2020-06-03 16:35:53
ስቅ! ስቅ! ስቅ! እምፍ! የሚል ቀጭን የሴት ለቅሶ ሰማሁ። የጆሮዬን መግላሊት እያዟዟርኩ ከወዴት እንደሆነ ለማወቅ ሞከርኩ።
ድምጹን እየተከተልኩ ስራመድ እንባዋን እንደነጠላ አጣፍታ ከለበሰች ሴት ጋር ተገጣጠምኩ ። ኩርምትምት ብላ ግድግዳው ስር ተወሽቃለች። ባንድ እጇ ምላጭ ይዛለች። ሌላኛው እጇ እየደማ ነው። ደም ስሯን ልትቆርጥ ስትል
እንደደረስኩባት ገባኝ። ደነገጥኩ። በፍጥነት ምላጩን ቀማኋት።
<<ምን ሁነሽ ነው?>> አፈጠጥኩባት
ዝም ብላኝ ለቅሶዋን ቀጠለች
<<….ምንድን ነው? በፈጣሪ!>>
<<….ተወኝ….አይገባህም…>>
<<ምንድን ነው እሱ?>>
<<አይገባህም አልኩህኮ>> አለችና አቀረቀረች።
በድንጋጤ አይኖቼን አፍጥጬ አያታለሁ።
ድንገት ቀጥ ብላ
<< እባክህ መጠጥ ግዛልኝ። መስከር እፈልጋለሁ!>> አለችኝ። ይህች ሴት <<ቤቴልሄም>> ናት። የምሰራበት መስሪያ ቤት ውስጥ በተላላኪነት ትሰራለች። በሚገርም ሁኔታ ከተቀጠርኩ
አንስቶ ሰላም ብያት እንኳ አላውቅም። ከስራ የመውጫ ሰአት ደርሶ ልወጣ ስል ነው እንዲህ ባንዱ ኮሪደር ስር ተሸርኩታ ያገኘኋት።
ቢሮ ውስጥ የነበሩትን ሁሉ ጠርቼ ተረባርበው ወደ ቤቷ ወሰዷት። ከዚያ በኋላ ለአንድ ወር አላየኋትም። ከስራ ቀረች። እኔ ደግሞ ወሩን ሙሉ ሳስባት ቆየሁ። ምን ነክቷት ይሆን እያልኩ።
ከወር በኋላ ስትመጣ ቢሮዬ አስጠራኋት።
<<ዛሬ እንዴት ነው መጠጣት ትፈልጊያለሽ>> አልኳት
<<አዎ>> አለችኝ።አንድ ሰአት እንድንገናኝ ቀጠርኳት። ስንገናኝ ከሰላምታ ውጭ ማውራት ከበደኝ። ራሱን ሊያጠፋ የነበረ ሰው ስለ ምን ሊወራ ይችላል። ዝም ተባባልን። ዝምታውን ተከትሎ ብዙ ቢራ ጠጣች! ጠጣች….ጠጣች…ጠጣች…..! ዝርክርክ አለች።
<<ምን ሁነሽ ነው ግን?>> አልኳት እንደምንም ተደፋፍሬ። ፊትለፊት የወደቀ ሎተሪ ነበር። ቢራ ተደፍቶበት በስብሷል። በጣቷ ወደሱ እየጠቆመች
<<….ልክ እንደዚህኮ ነው የተወኝ!>> አለችኝ
<<ማን ነው እሱ?>>
<<ቢንያም ነዋ! ሁለት አመት ሙሉ ፍቅሬን እንዲቀበለኝ ተንበርክኬ የለመንኩት ቢንያም!>>
<<እና ሁለት አመት ሙሉ እንቢ ካለሽ ምንድን ነው እንዳዲስ ያናደደሽ አልኳት>>
<<እንደምንም ቆጠረኝ። ካፌ ውስጥ ያ ሁሉ ሰው በተሰበሰበበት…ውሀ ደፋብኝ! < አልፈልግሽም ማለት አይገባሽም!!! ያምሻል?? እብድ ከሆንሽ ለምን ሆስፒታል አትሄጂም? በቃ ባንቺ ምክንያት እንደፈለኩ መንቀሳቀስ አልችልም ማለት ነው?> እያለ ጮኸብኝ። ያ ሁሉ
