Get Mystery Box with random crypto!

ሳሙኤል ተመስጌን ወ/ሃና

የቴሌግራም ቻናል አርማ tsidq — ሳሙኤል ተመስጌን ወ/ሃና
የቴሌግራም ቻናል አርማ tsidq — ሳሙኤል ተመስጌን ወ/ሃና
የሰርጥ አድራሻ: @tsidq
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 1.86K
የሰርጥ መግለጫ

ቤተክርስቲያን ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ።

Ratings & Reviews

2.67

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

1

3 stars

1

2 stars

0

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 2

2023-01-07 04:39:28
529 views01:39
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-01-07 04:39:27 ሞት በትቢት እንደ ተጀመረ
ድህነት በትህትና ተጀመረ
ማንም ሊቀርበው በማይችል በብርሃናዊ ቦታ የሚኖር አምላክ እንደ ምስኪን ድሃ በበረት ተኛ
ይህን ያህል ትህትና እንደ ምን ያለ ትህትና ነው
ይህን ያህል ሰው መውድ እንደ ምን ያለ ነው
የእግዚአብሔር ልጅ ያደርገን ዘመን የሰው ልጅ ሆነ
ሰማያዊ እንሆናለን ዘንድ ወደ ምድር መጣ
491 views01:39
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-01-06 08:13:08 + የሕዝብ ቆጠራ መዝገብ +

ጌታችን በቤተልሔም ለመወለዱ ምክንያት የሆነው ለሕዝብ ቆጠራ ሲሉ ወደ ይሁዳ አውራጃ በመምጣታቸው ነበር:: ለቆጠራ መጥተው ከመቆጠራቸው በፊት ጌታችን ተወለደ:: ወደ ናዝሬት ከመመለሳቸው በፊት ግን ሁለት ሆነው ሊቆጠሩ የመጡበትን የሕዝብ ቆጠራ ሦስት ሆነው አድርገው ተቆጥረዋል::

እባካችሁ ያንን የቆጠራ መዝገብ ያለበትን ቦታ የምታውቁ የሮማውያን ታሪክ መርማሪዎች ካላችሁ ብትነግሩኝ ደስ ይለኛል:: ደግሞ የሕዝብ ቆጠራ መዝገብ ምን ያደርግልሃል? ካላችሁ መዝገቡ ይገኝ እንጂ እኔ ግን የምፈልገው አንድ ስም አለ:: ከብዙ የይሁዳ ተወላጆች ስም መካከል ሰሎሜ ዮሴፍ ማርያም ከሚሉ ስሞች አጠገብ አንድ ዓለም የዳነበት ስም በሕዝብ ቆጠራው መዝገብ ሥር ተጽፎአል::

ጉልበት ሁሉ የሚሰግድለት ስም : ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የተሠጠን ስም : ከስም በላይ የሆነ ስም : ቅዱስ ገብርኤል በክብር ይዞት የወረደና ለድንግሊቱ የነገራት ስም : አጋንንት ሲሰሙት የሚንቀጠቀጡለት ስም : ሙታንን የሚያስነሣ ድውያንን የሚፈውስ ስም በዚያ የሕዝብ ቆጠራ መዝገብ ላይ እንደዋዛ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል::

ኢየሱስ

አንተ የሕዝብ ቆጠራ ሠራተኛ ሆይ ይህንን ስም እዚያ መዝገብ ላይ ስትጽፈው ብዕርህ አልተሰበረም ወይ? ቀለሙስ አልሸሸም ወይ? እጆችህስ አልተንቀጠቀጡም ወይ?

