Get Mystery Box with random crypto!

እደመልእክት (ምለቃቸውን ስታነቡ ለሃሳቡ ብዬ ብቻ እደምፅፍ ተረዱልኝ፣ ምንም አይነት የፅሁፍ እውቀ | ትዝታዊ🐣

እደመልእክት (ምለቃቸውን ስታነቡ ለሃሳቡ ብዬ ብቻ እደምፅፍ ተረዱልኝ፣ ምንም አይነት የፅሁፍ እውቀትም የለኝም፣ፀሐፊም አደለሁም ለመሆንም አደለም)

*
"ደናግል ሆይ የሰማያዊ ሕይወት አርአያና አምሳል የሆነችው የድንግል ማርያም ሕይወት ይኑራችሁ። እርስዋ ለክርስቶስ እናት ለመሆን በምንም የምታንስ አልነበረችም " የሚለውን ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ስለ ድንግሊቱ ሕይወት እንዲህ ይላላል ፦ ". . ልቀጥል አልቀጥል ንባቤን በሚል ጥርጣሬ ፌቷን አጠናሁት . . እዳጨለመችው ዓይኖቿ ይሰልሉኛል . . .

"የማን መፅሐፍ ነው . .?"

"የዲያቆን ሄኖክ. . "

"እምም. . "

"ይብቃሽ. . "

"እስቲ ልስማው . . "

. . . "እግዚአብሔር ዳኛዋ እንዲሆንላት ትፀልይ ነበር እንጂ በወንዶች መታየትን አችሻም ነበር። ከቤት ለመውጣት አትቸኩልም ነበር። በሕዝባዊ ስፍራዎች የሚያውቃት ሰው አልነበረም።

ማር እንደምትሰራ ንብ በቤትዎ ውስጥ ብቻ መቆየትን ትመርጥ ነበር።በቤትዋ የቀረውን ሁሉ ለድሆች በቸርነት ትሰጥ ነበር። ቃላትዋ ጥንቃቄን የተሞላ ነበር . . ድምፅዋም የተመጠነ ነበር ። ጮኻ አትናገርም ነበር። ማንም ላይ ክፋ አልተናገረችም. . ."

"ኤጭ . . በቃሽ"

ምራቄ ትን አለኝ . . . ስቅታዬ አንቆኝ ለማውራት ሲያኮላትፈኝ የዶርማችንን በር በርግዳው ወጣች. .

#
. . ባገኙት አጋጣሚ ስለ ሃጥያቴ ይዘምራሉ. . . ቢራቢሮ ለመሆን የምዳክር ትንሽዬ አባጨጓሬ ነኝ . .. እጭነቴን ይጠሉታል. . . ለአስርት ዓመታት አልጋ ወዳጁ ያረጋት እናቴ እግርና እጆቿ እኛን ለፍተው ለማብላት እንቢ ሲሉ ሞፈሩን የተቀበልኩ የበኩር ልጅ ነኝ. . ሂወት ያልገባቸው በእኩል የተሰፉ እህቶች አሉኝ . . በአባት ተንቀን የተተፋን እንቁላሎች ነን. . . እንዳይሰበሩ ነው አስኳሉን ለማቀፍ የቅርፊቱን ድርሻ ያለመቻሌን ያህል የተሸከምኩት

አዎ አመንዝራ ነኝ . . የርሃብ ሰልፍን ለመበተን ቀሚሴን አይኔን ጨፍኜ ገልጫለው። ያልተቀጣው አውታታ ልጅ ነኝ ፣ ያልተገራው ገርጋሪ

ስትሰበር ለማይቆም ጊዜ ታድያ እኔ ምን ላርግ ?
በብር ስክተት ላይ እደቆሙ የወርቅ ምስሎች የተመሰለችዋን ሴት ሆኜ እዳልፀና ለእህቶቼ ዳቦ አይገዛልኝም ፣ ለእናቴ ለህመሟ መድሃኒት አይሸምትልኝም . . ውልቅ ውልቅ እደሚለው የበሬ ቀንበር መሆን የመረጥኩት በኔ መገዛት በርሃብ የማያለቅስ ቀጫጫ ነፍስ ለማቆየት ነው. . የሚለበልበኝን የምድር ሲኦል እያለፍኩ ነው ታድያ ስለማላውቀው የሰማይ ሲኦል ለምን ፈራለው ?