ሰው በተሰበሰበት አሸማቀቀኝ…አሁን አፈቅርሀለሁ መባል ውሀ ያስረጫል?>>
<<አያስረጭም!>> አልኩ። ከኛ ወንበር አለፍ ብሎ የተቀመጠው ሰው ስለምን እያወራን እንደሆነ ለማጣራት ጆሮውን ሲያቆም ይታየኛል።
<< ሴት ልጅ ክብሯን ትታ ወንድ ልጅን ለመነች ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?>>
<<አላውቅም!>> የቀረበልኝን ከአልኮል ነጻ መጠጥ እየተጎነጨሁ።
<<አዎ አታውቅም! አንተ ብቻ አይደለህም ብዙ ወንዶች አያውቁም>> በረጅሙ ተነፈሰችና በርበሬ የመሰለውን አይኗን አፈጠጠችብኝ
<<ለመሆኑ አንተ ለመልክህ ትጨነቃለህ? ጠዋት ስትነሳ ቆንጆ አይደለሁም የሚል ሀሳብ ይይዝሀል?>>
<<አይዘኝም>> መልኬን ያን ያህል ገምግሜው አላውቅም።
<<እኔ ግን እጨነቃለሁ። ቆንጆ አለመሆኔ ያስቆጨኛል። ገና ከት/ቤት ጀምሬ ወንድ ጠይቄ እንጂ ተጠይቄ አላውቅም። ለምን? ምክንያቱም ቆንጆ አይደለሁም። አንተ ወንድ ነህ። ለመኖር ጠንክሮ መስራት ብቻ ነው የሚጠበቅብህ። እኔ ግን በተፈጥሮ ቆንጆ መሆን አለብኝ። ቆንጆ ካልሆንኩ ሰዎች ብቃቴን አይተው ሊያደንቁኝ አይችሉም። ፊታቸውን ከእኔ
ያዞራሉ…ተፈላጊነት አይኖረኝም >>
የተናገረችውን ሳስበው ትክክል መሰለኝ። ሴት ልጅ የተዋበ ፊት ፣ ማራኪ ወገብ አልያም የሚያሻፍድ ዳሌ ከሌላት በብዙ መስክ ስኬታማነቷ ይቀንሳል። በሆነ ጉዳይ ላይ ብቃት ያላት ሴት በመልኳ የምትሳቀቅ ከሆነ ከሚዲያ መሸሿ አይቀሬ ነው። ጥሩ የትወና ብቃት እያላት
ቦዘኔ ልትሆን ትችላለች። ምርጥ ገጣሚ ሁና ሳለ ከመድረክ ልትሸሽ ትችላለች።
<<ለምን እንደሱ ትያለሽ? አሁን ብዙዎቹ አትሌቶች መልካቸው ከዚህ ግባ የሚባል ሁኖ,ነው? ስራቸው ነው ያስከበራቸው!>> አልኳት የግዴን።
<<…ልታጽናናኝ አትሞክር…ቁንጅና ለወንዶች ቅንጦት ለሴቶች ደግሞ እንጀራ ነው። እንጀራ ብቻ አይደለም ክንድ ነው። የሀይስኩል ተማሪ እያለሁ ጓደኞቼ የፍቅር ደብዳቤ እየደረሳቸው ሲዝናኑ እኔ ግን ሰላምታ እንኳን አይደርሰኝም። ታምነኛለህ? እስካሁን አንድ ሰው እንኳ
<እወድሻለሁ> ብሎኝ አያውቅም። ለምን ይለኛል? ደብዳቤ ቢጽፍልኝስ ምን
ይለኛል?..ፊትሽ ጨረቃ ነው ሊለኝ?..
