Get Mystery Box with random crypto!

በኢትዮጵያ የ2ኛ እና 3ተኛ ክፍል ተማሪዎች ከግማሽ በላዩ ማንበብ እንደማይችሉ ጥናት አመለከተ። | TIKVAH-MAGAZINE

በኢትዮጵያ የ2ኛ እና 3ተኛ ክፍል ተማሪዎች ከግማሽ በላዩ ማንበብ እንደማይችሉ ጥናት አመለከተ።

የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ንባብን መሠረት አድርጎ ባካሄደው ጥናት በኢትዮጵያ የሚገኙ የ2ኛ እና 3ኛ ክፍል ተማሪች #56_በመቶዎቹ ምንም ዓይነት ቃል ማንበብ እንደማይችሉ አመልክቷል።

  በጥናቱ ምን ያህል ተማሪዎች ተሳተፉ?

በዚህ ንባብን መሠረት ባደረገ ጥናት ከ9 ክልሎች የተወጣጡ ከ16 ሺህ በላይ ተማሪዎች በዘፈቀደ (Random sampling ) ተመልምለው ተሳትፈዋል። ተማሪዎቹ ከ401 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተመረጡ ናቸው።

  ጥናቱ እንዴት ተካሄደ?

በጥናቱ የተመለመሉት ተማሪዎቹ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተጻፉ 50 ቃላት ቀርበውላቸው ቃላቱን ያነቡ እንደሆነ ተጠይቀዋል።

በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በአፋርኛ፣ በሶማሊኛ፣ በሀዲይኛ፣ በወላይትኛ፣ በሲዳምኛ እና ቤንሻንጉል ውስጥ በሚነገረው በርታ ቋንቋ የሚማሩ ተማሪዎች በዚህ ጥናት ተሳትፈዋል።

ከጥናቱ የሚጠበቀውም ፊደልን የመለየት፣ ቃላት ወይም አጭር አንቀጽ የማንበብ እና የማድመጥ እና የመረዳት ችሎታቸውን መመዘን ነው።

የጥናቱ ውጤት ምን ያመለክታል?

- በጥናቱ ከተሳተፉት የ2ኛ እና 3ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 56 በመቶ የሚሆኑት አንድም ቃል ማንበብ አይችሉም።

- በጥናቱ ከተሳተፉ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ቢያንስ አንድ ቃል ማንበብ የሚችሉት 37 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። የተቀሩት 63 በመቶዎቹ አንድም ቃል ማንብብ የማይችሉ (Zero renderers) ናቸው።

- የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ 55 በመቶ የሚሆኑት ከየትኛውም ፊደል ጋር እንደማይተዋወቁ ጥናቱ ጠቁሟል።

- ጥናቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉ፤ በተለምዶ ታዳጊ የሚባሉ ክልሎች ላይ ትኩረት እንዲደረግ ምክረ ኃሳብ አስቀምጧል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ ጥናቶች ምን ያመለክታሉ?

- በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ በደቂቃ ቢያንስ 60፤ የ3ኛ ክፍል ተማሪ ደግሞ 90 ቃላትን እንዲያነብ ይጠበቃል።

- ከላይ በተነሳው ነጥብ መሠረት በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚማሩት የ2ኛ ክፍል ተማሪዎች ቢያንስ በደቂቃ 43 እንዲሁም የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች 53 ቃላትን እንዲያነቡ ይጠበቅ ነበር።

መረጃው የተወሰደው ከቢቢሲ አማርኛ ነው።

@tikvahethmagazine