Get Mystery Box with random crypto!

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ዓመት ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉትን ቅድመ ዝግጅቶች ማጠናቀቁን አ | ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ዓመት ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉትን ቅድመ ዝግጅቶች ማጠናቀቁን አስታወቀ
....................................................

ሚያዝያ 04/2015ዓ.ም.(የትምህርት ሚኒስቴር) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ዓመት ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉትን ቅድመ ዝግጅቶች ማጠናቀቁን አስታውቋል ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና የዩኒቨርሲቲው ራስ-ገዝ መሆን የአካዳሚ፣ የአስተዳደር፣ የፋይናንስ እና የሰው ሀብት አስተዳደራ ላይ የመወሰን ነጻነት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ደግሞ ለቀጣይ የዩኒቨርሲቲው ሁለተናዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር ጣሰው ዩኒቨርሲቲው ሲመሰረት ከራስ-ገዝነት ሥልጣኑ ጋር መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን ከጊዜያት በኋላ በተለያዩ መንግሥታት ቀስ በቀስ የራስ-ገዝነት ሥልጣኑን እያጣ መጥቶ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተጠቁመዋል ።

ፕሮፌሰር ጣሰው ዩኒቨርሲቲው ከረዥም ዓመታት በኋላ ከቀጣይ አመት ጀምሮ የራስ-ገዝነት ሥልጣኑን ልያስመልሱለት የሚችሉ ውስጣዊ ቅድመ ዝግጅቶችን ላለፉት ሁለት አመታት ሲያደርግ መቆየቱንና በአሁኑ ወቅት ማጠናቀቁን ጠቅሰው ለአብነት ያክልም የዩኒቨርሲቲው የፋይናንስና የሰው ኃይል አደረጃጀት መመሪያ መዘጋጀቱን፣ በመመሪያ ላይ ከሠራተኞች ጋር ውይይት መደረጉንና በቀጣይ ለቦርድ ውሳኔ የሚቀርብ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በ14 ካምፓሶች 70 የቅድመ-ምረቃ እና 293 የድህረ-ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞችን እየሰጠ ይገኛል።