Get Mystery Box with random crypto!

ሁሉን ዓቀፍ ደኅንነት በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ 5፥72 | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

ሁሉን ዓቀፍ ደኅንነት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

5፥72 እነሆ በአሏህ የሚያጋራ ሰው አላህ በእርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፡፡ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ إِنَّهُ مَن يُشْرِكْ بِاللَّهِ فَقَدْ حَرَّمَ اللَّهُ عَلَيْهِ الْجَنَّةَ وَمَأْوَاهُ النَّارُ

በኢሥላም አስተምህሮት ሰው በአሏህ ላይ ላሻረከው የሺርክ ወንጀል አሏህ በእርግጥ ጀነትን እርም አድርጎበታል፥ ለሙሽሪክ መኖሪያውም እሳት ናት። አሏህ በእርሱ ማጋራትን በፍጹም አይምርም፥ ከዚህ ሌላ ያለውንም ኀጢአት ለሚሻው ሰው ይምራል፦
5፥72 እነሆ በአሏህ የሚያጋራ ሰው አላህ በእርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፡፡ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ إِنَّهُ مَن يُشْرِكْ بِاللَّهِ فَقَدْ حَرَّمَ اللَّهُ عَلَيْهِ الْجَنَّةَ وَمَأْوَاهُ النَّارُ
4፥48 አሏህ በእርሱ ማጋራትን በፍጹም አይምርም፡፡ ከዚህ ሌላ ያለውንም ኀጢአት ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡ إِنَّ اللَّهَ لَا يَغْفِرُ أَن يُشْرَكَ بِهِ وَيَغْفِرُ مَا دُونَ ذَٰلِكَ لِمَن يَشَاءُ

ወደ ባይብል ስንሄድም የማያምኑ የሚቀጡበት ቅጣት ዘውታሪ ቅጣት ለመሆኑ እኵሌቶቹ ወደ እፍረት እና ወደ ዘላለም ጕስቍልና እንደሚሄዱ ይናገራል፦
ዳንኤል 12፥2 በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረት እና "ወደ ዘላለም ጕስቍልና"።
ኤርምያስ 23፥40 የዘላለምንም ስድብ ከቶም ተረስቶ የማይጠፋውን "የዘላለምን እፍረት" አመጣባችኋለሁ።

ይህ ሆኖ ሳለ "ሁሉን ዓቀፍ ደኅንነት"universal salvation" የሚባለው ትምህርት "ሰው ሁሉ የሚቀጣው ቅጣት ተቀጥቶ ሁሉም ከገሃነም ይድንና ገነት ይገባል" የሚል ትምህርት ነው፥ ይህንን ትምርህት ከሚያስተምሩት የጥንት የቤተክርስቲያን አበው መካከል፣ በ 180 ድኅረ ልደት ቅዱስ ፔንታነስ፣ በ 150 ድኅረ ልደት የእስክንድርያው ቀለሜንጦስ፣ በ 220 ድኅረ ልደት የእስክንድርያው አርጌንስ እና በ 400 ድኅረ ልደት ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ተጠቃሽ ናቸው። እነርሱም ከሚጠቅሱስ ተወዳጆች ጥቅሳት መካከል ግንባር ቀደም ይህ ነው፦
ማርቆስ 9፥49 ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና፥ መሥዋዕትም ሁሉ በጨው ይቀመማል።

መሥዋዕት ሁሉ በጨው የሚቀመመው በጨው እንደሆነ ሰውም በእሳት መቀጣቱ ለእርማት መሆኑን ይናገራሉ፦
ዕብራውያን 12፥9-11 ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን? እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።

"እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል" በሚለው ውስጥ ሁሉም ጥፋተኛ የጥፋቱን ልክ ተቀጥቶ ወደ ገነት ይገባል የሚል ትምህርት ነው፥ "ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም" ማለቱ "የገሃነም ቅጣት ጊዜአዊ ነው" የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፦
1 ጢሞቴዎስ 4፥10 ሰውን ሁሉ ይልቁንም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ ነው።