#
ላስቆጣት አስቤ አደለም ያነበብኩላት "ስለቅድስት ድንግል ማርያም ስሰማ ጨለማ ነፍሴ ትረካለች ስለምትለኝ " ላስደስታት ማሰቤ ነበር

እናቴን እሷ ውስጥ አያለው. . ቀኑ መጥለቅ ሲጀምር እራሷን መስታወት ፊት አቁማ ታሰናዳዋለች . . ከድና ያዘጋጀችልኝን እራት እድበላ እያስጠነቀቀችኝ በሩን ከውጭ ቆልፋብኝ ትፈተለካለች. . የጫማዋ ቋቋታ ከጆሮዬ እስኪደበቅ በመረበሽ ሸኛታለው . . . እነዛ የሰቀቀን ምሽቶች አሁን ድረስ በቁሜ ያቃዡኛል. . . ቆርቆሮውን ንፋስ ሲያንጫጫው ትንሽዬ ነፍሴ ትርዳለች . . የፍርሃት ቁር ያንተከትከኛል. . . ጥርሶቼ እያፏጩም ቢሆን የሆዴን የርሃብ ጥሪ ለመመለስ ማኘካቸውን አይተዉም . . .

ቅድስትም እንደ እናቴ በምሽት መብረር የለመደች የለሊቱ ወፍ ነች. . . የመረቀዘውን ሴትነታቸው እራሳቸው ብቻ ይታመሙታል. .

. . ዶርም ውስጥ ካለነው አምስት ሴቶች ውስጥ በእፍታ ያህል ነው ምትቀርበኝ. . ላውቃት አልጥርም. . . ብቻ እዲሁ ነፍሷ ያሳሳኛል
ልፈልጋት ልውጣ እንዴ ?

#
". . . ያን ምሽት በመቅለስለስ የጀመረው ዝናብ ፍጥነቱን ጨምሮ ዘንቦ ለመገላገል በሚመስል ሁኔታ የቤታችንን የቆርቆሮ ጣርያ ያናጋዋል. . . የታሰረልኝ የቀዘቀዘ ሽሮ በእንጀራ ላንቃዬ ላይ ተለጥፎ ፍርሃቴ ያማስለዋል. . . የእናቴን ጫማ ማይመስል ኮቴ ዝናቡ ከቆርቆሮ ጋር ከሚያደርገው ጩኽት ጋር እየታገለ ለጆሮዬ በትንሹ አንሾኳሾከ. . . እግሮቼ በእርጥበት ሲሞቁ ነበር እራሴ ላይ እደሸናው ያስተዋልኩት . . መሽናቴ አናዶኝ ይሁን ኮቴው አስፈርቶኝ እሪ ብዬ ማልቀስ ጀመርኩ . . እምባዬ ኮቴው ቆርቆሮ በሩን ገንጥሉ ለመግባት ውለታው ይሁን ? አላውቅም. .

በማላውቀው ቀን ስነቃ እጄ ላይ መርፌ ተሰክቶ ከወገቤ በታች በህመም እየተሰቃየው ነበር. . . እናቴን ፈለኩ የለችም. . እስካሁን እፈልጋታለው የለችም. . ምን አልባትም ለወደፊትም አትኖርም

ደግ ኡስታዝ ናቸው ከዛ አልጋ ከወረድኩ ጀምሮ ያሳደጉኝ . . "ጁዲ" አሉኝ . . መልካምነት ፣እዝነት ፣ ርህራሄ፣ ማለት ነው. . . ምን አልባት ያ ሁሉ የድንጋይ ቁስል ለዚህ ለመታጨት ይሆናል. . ምን አልባት ይሄ የኔ መንገድ ይሆናል . . .እደምታዬኝ ትላንቴን የረሳው ብፅእት አደለውም በማንነት ጥያቄ ምሰቃይ ቁስለኛ ነበርኩ. . . " የሆነ ቀን እኚ ደግ አባቴ የዝሁር ሰላት ከመስጅድ ሰግደው ሲመለሱ በፀሃይዋ እየተበላው ስተክዝ አገኙኝ . .

