Get Mystery Box with random crypto!

በቴሌብር ሱፐር አፕ መረጃ መለዋወጥ የሚያስችል ሥርዓት ተዋወቀ። ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌብር ሱፐር አ | TIKVAH-MAGAZINE

በቴሌብር ሱፐር አፕ መረጃ መለዋወጥ የሚያስችል ሥርዓት ተዋወቀ።

ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌብር ሱፐር አፕ መተግበሪያው ላይ የሚካተቱ ተጨማሪ አገልግሎቶችን በዛሬው ዕለት አስተዋውቋል።  በዛሬው ዕለት ካስተዋወቀው አገልግሎት አንዱ "ቴሌብር ኢንጌጅ" የተሰኘው አገልግሎት አንዱ ነው።

"ቴሌብር ኢንጌጅ" ሦስት መሰረታዊ ዓላማዎችን ለማሳካት የተጨመረ አገልግሎት መሆኑን የገለጹት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፥ ገንዘብ ማስተላለፍ፤ ማኅበራዊ ትስስር መፍጠርና ማጋራትን መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል።

ይህ አዲስ አገልግሎት በግለሰብም ሆነ በቢዝነስ ደንበኞች መካከል የተናጠል ወይም የቡድን የቀጥታ ውይይቶችን (online chat) ለማድረግ የሚያስችል ሲሆን የድምጽ፤ የፎቶ፤ የቪዲዮ፤ የፋይል መልዕክቶችን መላላክ ያስችላል።

በተጨማሪም በውይይት ወቅት ገንዘብ ማስተላለፍ የአየር ሰዓት መግዛትና መላክን ያካትታል። ከዚህም በተጨማሪ የተገልጋይ አካውንት መክፈት(ማስተካከል)፤ የጓደኝነት ጥያቄ ማቅረብ መቀበል በአዲሱ አገልግሎት የተካተቱ ናቸው።

በግሩፕ ውስጥ ሥጦታ መላላክን የሚያበረታታው "ሻሞ" የተሰኘ አገልግሎትም የተካተተ ሲሆን ለሰዎች ቀጥታ መሸልም ወይም እድለኛ ለሆኑ ሰዎች ሽልማት ማቅረብ ያስችላል።

ቴሌብር ኢንጌጅ የማኅበራዊ ሚዲያ ይሆን?

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አገልግሎቱን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት "አዲሱ አገልግሎት ከሶሻል ሚዲያ ያልተናነሰ ፊቸር ያለው ነገር ግን ስሻል ሚዲያን ለመተካት ሳይሆን የመጣው ዲጂታል ህይወትን ለማቅለል [ነው] " ሲሉ አስረድተዋል።

ዛሬ የተዋወቀው ሌላኛው አገልግሎት "የዴቨሎፐርስ ፖርታል" ምንድን ነው?

ኩባንያው "የዴቨሎፐርስ ፖርታል" የተሰኘ ሲስተሞችን ከቴሌብር ሱፐርአፕ ጋር ለማስተሳሰር (integrate) ያግዛል የተባለውን ሥርዓት አስተዋውቋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንደገለጹት አሁን ላይ ወደ 237 የንግድ ተቋማት እንዲሁም 108 የሚሆኑ የመንግስት አገልግሎቶች የክፍያ ሥርዓታቸውን ከቴሌብር ጋር ማስተሳሰራቸውን ጠቅሰው ይህ ግን በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም ሲስተሞችን ከቴሌብር ጋር ለማገናኘት ከ2 እስከ 3 ወራት ይፈጅ የነበረ ሲሆን አሁን ይፋ በተደረገው ሥርዓት ግን ተቋማት በሁለት እና በሦስት ቀናት ውስጥ ሥርዓታቸውን ከቴሌብር ሥርዓት ጋር ማስተሳሰር ይችላሉ ተብሏል።

የቴሌብር ሱፐር አፕን ከኢንተርኔት ክፍያ ነጻ (offline) መጠቀም ይቻላል?

የቴሌብር ሱፐር አፕ ከዚህ ቀደም ደንበኞች ሲጠቀሙ የነበሩትን አገልግሎቶች ጨምሮ አዲስ የተዋወቀውን አገልግሎት ያለምንም የኢንተርኔት ክፍያ መጠቀም ይችላሉ ተብሏል።

ይህም ኩባንያው ባለፉት ጊዜያት የራሱን የክላውድ መሰረተ ልማት በመዘርጋቱ "የራሳችንን ዳታ ራሳችን እንድንጠቀም አስችሎናል" ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።

ይህም ሌሎች የኢንተርኔት አገልግሎቶች ቢቋረጡ እንኳን አገልግሎት መስጠት ያስችለዋል ተብሏል።

የቴሌብር ቁጥራዊ መረጃዎች ምን ይላሉ?

- በሦስት ዓመት ውስጥ 44.5 ሚሊዮን ደንበኞችን ማፍራት ችሏል።

- በሦስት አመት ውስጥ 775 የገንዘብ ዝውውሮች የተደረጉ ሲሆን ከ2 ትሪሊየን ብር በላይ አንቀሳቅሷል።

- ዛሬ ላይ በቀን 5 ቢሊዮን ትራንዛክሽን ይፈጸምበታል።

@TikvahethMagazine