Get Mystery Box with random crypto!

'እናቴ ማርያምን ባሰብኳት ጊዜ አለቀስኩ' አንድ ወቅት ላይ ነበር ይህን ከላይ የምትመለከቱት | ማኅሌት ሚዲያ

"እናቴ ማርያምን ባሰብኳት ጊዜ አለቀስኩ"

አንድ ወቅት ላይ ነበር ይህን ከላይ የምትመለከቱትን ምስል በfacebook ገጽ ላይ ያገኘሁት ። ይህች እናት የልጇን መርፌ እርሷ የተወጋች እስኪ መስል ድረስ መሸማቀቋን ፊቷ ያሳብቃል ። ይህን ስሜት ለመረዳት ሞኮርኩ ግን አልቻልኩም እናት መሆን ካልቻሉ አይረዱትምና። ምስሉ ሳላስበው ልቦናዬን ወደ ቀራንዮ ወሰደውና የልጇን መከራ በአይኗ ትመለከት ስለነበር ስለ አንዲት እናት አሰብኩ ።

ያቺስ እናት በዚያን ጊዜ እንዴት ሆና ይሆን!?


ልጇ..ሥጋን ከአጥንት በሚለይ ጅራፍ እየተገረፈ ስታይ የነበረችው ይህች እናት ልቧ ምን ያህል በሀዘን ጅራፍ ተገርፎ ይሆን!?

ልጇ...ጭንቅላትን የሚሰነጥቅ የእሾህ አክሊል በራሱ ላይ ተደርጎበት ስታይ የነበረችው ይህች እናት ምን ያህል ነፍሷ በሀዘን ተሰንጥቃ ይሆን!?

ልጇ...እጅና እግሩ በሚስማር ሲቸነከር የምታየው ይህች እናት ሚስማሩ ሲመታ ሰውነቷ እንዴት ተሸማቅቆ ይሆን! ?

ልጇ...በቀራንዮ አደባባይ ዕራቃኑን ሲሰቀል የምታየው ይህች እናት ኅሊናዋ በለቅሶ እንዴት ተሰቅሎ ይሆን?!

ልጇ...በመስቀል ላይ ተጠማሁ እያለ ሲጮህ የምታየው ይህች እናት አንጀቷ እንዴት ተንሰፍስፎ ይሆን?!

ህጻን ሳለ ልጇን ሄሮድስ እንዳይገልባት በግብጽ በረሀ ተንከራታ አስመልጣ ፣ እንዲህ የተቸገረችለት ልጇ እንደወንጀለኛ ሲሰቀል ያየችውን ፣ ስትወልድ ያላገኛት ምጥ ፣ ልጇ ሲሰቀል ግን የተሰቃየችው እናት ወደ ኋላ ተመልሼ አስተዋልኳትና

" እናቴ ማርያምን ባሰብኳት ጊዜ አለቀስኩ"

ዲ/ን ዘአማኑኤል ገዛኸኝ
2013 ዓ. ም
ሐዋሳ