"የአላህ በርሃብ ገደልኩሽ " አሉኝ እየተንሰፈሰፉ

"ማነኝ ጋሼ ? ማነኝ ? "አልኳቸው የተበታተኑ ላባዎቿን እንደምትለቅም እርግብ እየቃጣኝ

በእጃቸው ከያዙት ቅዱስ ቁርዓን ውስጥ አንዲት ምዕራፍ ከፍተው አነበቡልኝ

" በረፋዱ እምላለሁ ፣ በሌሊቱም ÷ ፀጥ ባለ ጊዜ፤ ጌታህ አላሰናበተህም ፤ አልጠላህምም። በመጨረሻይቱ( ዓለም ) ከመጀመርያይቱ ይልቅ ላንተ በላጭ ናት። ጌታህም ወደ ፊት ( ብዙ ስጦታ) በእርግጥ ይሰጥሃል ፤ ትደሰታለህም። የቲም ኾነህ አላገኘህምና አላስጠጋህምን ?(አስጠግቶሃል) የሳትክም ኾነህ አገኘህ ፣ መራህም". .

ላባዎቼን በሌላ ላባ ተክቼ ሙብረሬ ግድ ነበር ያረኩትም ይሄን ነው. .

#
አጠገቤ መታ ከደረጃው ድንጋይ ስትቀመጥ እዳላየ ተውኳት ፣ ሳልጠይቃት ስለራሷ ታወራኝ ነበር. . . ምድር ላይ ብቻዋን ያልተገፋች ሴት እደሆንኩ እዳስብ ፈልጋ ይሆናል. .

"ይቅር እባል ይሁን ?" እደመጣልኝ ጠየኳት

"በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ተኝተን ሳለ ባሉን የሰውነት ቀዳዳዎች ውስጥ ነፍሳት ማይገቡብን ፃድቅ ስለሆንን ይመስልሻል ?"

"እኔጃ "

"ሁላችንም የተጎናፀፍነው ነውር አለ . . በጉልበታችን ተንበርክከን በግንባራችን በመደፋት "ማረን" ምንለው. . . ስለማደፋችን የማይፀየፈን ፣ ስለደጋገምነው ጥፋት ይቅር ማለት ማይደከመው አምላክ ከሰማይ አለ. . . መፅሐፈ መቃብያን ሣልስ ላይ. . 'የወደደኝን እወደዋለሁ ፤ ያከበረኝንም አከብረዋለሁ ፣ ወደ እኔ የተመለሰውንም እጠብቀዋለሁ 'ብሎ የለ ታድያ ለምን ትፈርያለሽ ? "

"እኔጃ. . . ማይቆም ሃጥያት በምኑ ማረኝ ይላል ? እንደ ወፊቷ እምነት የለኝም ይመግበናል ብዬ ባዶ ሆዴን አልበርም፤ እንደ ዩሁዳ ሰነፍ ነኝ ዲናሩ ያስፈልገኛል ቃሉን እረግጬ ገላዬን ሸጣለው. . . "

"እስቲ ተመልከችኝ ?"

እየተረበሽኩ ተመለከትኳት. . . ሚያቅፉ አይኗች አሏት

"ዲናሩን በትኝው እጄን ያዢው አብረን እንለፈው ይሄን እሳት ? "

ለመጀመርያ ጊዜ ከአካሌ ላይ በሚፈሰው
ሰላማዊ ጠረን አፍንጫዬ እየሰከረ ነበር. .

*
እጇን ከእጄ ላይ ስታሳርፍ አንድ የአምላክን ተዓምር ውስጤ ያሰላስል ነበር

'ሁሉም ሰው አንድ መዳኛ ሰዋዊ መልኣክ አለው ! ጥሪውን ማዳመጥ ብቻ ነው !

/ትዝታ/

❀:✧๑♡๑✧
@tiztawe
@tiztaw
❀:✧๑♡๑✧