ ደቀ መዛሙርት አድርጉ"።
(አውሳቢዮስ የወንጌል ማረጋገጫ ቅጽ 1 መጽሐፍ 3 ምዕራፍ 7 ቁጥር 136 ገጽ 157)

፨፦ "እርሱም ለእነርሱ እንዲህ አላቸው፦ "አሕዛብን ሁሉ በስሜ ደቀ መዛሙርት አድርጉ"።
(አውሳቢዮስ የወንጌል ማረጋገጫ ቅጽ 1 መጽሐፍ 3 ምዕራፍ 7 ቁጥር 138 ገጽ 159)

"አሕዛብ" የሚለው የግዕዝ ቃል "ሕዝብ" ለሚለው ብዜት ሲሆን በጸያፍ ርቢ "ሕዝቦች" ማለት ነው፥ በዕብራይስጥ ለዕብራውያን በተጻፈው የመጀመሪያው የማቴዎስ ወንጌል ላይ ኢየሱስ፦ "አሕዛብን ሁሉ በስሜ ደቀ መዛሙርት አድርጉ" የሚል ሆኖ ሳለ ስሙ እና ማንነቱ በውል የማይታወቅ ሰው የማርቆስን ወንጌል መሠረት አድርጎ በግሪክ ኮይኔ በማቴዎስ ዳቦ ስም የማቴዎስ ወንጌል አዘጋጀ። በዚህ ወንጌል ውስጥ፦ "እንግዲህ ሂዱ እና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው" የሚል ሥላሴአዊ ቅጥፈት ተቀጠፈ፥ ዓይን ያስፈጠጠ እና ጥርስ ያገጠጠ ይህንን ሐቅ መድብለ-ዕውቀት"encyclopedia" እንዲህ ያትታሉ፦
፨፦ "ማቴዎስ 28፥19 በኃላ በቤተክርስቲያን ሁኔታ በተለየ ብቻ ቀኖናዊ የሆነ ነው፥ ለዛ ነው ዓለም አቀፋዊነቷ ከቀደምት የክርስቲያን ታሪክ እውነታዎች ጋር የሚቃረን የሆነው። የሥላሴአውያን ቀመር ለኢየሱስ ንግግር ባዕድ ነው"።
(ዓለም ዓቀር መደበኛ የባይብል መድብለ ዕውቀት ቅጽ 4, ገጽ 2637)

፨፦ "የጥምቀት ቀመር "በኢየሱስ ስም" ከሚል ወደ "በአብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ስም" ወደሚል በዓለም ዐቀፍ ቤተክርስቲያን በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ተለውጧል"።
(የካቶሊክ መድብለ ዕውቀት ቅጽ 2, ገጽ 263)

በተጨማሪም "እንግዲህ ሂዱ እና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው" የሚለውን ሥላሴአዊ ቅጥፈት እና ቅሰጣ የባይብል ማብራሪያ"Commentary" እና እትም"Version" ወሮበላ መሆኑን እንጩን ፍርጥ አርገው ነግረውናል፦
፨፦ "በአብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ስም" የኢየሱስ ቃል ሳይሆን በኃላ የተጨመረ ቃል ነው"።
(ቴንደል የአዲስ ኪዳን ማብራሪያ ቅጽ 1, ገጽ 275

፨፦ "ዘመናዊ ኂስ ይህንን የሥላሴአውያን ቀመር ኢየሱስን ማስዋሸት ነው፥ ያ በኃላ ላይ የቤተክርስቲያን ትውፊት የሚወክል ነው"።
(1989 አዲሱ የተሻሻለ የመደበኛ ባይብል እትም)

የሥላሴ አማንያን"trinitarian" ሆይ! ፈጣሪን "አንድ ነው" ባላችሁበት አፍ «ሦስት ነው» አትበሉ! ተከልከሉ! ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አሏህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፦
4፥171 «ሦስት ነው» አትበሉ! ተከልከሉ! ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አሏህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ وَلَا تَقُولُوا ثَلَاثَةٌ ۚ انتَهُوا خَيْرًا لَّكُمْ ۚ إِنَّمَا اللَّهُ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ

አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም በተውሒድ ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም