Get Mystery Box with random crypto!

ኢየሱስ አብ ነውን? በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ 59፥24 እ | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

ኢየሱስ አብ ነውን?

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

59፥24 እርሱ አላህ ፈጣሪው፣ "አስገኚው"፣ ቅርጽን አሳማሪው ነው፡፡ ለእርሱ መልካሞች ስሞች አሉት፡፡ هُوَ اللَّهُ الْخَالِقُ الْبَارِئُ الْمُصَوِّرُ ۖ لَهُ الْأَسْمَاءُ الْحُسْنَىٰ

አምላካችን አሏህ በቁርኣን ከተገለጹ ዘጠና ዘጠኝ ስሞቹ አንዱ "አል ባሪእ" الْبَارِئ ማለትም "አስገኚው" ነው፦
59፥24 እርሱ አላህ ፈጣሪው፣ "አስገኚው"፣ ቅርጽን አሳማሪው ነው፡፡ ለእርሱ መልካሞች ስሞች አሉት፡፡ هُوَ اللَّهُ الْخَالِقُ الْبَارِئُ الْمُصَوِّرُ ۖ لَهُ الْأَسْمَاءُ الْحُسْنَىٰ

በዕብራይስጥ ለአንዱ አምላክ "አብ" אָ֑ב ማለት "አስገኚ" "ምንጭ" ማለት ነው፥ አንዱ አምላክ ሰውን ጭቃ አርጎ ስለ ሠራ "አብ" אָ֑ב ተብሏል፦
ኢሳይያስ 64፥8 ያህዌህ ሆይ! አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ጭቃ ነን አንተም ሠሪያችን ነህ፥ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን። יְהוָ֖ה אָבִ֣ינוּ אָ֑תָּה אֲנַ֤חְנוּ הַחֹ֙מֶר֙ וְאַתָּ֣ה יֹצְרֵ֔נוּ וּמַעֲשֵׂ֥ה יָדְךָ֖ כֻּלָּֽנוּ׃

እዚህ አንቀጽ ላይ አንዱ አምላክ "አብ" אָ֑ב ሲባል ሰዎች "ጭቃ" ተብለዋል፥ ጭቃው የእጁ ሥራ ሲሆን "አባት" የሚለው "ሠሪ" ማለት ስለሆነ "አባታችን" የሚለው "ሠሪያችን" በሚል ተለዋዋጭ ቃል መጥቷል። "ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? ሲልም "ለሁላችን አንድ ሠሪ" መኖሩን የሚያሳይ ነው፦
ሚልክያስ 2፥10 ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን? הֲלֹ֨וא אָ֤ב אֶחָד֙ לְכֻלָּ֔נוּ הֲלֹ֛וא אֵ֥ל אֶֽחָ֖ד בְּרָאָ֑נוּ
ዮሐንስ 8፥41 አንድ አባት አለን፥ እርሱም አምላክ ነው። ἕνα Πατέρα ἔχομεν τὸν Θεόν.
ኤፌሶን 4፥6 አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። εἷς Θεὸς καὶ Πατὴρ πάντων,

"አባት" ለአንዱ አምላክ ሲቀጸል በራሱ "አስገኚ" ማለት እንጂ "የባሕርይ አባት" ማለት አይደለም። ይህ ሆኖ ሳለ የሐዋርያት ቤተክርስቲያን በተለምዶው ኢየሱስ ብቻ"only Jesus" የሚባሉት "ኢየሱስ አብ ነው" ብለው ይህንን ጥቅስ ይጠቅሳሉ፦
ዮሐንስ 14፥10 ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። ὁ δὲ Πατὴρ ἐν ἐμοὶ μένων ποιεῖ τὰ ἔργα αὐτοῦ.

ይህ ጥቅስ ጭራሽ "እኔ" የሚለው ማንነት እና "እኔ" በሚለው የሚኖረው አብ ሁለት ማንነት እንደሆኑ ቁልጭ አርጎ ያሳያል፥ እዚህ አንቀጽ ላይ "የሚኖር" ለሚለው የገባው ቃል "ሜኖን" μένων ነው። አብ በኢየሱስ መኖሩ ኢየሱስን አብ ካሰኘውማ በፍቅር የሚኖር ሰው አምላክ ሊሆን ነው፦
1ኛ ዮሐንስ 4፥16 በፍቅርም የሚኖር በአምላክ ይኖራል፥ "አምላክ በእርሱ ይኖራል"። καὶ ὁ μένων ἐν τῇ ἀγάπῃ ἐν τῷ Θεῷ μένει καὶ ὁ Θεὸς ἐν αὐτῷ μένει.

እዚህ አንቀጽ ላይ "ይኖራል" ለሚለው የገባው ቃል "ሜኔይ" μένει ሲሆን ከላይ ካለው ጋር በተመሳሳይ መሠረቱ "ሜኖ" μένω ነው፥ ታዲያ በፍቅር የሚኖር ሰው አምላክ ነውን? በመቀጠል "ኢየሱስ አብ ነው" ብለው ይህንን ጥቅስ ይጠቅሳሉ፦
ዮሐንስ 14፥11 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ። πιστεύετέ μοι ὅτι ἐγὼ ἐν τῷ Πατρὶ καὶ ὁ Πατὴρ ἐν ἐμοί·

"እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ" ማለቱ ኢየሱስን አብ አብን ኢየሱስ ካደረገው ሐዋርያት ኢየሱስ ወይም ኢየሱስ ሐዋርያት ይሆኑ ነበር፦
ዮሐንስ 14፥20 እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ። ἐν ἐκείνῃ τῇ ἡμέρᾳ γνώσεσθε ὑμεῖς ὅτι ἐγὼ ἐν τῷ Πατρί μου καὶ ὑμεῖς ἐν ἐμοὶ κἀγὼ ἐν ὑμῖν.

"እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ" ማለቱ ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር ያላቸውን ግኑኝነት የሚያሳይ እንጂ ሐዋርያትን ኢየሱስ ካላደረገ እንግዲያውስ "እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ" ማለቱ አብ ከኢየሱስ ጋር ያለውን ግኑኝነት የሚያሳይ እንጂ ኢየሱስን አብ አያደርገውም። በነገራችን ላይ ሥላሴአውያን ለኢየሱስ አምላክነት ከሚጠቅሷቸው ተወዳጆች ጥቅስ አንዱ ነውና ሙግቱ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ነው፥ ስለዚህ ኢየሱስ አብ ወይም አምላክ ሳይሆን የአምላክ መልእክተኛ ነው። እናንተንም አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም