Get Mystery Box with random crypto!

የችሎት ዜና ጋዜጠኞቹ መስከረም አበራና ጎበዜ ሲሳይን ጨምሮ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ | የዛሬ መረጃ ®

የችሎት ዜና
ጋዜጠኞቹ መስከረም አበራና ጎበዜ ሲሳይን ጨምሮ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ችሎት ለህዝብ ክፍት እንዲደረግ ታዘዘ

በአማራ ክልል ከልዩ ሀይል መፍረስና ፋኖን ትጥቅ ማስፈታት ጋር ተያይዞ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረዋል ተብለው ለእስር የተዳረጉ በአማራ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ምሁራን ዛሬ ሰኔ 5/2015 ዓ/ም ከሰዓት በኋላ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበዋል።
ችሎቱ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው አቃቤ ህግ በእያንዳንዳቸው ተከሳሾች ላይ በሬጅስትራር በኩል የተረጋገጠ ክስ እንዲያቀርብ ነበር።
ሆኖም አቃቤ ህግ የተረጋገጠ ክስ ለሬጅስትራር ሰጥቻለሁ ቢልም ሬጅስትራር ግን ሊደርስልኝ የቻለው የ13 ተከሳሽ ክስ ብቻ ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
በዚህም አቃቤ ህግ ባሉበትና በሌሉበት በሚል ክስ ከመሰረተባቸው 51 ተጠርጣሪዎች መካከል ለአስራ ሶስቱ የክስ ቻርጅ እንደተሰጣቸው ሮሃ ቲቪ በችሎት ተገኝታ ተከታትላለች።
በዚህ ላይ አስተያየት የሰጡት የተከሳሽ ጠበቆችም " የአስራ ሶስቱ ተከሳሾች ጉዳይ መታየት ይችላል ችግር የለብንም " ብለዋል።
ለችሎቱ የሰብዓዊ መብት አያያዛቸውን በተመለከተ ለችሎቱ አስተያየት የሰጡት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው በበኩላቸው " ዶክመንተሪ ተሰርቶብን ስማችን የጠፋ የፖለቲካ እስረኞች ስለሆንን  ችሎቱ ለቤተሰቦቻችን በተለይም ለአማራ ህዝብ ክፍት ተደርጎ በሰፊ አዳራሽ እንዲታይልን" ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በበኩሉ "ሌላ ቦታ የተሰደብነውና የተደበደብነው  ሳያንስ በችሎት አዳራሽ ፊት በፖሊሶች እንሰደባለን፣ ከጠበቆቻችን ጋር እንዳናወራ እንደረጋለን" ብሏል።
ዶ/ር መሰረት ቀለመወርቅ ደግሞ "የደረሰብንን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቅርበን ነበር አሁን ግን የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ወደ መደበኛ ችሎት ስለተቀየረ ምን ላይ እንዳለ አናውቅም ፣ ከምን እንደደረሰ ግልፅ ይደረግልን" ሲሉ ጠይቀዋል።
47ኛ ተከሳሽ ማስረሻ እንየው " በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ሰውነቴ ውስጥ የቀረ ጥይት አለ ፣እንዳልታከም ተደርጌያለሁ ፣በቀጠሮዬ ቀንም ህክምና እንዳልቀርብ ተደረወጌያለሁ፣ በዚህም ለ75 ቀናት ገላዬን እንኳን መታጠብ አልቻልኩም " ብሏል ለችሎቱ።
ችሎቱም ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይና ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው ላቀረቡት "ጉዳያችን በክፍት አዳራሽ ይታይ" ጥያቄ በሰጠው ምላሽ በቀጣይ ጉዳያቸው በትልቅ አዳራሽ እንዲታይና ለህዝብ ክፍት እንዲሆን አዟል።
በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ በኢሰመኮ  እንዲጣሩ ውሳኔ የተሰጠባቸውን መዝገቦች እኛ እናጣራለን ብሏል የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት።
ዶክመንተሪ ሰርተው ተጠርጣሪዎቹ በህግ ፊት ነፃ ሆኖ የመታየት መብታቸውን ያሳጡ የተባሉት የመንግስት ሚዲያዎች በስም የተጠሩ ሲሆን ፣ ይህንንም ጉዳይ እንደሚያጣራ ነው  ችሎቱ ያሳወቀው።
አቃቤ ህግ ግን "ዶክመንተሪ የሰራው የጋራ ግብረሃይሉ ነው እኔን አይመለከተኝም" ብሏል።
"ለአስራ ሶስቱ ተከሳሾች የቀረበው ክስና የሰነድ ማስረጃን በተመለከተ  ሃላፊነቱን የወሰደው አቃቤ ህግ ስምና ፊርማ የለም ፣ሃላፊነት የሚወስድ አካል ያስፈልጋል " ሲሉም የተከሳሽ ጠበቆች ጠይቀዋል።
አቃቤ ህግም" ሃላፊነቱን የሚወስደው ፍትህ ሚኒስቴር ነው ፣ የፍትህ ሚኒስቴር ማህተም እስካለ ድረስ ሃላፊነቱን የሚወስደው ተቋሙ ነው "የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዚህና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 9/2015 ቀጠሮ ሰጥቷል።

ሮሃ ሚዲያ ROHA MEDIA
@TodayNewsEthiopia