ጌታችን በዚያ መዝገብ ላይ ተጻፈ:: በዚያ መዝገብ ከጌታ ጋር የተጻፉት ንጽሕት ድንግልና ጻድቁ ዮሴፍ ብቻ አልነበሩም:: በዚያች ግዛት ያሉ ሰዎች ሁሉ አብረው ተጽፈዋል:: ጥሩ ሰዎች ክፉ ሰዎች ወንጀለኞች ነፍሰ ገዳዮች ሰካራሞች አመንዝሮች በዚያ መዝገብ ላይ ስማቸው ተጽፎአል::

ክርስቶስም ገና ከመወለዱ ከኃጢአተኞች ጋር ተቆጠረ:: በሕይወት ዘመኑ የኃጢአተኞች ወዳጅ የሚል ቅጽል ስም የወጣለት ጌታ በዕለተ አርብም በግራና ቀኙ ከወንበዴዎች ጋር አብሮ የተሰቀለው ጌታ አሁንም በልደቱ ጊዜ "ከዓመፀኞች ጋር ተቆጠረ" (ኢሳ 53:12)

እኛን ከቅዱሳን ጋር ሊደምረን እሱ ከኃጢአተኞች ጋር ተቆጠረ:: እኛን "ስማችሁ በሰማይ ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ" ለማለት እርሱ በምድር መዝገብ ላይ ተጻፈ::

ወዳጄ ክርስቶስ ስለ አንተ ሲል ከኃጢአተኞች ጋር ተቆጠረ:: አንተ ስለ እርሱ ከንጹሐን ጋር ተቆጠርለት:: በተወለደበት ጊዜ ከሰካራሞችና ዘራፊዎች ስም ዝርዝር ጋር ለአንተ ሲል አብሮ ተቆጠረ:: እስቲ አንተ ልደቱን አስበህ ከሚሰክሩት ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ውጣ:: ከዘራፊዎችም መካከል ተለይ:: ክርስቶስ ወደ አንድ ነገር የሚገባው የሚገቡትን ሊያወጣ ነው:: ወደ ሞት የገባው ሙታንን ሊያወጣ ነው:: ወደ ሲኦል የወረደው ነፍሳትን ከሲኦል ሊያወጣ ነው:: ወደ ሮማውያን የሕዝብ ቆጠራ የኃጢአተኞች መዝገብ ስሙ የገባውም የሁላችንን በደል ተሸክሞ እኛን ከዚያ መዝገብ ሊያስወጣን ነው::

"ስማችሁ ግን በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ"
ሉቃ 10:20

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 28 2013 ዓ ም

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ!
550 views05:13
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-01-04 12:09:00 + ጌታ የተወለደው የት ነው? +

የገና ዋዜማ የት ልትሔድ አሰብህ? ምሽቱንስ የት ልታሳልፍ ነው? የትኛው ሆቴል? የትኛው የሙዚቃ ድግስ? "የገናን በዓል አስመልክቶ የተዘጋጀ ልዩ የሙዚቃ ድግስ" ላይ ጌታ የለም:: ባለ ልደቱ ጌታ የት ነው ያለው? አድራሻው ከጠፋብህ የተወለደ ዕለት የሆነውን ልንገርህ!

የተወለደውን ክርስቶስ ለማየት ብዙ ሀገራትን አልፈው ተጉዘው የመጡት ሰብአ ሰገል በኮከብ ተመርተው ነበር::
ለእስራኤላውያን እረኞች በታሪካቸው ውስጥ በሚያውቁአቸውና በለመዱአቸው መላእክት ልደቱን የገለጠው አምላክ ኮከብ ሲቆጥሩና ሲጠነቁሉ ለኖሩት ሰብአ ሰገል ደግሞ በሚያውቁት ኮከብ መራቸው::
ሕጻኑ ክርስቶስ ገና ከመወለዱ ብዙ እንደ ጣዖት የሚመለኩ ነገሮችን ድል አድራጊ መሆኑን አሳየ::

በሲና በረሃ እስራኤል ጥጃን አምላክ ብለው በወርቅ ጣዖት ሠርተው ነበር:: በቤተልሔም ጥጃ ትንፋሹን ለክርስቶስ በመገበር አምላኬ እርሱ ነው ሲል መሰከረለት:: በሬም ገዢውን አወቀ ሕዝቤ ግን አላወቀኝም የሚለው ተፈጸመ:: ከዋክብትንና ፀሐይን ያመልኩ የነበሩን የዞረዳሸት (ዞራስትራኒዝም) ፍልስፍናን የሚያምኑ ሰብአ ሰገልም በሚያመልኩት ኮከብ ፈጣሪያቸውን አገኙ:: ቅዱስ ኤፍሬም እንዳለው "የሚያመልኳት ፀሐይም በሰብአ ሰገል ጉልበት ለፈጣሪዋ ሰገደች"

