Get Mystery Box with random crypto!

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ! * በሀገራችን ኢትዮጵያ ላለ | Voice of Amhara የአማራ ድምጽ ®

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ!
*
በሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት ዲሞክራሲያዊ ሥርአት ለመትከል ፣ እኩልነትን ለማረጋገጥ እና የኢትዮጵያን ሕዝብ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ለማድረግ በርካታ መስዋዕትነት የተከፈለ እና በብዙ ውጣውረዶች ውስጥ ያለፍን ቢሆንም ፣ ትግላችን እና ጉዟችን ከድጡ ወደማጡ እየሆነ ፣ ሀገራዊ ፈተናዎቻችን እየበረቱ እና አዳዲስ ችግሮች እየተፈጠሩ በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ ኅልውናችንን እና አንድነታችንን ላይ አደጋ የጋረጡ ፈተናዎች ከፊት ለፊታችን ተደቅነው ይገኛሉ፡፡ ባለፉት አምስት አስር ዓመታት ውስጥ በሀገራችን ኢትዮጵያ ከተፈጠሩ ፖለቲካዊ የኃይል አሰላለፎች ውስጥ ዋነኛ ኃይል ሆኖ የወጣው “የነጻ-አውጭዎች” የኃይል አሰላለፍ የአማራን ሕዝብ በጠላትነት በመፈረጅ እድልና አጋጣሚ በፈቀደለት ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ሁሉ በሕዝባችን ላይ ተነግሮ የማያልቅ መከራ እና እልቂት ሲያደርስ ቆይቷል፡፡

ሀገር ለማፍረስ ተማምለው ጫካ የወረዱ እና በለስ ቀንቷቸው አራት ኪሎ እግር የጣላቸው “ነጻ-አውጭ” ድርጅቶች ያለሕዝብ ፈቃድ እና ይሁንታ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫኑት ሀገር-አፍራሽ ሕገ-መንግስታዊ ሥርአት እና አፓርታይዳዊ የአስተዳደር መዋቅር ስራ ላይ ከዋለበት ካለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ፖለቲካዊ ቀውሱ እና ምስቅልቅሉ ወደ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል እንዲወርድ እና በየእለቱ የወገኖቻችን ሕይወት የሚቀጠፍበት ፣ ከቀያቸው የሚፈናቀሉበት እና በማያቋርጥ የእልቂት እና የቀውስ አዙሪት ውስጥ ተዳርገን እንገኛለን፡፡ የቀውስ አዙሪቱ ተባብሶ ቀጥሎ ቀድሞ እያሰለሰ በአማራ ሕዝብ ላይ ሲፈጸም የኖረው የዘር-ማጥፋት ወንጀል አሁን የዕለት ተዕለት ክስተት እና የተለመደ የአዘቦት ተግባር ወደመሆን ተሸጋግሯል፡፡ በዚህ የቀውስ አዙሪት ውስጥ ዋነኛው ገፈት ቀማሽ የአማራ ሕዝብ ቢሆንም የኦሮሞን ህዝብ ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የቀውስ አዙሪቱ ተጠቂ እና የግፍ ጽዋው ተቋዳሽ መሆናቸው አልቀረም፡፡

በሥራ ላይ ያለው ሀገር-አፍራሽ ሕገ-መንግስት እና አፓርታዳዊ የአስተዳደር መዋቅር ዋነኛ አርክቴክት እና አናጺ የሆነው አሸባሪው ትሕነግ በጦር ግንባር ተሸንፎ ትጥቅ ለመፍታት መፈረሙን ተከትሎ ፣ የሽብር ቡድኑ ይፋዊ አጋር የሆነው ኦነግ-ሸኔ እና በህቡዕ እና በይፋ ለቡድኑ ሥልታዊ እና ቀጥተኛ ድጋፍ ሲሰጡ የቆዩት የኦሮሚያ ክልልን የሚዘውሩ አንዳንድ ባለስልጣናት ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ የወደቁ ሲሆን ፣ በአዲስ አበባ እና በፌዴራል መንግስቱ ውስጥ ያለውን መዋቅራቸውን በማንቀሳቀስ በኦሮሚያ ክልል ፣ በአጎራባች ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ ቀውስ ለመፍጠር እና ሀገር ለማተራመስ የመጨረሻውን አቅማቸውን አሟጠው በመጠቀም ወደለየለት የሽብር ስራ ገብተዋል፡፡ በውጤቱም በበርካታ የወለጋ ዞኖች በአማራ ተዋላጆች ላይ እያሰለሱ ሲፈጽሙት የቆዩትን የዘር ማጥፋት ወንጀል የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ያደረጉ ሲሆን ፣ በፌዴራል መንግስት መዋቅሮች ውስጥ በየደረጃው በተቀመጡ አስፈጻሚወቻቸው በኩል በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል መዝሙር ዘምሩ እና የኦሮሚያን ባንዲራን አውለብልቡ የሚል የማተራመሻ ስልት ይዘው በመግባት፣ በህጻናትና በመምህራኖች ላይ ነውረኛ ጫና በመፍጠር አዲስ አበባ ከተማን የቀውስ ማዕከል ለማድረግ ያለ የሌለ አቅማቸውን አሟጠው እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡

