Get Mystery Box with random crypto!

ኮሜዲያን ያሬድ በ 1 ዓመት ቀላል እስራትና በ2 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወሰነ ኮሜዲ | TIKVAH-MAGAZINE

ኮሜዲያን ያሬድ በ 1 ዓመት ቀላል እስራትና በ2 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወሰነ

ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም (ልጅ ያሬድ) በተከሰበት የወንጀል ክስ በአንድ አመት ቀላል እስራት እና በሁለት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ውሳኔ ተላልፎበታል።

ተከሳሹ ጥፋተኛ ተብሎ ቅጣቱ የተላለፈበት በኮምፒዩተር የሚፈጸም ወንጀል ድንጋጌን መተላለፍ፣ የቤተክርስቲያንና የሰዎችን ክብርና መልካም ስም ማጉደፍ እንዲሁም የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት በሚሉ ተደራራቢ ክሶች ነው።

ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም የቀረበበት ክስ እንዲሻሻል የክስ መቃወሚያውን በጽሁፍ ያቀረበ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ በኩል ክሱ ሊሻሻል የሚችልበት የህግ አግባብ እንደሌለ ተጠቅሶ መልስ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሹ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ጥያቄ የህግ አግባብነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎታል።

ተከሳሹ የመከላከያ ማስረጃ አለኝ ማለቱን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ያቀረባቸውን የሰው መከላከያ ማስረጃዎችን ቃል አዳምጧል።

ተከሳሹ የሰው የመከላከያ ማስረጃ ያቀረበ ቢሆንም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል ባለመቻሉ እና በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸሙ በፍርድ ቤቱ በመረጋገጡ በዛሬው ቀጠሮ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶበታል።

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ህገመንግስታዊና በህገመንግስት ስርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ተከሳሹ ያቀረበውን አምስት የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን ይዟል።

ፍርድ ቤቱ በድርጊቱ የእርስ በእርስ ግጭት አለመፈጠሩንና ጉዳት አለመድረሱን ከግምት ውስጥ በማስገባት በዕርከን 6 መሰረት በአንድ ዓመት ቀላል እስራትና በሁለት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ከነሃሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን ጊዜ ታሳቢ እንዲያደርግ ታዟል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ መረጃው የኤፍ ቢ ሲ መሆኑን ይገልጻል።

@TikvahethMagazine