ኮከብ የሚወጣበት ጊዜ በዚያን ቀን የሰውን ዕጣ ፈንታ ይወስናል ብለው የሚያምኑም ብዙዎች ናቸው:: ይህ የሆነው በኮከቤ ምክንያት ነው! ኮከባችን አይገጥምም የሚባባሉ ብዙዎች ናቸው:: ይህ ሁሉ ባዕድ አምልኮ ነው:: ኤሳውና ያዕቆብ መንትዮች ናቸው:: የተወለዱት በአንድ ቀን ነው:: እነርሱ በተወለዱ ቀን የወጣው ኮከብም አንድ ነው:: "ኮከባቸው" አንድ ሆኖ ሳለ ምነው ነገራቸው ሁሉ አልገጥም አለ? ኮከባቸው ይገጥማል ምነው እነርሱ አልገጠሙም? ስለዚህ ሐሰት ነው::

የተወለደው ንጉሥ ግን ኮከቡ ዕጣ ፈንታውን የሚወስነው ሳይሆን ከዋክብትን በየስማቸው የሚጠራቸው በቁጥር የሚያውቃቸው ጌታ ነው:: እንደ ዮሴፍ 11 ከዋክብት ሐዋርያቱ ከይሁዳ በቀር የሰገዱለት እናቱ ማርያምም እንደ ያዕቆብ በልብዋ እያሰበች የተደነቀችበት የከዋክብት ጌታ የጨረቃ ንጉሥ የፀሐዮች ሁሉ ፀሐይ ነው እርሱ::

ሰብአ ሰገል መሪያቸው የነበረውን ኮከብ ሲያጡት ወደ ሔሮድስ መጡና "የተወለደው ንጉሥ ወዴት ነው?" አሉ::
እውነትም ጠቢባን ናቸው:: መንገድ ከጠፋብን : መሪ ኮከብ ካጣን ልደቱን የፈለግንበት እናክብር አላሉም:: የተወለደው ወዴት ነው? ብለው ቤተ መንግሥት ሔደው ጠየቁ:: ጥሩ በዓል ለማክበር ከቤተ መንግሥት የተሻለ ሥፍራ የለም:: በቤተ መንግሥት ራት እየበሉ ጮማ እየቆረጡ በዘፈን ታጅበው በዓሉን ማክበር ይችላሉ:: እነርሱ ግን የትም ቢሆን ንጉሡን ሳናገኝ አንቆይም:: እሱ የሌለበት ቦታ ቤተ መንግሥትም ቢሆን ልደቱን አናከብርም:: አይ ሰብአ ሰገል! ይህንን ዘመን መጥተው ቢያዩ ምን ይላሉ?

ወዳጄ አንተ የጌታን ልደት የት ታከብራለህ? መቼም
ልደት የሚከበረው ባለ ልደቱ ባለበት ሥፍራ ነው:: በእውነት የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በጭፈራ ቤት ነውን? በመጠጥ ቤት ነውን? የት ነው ያለው ብለህ ጠይቀሃል?

"የሚመራኝ ኮከብ የለም" ትል ይሆናል:: ምንም ቢሆን ግን ሕፃኑ በሌለበት ልደቱን ለማክበር መወሰን የለብህም:: ምንም ያሸበረቁ ሥፍራዎች ቢኖሩም እንዳትታለል:: የሔሮድስ ቤተመንግሥት ውበት የግብዣው ስፋት አታልሎህ የተወለደውን ንጉሥ እንዳያስረሳህ ተጠንቀቅ:: እሱ ከሌለበት ያማረ ሥፍራ ይልቅ እሱ ያለበት በረት ይሻልሃል:: እሱ ያልመረጠውን ሥፍራ መርጠህ ከመንገድ አትቅር:: "የተወለደው የአይሁድ ወዴት ነው" ብለህ ጠይቅ::