ሃሃሃሃሃሃ>> ሳቋ የሚያስበረግግግ ነበር።
ከዚህች ሴት ጋር በንደዚህ አይነት ሁኔታ ማውራቴ ትንሽ አስፈራኝ።
የተንጨባረረ ጸጉርና የሚያሳቅቅ አለባበሷን ሳስተውል <አብዳ ይሆን እንዴ> ብዬ አሰብኩ…ብቻ ፈራኋት።
አስተናጋጁን ጠርቼ ሂሳብ ከፈልኩ።
ልነሳ ስል <<በናትህ…ልለምንህ…በሆነ ነገር እርዳኝ?>>አለችኝ እየተለማመጠች።
<<ምን ልርዳሽ>>
<< በቃ እኔም እንደሴቶቹ መለመን እፈልጋለሁ። ገብቶሀል ኣ? ወንድ ቀጥሮኝ መቅረት ፣ ሲደወልልኝ እየዘጋሁ ማንገላታት፣ የኔ ፍቅር እባክሽ ብሎ ሲንበረከክ ትቼው መራመድ….እንደሴቶቹ መሆን እፈልጋለሁ።በቃ ከቻልክ>>አለችና ጸጥ አለች <<ከቻልኩ ምን?>>
<<ከዚህ ስሜት እስክወጣ ደውልልኝ>>
<<ደውዬስ?>>
<<አፈቅርሻለሁ እያልክ ለምነኝ። ትንሽ ልንቀባረርብህ…ለተወሰነ ጊዜ ብቻ! እባክህ ለተወሰነ ጊዜ ለምነኝና የሴትነት ወጉ ይሰማኝ>>
እብደቷ ስለገረመኝ እሺ አልልኳት። እና ብዙ ብዙ ነገር አወራችኝ። ላይዋ ላይ የሰፈረው የዝቅተኝነት ስሜት ብዙ እንደጎዳት አስተዋልኩ። እንግዲህ ከሰኞ እስከ አርብ እየደወልኩ እንድለምናት ነው የጠየቀችኝ። ከሰኞ እስከ አርብ አፍቃሪዋ ሁኜ እተውናለሁ። እሷም ቆንጆ እና ኩራተኛ ሴት ሁና ትንቀባረርብኛለች …ከዚያ ቅዳሜና እሁድ ከትወናው ወጥተን በትክክል እናወራለን። እንደዛ እንዲሆን ነው የጠየቀችኝ። ሃሃ እብድ ናት!።
….
ሰኞ እለት ደወልኩላት። እየገረመኝም ሳቄ እየመጣኝም እንደምንም እያፈንኩ ነው ያወራኋት።
<<እባክሽ የኔ ቆንጆ አውሪኝ…>>
<<አትጨቅጭቀኝ አልኩህ አይደል እንዴ?>>
<<…በጣምኮ ነው የምወድሽ…>>
<<እኔ ደግሞ አልፈልግህም አልኩኮ>> ኮስተር ያለ ድምጽ!
….
ረቡእ!
<<የኔ ማር…በምትወጂው ሁሉ እለምንሻለሁ>>
<<ውይይይይይ! አሁንስ አንተ ልጅ በጣም እያማረርከኝ ነው>> (አልዋሽም እንዲህ ስትለኝ
ሳቄ ለጥቂት ሊያመልጠኝ ነበር)
….
ሀሙስ<<ውዴ….አንቺኮ ማለት ለእኔ የልብ ትርታዬ ነሽ! ያላንቺኮ ምንም ነኝ>>
<<ለምት ትነዘንዘኛለህ? አንተ ደግሞ ለእኔ የልብ ድካሜ ነህ! ምን አይነቱ ነው?>> <በቃ
እብድ ነገር ናት> አልኩ በልቤ!!
…
እሁድ አንድ ካፌ ውስጥ ተቀምጠናል
<<ታውቂያለሽ ግን እብድ ነሽ!>> አልኳት
<<አንተ ደግሞ በጣም ቅን ሰው ነህ። ከልብ አመሰግናለሁ! ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ እያደረክ ነው። >> አለችኝ።
አንዳንድ ጊዜ ሳስበው ለማመን ይከብደኛል። ግን ሆነ። በዚህ ሁኔታ ከዚህች እብድ ልጅ ጋር ሁለት አመት ቀጠልን። በቃ እደውልላታለሁ። <<አፈቅርሻለሁ፣ እወድሻለሁ፣ ህይወቴ ነሽ>> ምናምን እላታለሁ (ራሷን ልታጠፋ የሞከረች ልጅ ማከሜ ነው በእኔ ቤት) እሷ ደግሞ አጸፋውን በኩራትና በቁጣ ተሞልታ ትመልሳለች። ቅዳሜ እና እሁድ ግን ራሳችንን ሁነን ስለሳምንቱ እያወራን እንዝናናለን። በዚህ ሁኔታ ተላመድን። መላመድ ክፉ ነገር ነው። እብደቷን ወደድኩት።
243 viewsedited 13:35