በጫካ ያለውም ሆነ የመንግስት መዋቅርን የተቆጣጠረው ኦነግ-ሸኔ ወደ ለየለት የሽብር ተግባር ውስጥ ገብተው ንጹሃንን ዕለት በዕለት የሚጨፈጭፉት እና አዲስ አበባ ከተማ ድረስ ዘልቀው አዲስ የቀውስ ማዕከል ለመፍጠር እየተጣጣሩ ያሉት ፣ ተሸንፎ እጅ የሰጠውን የጥፋት አጋራቸውን እና አሸባሪውን ትሕነግ ከገባበት ቅርቃር ለማውጣት እና እነሱም የማይቀርላቸውን የሽንፈት ጽዋ ላለመጎንጨት የመጨረሻውን መንፈራገጥ እያደረጉ ለመሆኑ (The last kick of a dying horse) ማሳያ ከመሆን የሚያልፍ አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ አሸባሪው ኦነግ-ሸኔ እና የኦሮሚያ ክልልን የሚዘውሩት አንዳንድ ባለስልጣናት በአማራ ተወላጆች ላይ እየፈጸሙት ያሉት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፣ በኦሮሚያ ክልል እየፈጠሩት ያለው ፖለቲካዊ ምስቅልቅል እና አዲስ አበባን የቀውስ ማዕከል ለማድረግ እየሄዱበት ያለው እርቀት የሚያረጋግጠው የስብስቡን ጥንካሬ ሳይሆን ፣ በሥራ ላይ ያለው አፓርታዳዊ የአስተዳደር መዋቅር ለሽብርተኝነት እና ሽብርተኞች መደበቂያነት የተመቸ መዋቅር መሆኑን ፣ ሥርአቱ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለቀ እና ሊጠገን በማይችል ስብራት ላይ የሚገኝ መሆኑን ነው፡፡

ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የአማራ ሕዝብ ላይ የኅልውና አደጋ የደቀኑትን የፖለቲካ ኃይሎች ነጥሎ ሲታገል የቆየ ሲሆን ፣ ይህን የትግል መስመር አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ፓርቲያችን አብን የአማራ ሕዝብ የተደቀነበትን የኅልውና አደጋ ለመቀልበስ በሚችልበት የተሟላ አቋም ላይ እንደሚገኝ ይተማመናል! ሕዝባችን ሊሸነፉ አይችሉም የተባሉ ጠላቶቻችንን በአስደናቂ ተጋድሎ እያሸነፈ እና እጅ እያሰጠ በድል ግስጋሴ ላይ እንደሚገኝ ጠላትም ወዳጅም የሚውቀው ሃቅ ነው፡፡ ባልታጠቁ እና ራሳቸውን ለመከላከል በማይችሉ ህጻናት ፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች እና ሲቪል ወገኖቻችን ላይ በየእለቱ የሚፈጸመው ጭፍጨፋ እና እልቂት ሀዘን አጥንታችን ድረስ ዘልቆ ቢገባም ፣ እንደ ሕዝብ እየተፈጸመብን ያለው የማያባራ ጥቃት አንገታችንን አያስደፋንም! ለጠላቶቻችን እጅ አያሰጠንም! ኦነግ-ሸኔ እና በመንግስት የሲቪልና የጸጥታ መዋቅር ተሰግስገው በሕዝባችን ላይ ያለእረፍት ጭፍጨፋ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸሙ ያሉት እና አዲስ አበባ ከተማን የቀውስ ማዕከል ለማድረግ እየተውተረተሩ ያሉት ሽብርተኞች ምኞት እንደማይሳካ እና ሽንፈታቸው የማይቀር ለመሆኑ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል፡፡ 

ፓርቲችን አብን ለመላው የአማራ ሕዝብ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ አንድነቱን እንዲያጠናክር ጥሪውን እያስተላለፈ ፣ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በግፍ እየተጠቃ ካለው የአማራ ሕዝብ ጎን እንድትሰለፉ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ ድል ለአማራ ሕዝብ! ድል ለሀገራችን ኢትዮጵያ! 

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
አዲስ አበባ ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
ሕዳር 30 ቀን 2015