ሕያው አምላክ የሚያምኑት ብቻ ሳይሆን "ሰውን ሁሉ" እንደሚያድን ከላይ ያለው ጥቅስ ፍንጭ ይሰጣል፥ ሰዎችን ሁሉ የሚያድን ይህ ጸጋ የተገለጠው ሰዎች ሁሉ ሊድኑ በሚወድ በአምላክ ፊት መልካም እና ደስ የሚያሰኝ ጳውሎስ ተናግሯል፦
ቲቶ 2፥11 ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና።
1 ጢሞቴዎስ 2፥3 ሰዎች ሁሉ ሊድኑ እና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካም እና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።
ሮሜ 5፥19 በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።

"ብዙዎች" የሚለው ቃል "ሁሉም" በሚል ይረዱትና ሁሉም ሰው በአንዱ አዳም ኃጢአተኞች ከሆኑ ሁሉም ሰው በአንዱ ክርስቶስ ጻድቃን ይሆናሉ የሚል ትምህርት ነው። ታዲያ ለምን ብዙ ቦታ "በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ" ይላል?፦
2 ተሰሎንቄ 1፥9 ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ። οἵτινες δίκην τίσουσιν ὄλεθρον αἰώνιον ἀπὸ προσώπου τοῦ Κυρίου καὶ ἀπὸ τῆς δόξης τῆς ἰσχύος αὐτοῦ,

እዚህ አንቀጽ ላይ "ዘላለም" የሚለው የግሪከኛ ቃል "አይኦንዮን" αἰώνιον ሲሆን መጨረሻ የሌለው ዝንተ ዓለም ጊዜ ብቻ ሳይሆን የማይታወቅ መጻኢ ውስን ጊዜን ስለሚያመለክት "ቅጣቱ ጊዜአዊ ነው" በማለት "አይኦንዮን" αἰώνιον ለማይታወቅ መጻኢ ውስን ጊዜን የተጠቀመበት ጥቅስ ይጠቅሳሉ፦
ይሁዳ 1፥7 "በዘላለም እሳት" እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል። πρόκεινται δεῖγμα πυρὸς αἰωνίου δίκην ὑπέχουσαι.

"ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች የተቀጡት ለውስን ጊዜ ቢሆንም ቅጣታቸውን "በዘላለም እሳት" በማለት ተናገረ ማለት መጨረሻ የሌለው ዝንተ ዓለም ጊዜ አይደለም" በማለት ይሞግታሉ። ይህ ሙግት ሥነ ልቡናዊ ሙግት ቢመስልም ውኃ የሚያነሳ እና የሚቋጥር ሙግት አይደለም፥ ምክንያቱም ሰው በገነት ለሚኖረው ዘላለማዊ ሕይወት የገባው ቃል ተመሳሳይ "አይኦንዮን" αἰώνιον ነው፦
ማቴዎስ 25፥46 እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ። καὶ ἀπελεύσονται οὗτοι εἰς κόλασιν αἰώνιον, οἱ δὲ δίκαιοι εἰς ζωὴν αἰώνιον.

"ዘላለም ቅጣት" ለሚለው የገባው "አይኦንዮን" αἰώνιον የማይታወቅ መጻኢ ውስን ጊዜን ካመለከተ ጻድቃን የሚገቡበት "ዘላለም ሕይወት" ለሚለው የገባው "አይኦንዮን" αἰώνιον የማይታወቅ መጻኢ ውስን ጊዜ ነውን? ገሃነም ጊዜአዊ ከሆነ ቢያንስ "ወደ ገነት ይገባሉ" ይባል ይሆናል፥ ገነት እንደ ገሃነም ጊዜአዊ ከሆነ ከገነት ወደ የት ይገባሉ? ይህ የተመታ እና የተምታታ ትምህርት እነ ቅዱስ ፔንታነስ፣ እነ የእስክንድርያው ቀለሜንጦስ፣ እነ የእስክንድርያው አርጌንስ፣ እነ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ የጠነሰሱት ጥንስስ የጳውሎስን ትምህርት መሠረት አርገው ነው። ዛሬ በዘመናችን ሁሉን ዓቀፍ ደኅንነት የሚባል ትምህርት ከሚያስተምሩ መካከል የእግዚአብሔር መንግሥት ቤተክርስቲያን መስራች ካሳ ኬርጋ እና አዲሱ ዘመን እንቅስቃሴ የመሳሰሉት ናቸው።
ይህንን ትምህርት የሚያስየምሩት እና ባለማወቅ የሚማሩትን አሏህ ሂዳያህ ይስጣቸው! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም