Get Mystery Box with random crypto!

#ሰበር ዜና# ከ25 በላይ አርሶ አደሮች በኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተሰማ! በኦሮ | Voice of Amhara የአማራ ድምጽ ®

#ሰበር ዜና#

ከ25 በላይ አርሶ አደሮች በኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተሰማ!

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ሳሲጋ ወረዳ አዝመራ ስብሰባ ላይ የነበሩ ከ25 በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮች በኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የአይን እማኞች ለአማራ ድምፅ ገለፁ።

በሳሲጋ ወረዳ ልዩ ስሙ ሃያ አራት ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች ህዳር 27/2015 ዓ/ም በከፈቱት ጥቃት አዝመራ ስብሰባ ላይ የነበሩ ከ25 በላይ የአማራ ተወላጆችን መገደላቸውን ነው ከጥቃቱ የተረፉ የአይን እማኞች ለአማራ ድምፅ ያረጋገጡት።

የፀጥታ ኃይሎቹ ህዳር 24/2015 ዓ/ም ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ በሃያ አራት ቀበሌ ማሳ ለማሳ እየዞሩ ፋኖ ያለበትን ለምን አልጠቆማችሁንም በሚል አዝመራ ሲሰበስቡ የነበሩ አርሶ አደሮችን ከሰበሰቧቸው ቦኋላ በስለት እንደገደሏቸው ነው ከጥቃቱ የተረፉ የአይን እማኞቹ የገለፁት።

የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች አርሶ አደሮችን ከገደሉ ቦኋላ አስከሬናቸው በየማሳው የጣሉት ሲሆን ከቀናት ቦኋላ የዘጠኙ ሟቾች አስከሬን ተገኝቶ ዛሬ ህዳር 30/2015 ዓ/ም ስርአተ ቀብራቸው ተፈፅሟል።

ከሟቾቹ መካከል፦
እንድሪስ አህመድ፣
በለጠ እንድሪስ፣
ጀማል አህመድ፣
ጀማል ሁሴን የተባሉ የአንድ ቤተሰብ አባላት ይገኙበታል የተባለ ሲሆን ሌሎች በጉልበት ስራ የተሰማሩ ወጣቶች እና በአዝመራ ስብሰባ ስራ ላይ ለነበሩ ቤተሰቦቻቸው ምግብ ለማድረስ የሄዱ ታዳጊዎችም እንዳሉበት የአይን እማኞቹ ለአማራ ድምፅ ገልፀዋል።

ከአንድ አከባቢ ብቻ አዝመራ ስብሰባ ላይ እንዳሉ የተገደሉት የአማራ ተወላጅ የ25 አርሶ አደሮች ናቸው ሲሉ ለአማራ ድምፅ የገለፁት የአይን እማኞቹ፡የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች በሃያ አራት ቀበሌ ስር በሚገኙ ሌሎች አከባቢዎችም የገደሏቸውን አርሶ አደሮች አስከሬናቸውን በፓትሮል ጭነው ወዳልታወቀ ስፍራ እንደወሰዱትም ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ኃይሎች በተለይ ከህዳር 9/2015 ዓ/ም ጀምሮ በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ፣ጊዳ፣ሳሲጋ በተባሉ ወረዳዎች እንዲሁም በሆሮ ጉድሩ ወለጋ አሙሩ፣ጃርጄጋ ጃርቴ፣ሆሮ ቡሉቅ በተባሉ ወረዳዎች ስር በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ 300 የሚደርሱ የአማራ ተወላጆች እንደተገደሉ የአማራ ድምፅ ሚድያ የአይን እማኞችን በማነጋገር በተለያየ ግዜ በሰራው ዘገባ አረጋግጧል።

    (የአማራ ድምፅ)