እሱ ደሃ ሆኖ ባለጠጋ የሚያደርግህን ንጉሥ በሚያልፍ ደስታ አትጣው:: በስካር በዝሙት በጭፈራ በሔሮድስ ቤተ መንግሥት ቀልጠህ ቀርተህ የተወለደውን ሕፃን ሳታየው አትቅር:: እሱ በተወለደባት ሌሊት አንተ ስትሞት አትደር:: እመነኝ የተወለደው ይሻልሃል ከሞቱት ጋር ጊዜህን አታጥፋ::

ሰብአ ሰገል "የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?" ብለው ለአይሁድ ንጉሥ ሔሮድስ ጠየቁት:: የአህያ ውኃ ጠጪው ሔሮድስ ክው ብሎ ቢደነግጥም ፈገግ ብሎ ላጣራላችሁ ቆይ ብሎ አቆያቸው:: መጽሐፍ አዋቂዎቹን ጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠሩ:: እነ ሊቄ መለሱ:: "እንደተነገረው ትንቢት ከሆነማ" አሉ ኩፍፍፍስ ብለው
"በይሁዳ ቤተልሔም ነው" ብለው የተወለደውን ንጉሥ አድራሻ ተናገሩ:: ሔሮድስ ከነተንኮሉ ለሰብአ ሰገል መልእክቱን አደረሰ:: ሰብአ ሰገልም ሔደው ለንጉሡ ሰግደው እጅ መንሻ አቀረቡ::

ሔሮድስን ትተን እስቲ የጸሐፍቱን ነገር ትንሽ እናስተውለው:: የተወለደውን ጌታ አድራሻ ጠቁመው ለሰብአ ሰገል መንገድ የመሩ እነርሱ ግን መንገድና እውነት ሕይወትም የሆነው ጌታ የተሰወረባቸውን የታወሩ መሪዎች በሽተኛ ሐኪሞች የተራቡ መጋቢዎችን እስቲ ልብ እንበላቸው:: "ጥሩምባ ነፊ ቀብር አይገኝም" ማለትስ አይሁድ ናቸው::

ሌላውን ወደ ጌታ እየመራ እርሱ ከጌታው የራቀ : የእርሱን ቃል ሰምተው ሰዎች ሲድኑ እርሱ በኃጢአት ቁስል የተወረሰ ስንት አይሁድ እለ? ቅዱስ አምብሮስ እንዳለው የኖህ መርከብ ሲሠራ ሚስማርና መዶሻ እያቀበለ የሠራ ነገር ግን ከጥፋት ውኃ ያልዳነ ስንት በየቤቱ አለ::

እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል ማለት ቀላል ነው:: እንደተጻፈው መኖር ግን ከባድ ነው:: ከመጽሐፍ ጥቅስ ማውጣት ቀላል ነው የሚጠቀስ ሕይወት መኖር ግን ከባድ ነው:: ወዳጄ ለብዙ ሰብአ ሰገሎች ስለተወለደው ንጉሥ ነግረሃል:: በአንተ ሕይወት ውስጥስ "የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?" ወይስ በአንተ ሕይወት ገና አልተወለደም? ወይስ እንደ እንግዶች ማደሪያ ቦታ የለም ብለህ መልሰኸዋል? ኸረ እኔ እንኩዋን የቆሸሸ ሕይወት ነው ያለኝ እሱ በእኔ አያድርም አትበል? እንደ በረት ብትሸት እንደ እንስሳ እየኖርህ ቢሆንም አትፍራ እርሱ አይጠየፍህም? ወደ ልብህ መለስ ብለህ እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ "በእኔ ሕይወት ውስጥ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?"

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 27 2012 ዓ ም
ሻሸመኔ ኢትዮጵያ
ተሻሽሎ የተጻፈ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ! በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)
676 views09:09
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-12-31 22:24:03 ለአንድ ሰው ሕይወቱን የሚለውጥ አስደሳች ዜና የመናገር ዕድል ቢሠጥህ ምን ይሰማሃል? መርዶ መንገር የሚያስጠላውን ያህል የምሥራች መናገር ደግሞ ያስደስታል::

በምድር ላይ ቅዱስ ገብርኤል ለድንግል ማርያም ያበሠራትን መልካም ዜና የሚወዳደር ዜና የለም:: ገብርኤል ለድንግል የነገራት ሰበር ዜና (breaking news) ሳይሆን ፈዋሽ ዜና (healing news) ነው:: የድንግሊቱን ብቻ ሳይሆን የመላውን ዓለም ሕይወት የሚለውጥ ዜና ለሰሜን (North) ለምሥራቅ (East) ለምዕራብ (West) ለደቡብ (South) የሚያስደስት ዜና (N- E - W- S) ነው::

የምሥራች የመናገር ዕድል ቢሠጥህ በእግርህ ከሆነ ትሮጣለህ:: በመኪናም ከሆንክ ትፈጥናለህ:: ክንፍ ቢኖርህና ብትበር ግን ደስ ይልሃል::

ቅዱስ ገብርኤል ግን ክንፍ በኖረኝ አይልም:: በብርሃናዊ ክንፎቹ እየበረረ ወደ ድንግሊቱ መጣ:: ይህን ዜና መናገር የፍጥረትን ታሪክ መለወጥ ነውና ለራሱ ለቅዱስ ገብርኤልም ከዚያች ዕለት የበለጠ ቀን የለም:: ቅዱስ አምብሮስ እንዳለው "ይህንን ዜና ይዤ ለምን እዘገያለሁ? ለምንስ እቆማለሁ? ለተመረጠችው ድንግል ልንገራት እንጂ" ብሎ ክንፎቹን እያማታ ወደ ገሊላ ናዝሬት ገሰገሰ::
መላእክትን ባለንበት እንጽና ብሎ ያረጋጋው መልአክ አሁን ይህንን ታላቅ የምሥራች እንዲሸከም ከመላእክት የተመረጠ ዕድለኛ መልአክ ነውና በደስታ ተሞልቶ ወደ ድንግሊቱ በረረ:: (ወበእንተዝ ደለዎ ከመ ይፁር ዜናሃ ለድንግል እንዲል)

ገብርኤል በድንግሊቱ ፊት ሲቆም የተለየ ነበር:: የባቢሎንን እሳት ያልፈራው ኃያሉ ገብርኤል በዓሥራ አምስት ዓመት ብላቴና ፊት አደግድጎ ሰላምታ ሲያቀርብ ተመልከቱት:: ለዘካርያስ ጥያቄ ካላመንህ ዲዳ ትሆናለህ ያለ ገብርኤል በድንግል ፊት ግን በትዕግሥትና ትሕትና ጥያቄዋን መለሰ::

የልጅ አዋቂዋ ድንግል ያለ ዘር ትጸንሻለሽ ሲላት እንደ አሮጊት እናትዋ ሣራ በመጠራጠር አልሳቀችም:: እግዚአብሔር ለሣራ ያለውን "ለእግዚአብሔር የሚሳነው የለም" የሚል ቃል ገብርኤል ለድንግል ሲደግምላት አሜን ብላ ተቀበለችው:: ሔዋን ለዕባብ እሺ ብላ ከገነት እንዳስወጣችን ድንግል ለገብርኤል እሺ ብላ ወደ ገነት መለሰችን:: ገብርኤል ይሁንታዋን ሲሰማ ከእርስዋ ሔደ:: ከመሔዱ በፊት ግን የላከውን አምላክ ቃልዋን ተከትሎ በማሕፀንዋ ሲያድር አይቶ ተደንቆ ከእርስዋ ሔደ:: ደስተኛው ገብርኤል ሆይ እኛም በክፉ ዜና አዝነናል:: በሰበር ዜና ተሰባብረናልና ቃልህን አሰማን::

ኦ ገብርኤል ናዝዘነ ወአስምዓነ ቃለከ

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 22 2013 ዓ ም
አዲስ አበባ

ፎቶ :- ናዝሬት ገሊላ እመቤታችንን ያበሠረበት ሥፍራ
577 views19:24
ክፈት / አስተያየት ይስጡ