Get Mystery Box with random crypto!

ህጻናትን መሬት ላይ ሸፋፍኖ፣ አስተኝቶ መለመን ... የልመና ስልት ይሆን? በመዲናዋ ብዙ አይነት | TIKVAH-MAGAZINE

ህጻናትን መሬት ላይ ሸፋፍኖ፣ አስተኝቶ መለመን ... የልመና ስልት ይሆን?

በመዲናዋ ብዙ አይነት የልመና አይነቶችን እንመለከታለን። አንዳንዶቹ ልመናዎች ግን ህጻናትን ጭምር በመጠቀም የሚደረጉ በመሆናቸው ልብን ሰብሮ ምጽዋት ከመስጠት ባለፈ ጥያቄ ይጭራል።

በተለይ መገናኛ አካባቢ ህፃናትን አስተኝቶ መለመን መለመዱን ጥቆማውን ያደረሱን ቤተሰቦቻችን የገለጹ ሲሆን ጨቅላ ህፃን አስፓልት ላይ አስተኝቶ መለመን ለጤናም ሆነ ለሞራል የሚከብድ ነገር እንደሆነ ነው የጠቀሱት።

በዚህ ጉዳይ ላይ ቲክቫህ ኢትዮጵያ የአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናትጉዳዮች ቢሮን አነጋግሯል፦

ጉዳዩ እንደ ቢሮ በሚገባ ይታወቃል፤ ለኛም በጣም አሳሳቢ እና አስጨናቂ ጉዳይ ሲሉ በቢሮው የህጻናት መብት ደህንነት ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ አንዷለም ታፈሰ  ይገልጻሉ። ሆኖም ቢሮው ክልከላ የማድረግ ወይንም የህግ አግባብን ለመተግበር ግን ስልጣን እንደሌለው ነው ያነሱት።

ዳይሬክተሩ አክለውም "እየከፋ እየመጣ ያለው ልመናን በወንጀል ደረጃ አስቀምጦ ወይንም አላግባብ የሆነ የልመና ሂደቶችን ክልከላ ያስቀመጠበት ህግ ስለሌለን እነዚህን እናቶች ወጥታቸሁ አትለምኑም ማለት አንችልም" ሲሉ ተናግረዋል።

ለመሆኑ ህጻናቱን ለልመና ብለው የሚሰርቁት ለዚሁ ይሆን ?

እንደ ቢሮው መረጃ ልጅ ጠፋ ሚባሉ ነገሮችን በተደጋጋሚ እንደሚሰማና አንዱ ልጅ የሚጠፋበትም ምክንያትም ለገቢ ማስገኛ ዘዴ እነደሆነ ይጠቁማል፡፡

ለምሳሌ በ2014/15 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት 58 አካባቢ የሚሆኑ ልጅ የመጥፋት ኬዞች የተመዘገቡ ሲሆን ከዚህም ውስጥ በሁለት መንገድ ሕጻናቱን በመስረቅ ለገቢ ማስገኛ እንደተጠቀሟቸው ተገልጿል።

የመጀመሪያው ልጅን አግቶ ገንዘብ መደራደር አይነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አሁን እንደምናየው በተለያየ መንገድ ልጆቹን በመውሰድ ለልመና እንደሚጠቀሟቸው እንሰማለን፡፡

ቢሮው ችግሩን ለመቅረፍ የህግ ማዕቀፍ እያዘጋጀው ነው ብሏል።

የህጻናት መብት ደህንነት ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ አንዷለም ታፈሰ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር በኩል ይህንን ድረጊት በህግ ሊከለክል የሚችል (ሊያስቆም የሚችል) አዋጅ እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑንና ረቂቁ ማለቁን ጠቁመዋል።

ይህ አዋጅ ተተግብሮ ወደ ሥራ ከተገባ ትልቅ እፎይታ ይፈጥራል ብለው እንደሚያስቡ የገለጹት ዳይሬክተሩ አዋጅ ተግባራዊ እስከሚደረግ ድረስ ቢሮው መመሪያ ማዘጋጀቱን አንስተዋል።

ለመሆኑ መመሪያው ላይ ምን ተካቷል?

መመሪያው ህጻናትን የያዙ እናቶች ልጆቻቸውን የቀን ማቆያ ውስጥ ማዋል እንዲችሉ፤ ምቹ በሆነ ቦታ ላይ ህጻናቱን አድርገው የተለያዩ ገቢ ሚያስገኙ ስራዎቹን ሰርተው በመመለስ ህጻናቱን መልሰው ሊወስዱ የሚችሉበት አሰራር የሚዘረጋ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

መመሪያው ህጻናቱ ማቆያ ውስጥ ሲቆዩ ምን ምን አገልግሎቶችን ያገኛሉ? ምን አይነት ነገሮች ሊሟሉላቸው ይገባል? ምን አይነት ህጻናቶች ናቸው እዚህ ውስጥ ሚገቡት? የሚሉትን የሚመልስ ሲሆን አሁን ላይ ተጠናቆ የፍትህ ቢሮ የህግ አስተያየት ሰጥቶበት ለፋናንስ ቢሮ መላኩን አክለው ገልጸዋል።

ይህ ጎዳና ላይ ለሚለመንባቸው ህጻናት ብቻ ሳይሆን ልጆቻቸው አካል ጉደተኛ ሆነው ወተው መስራት ለማይችሉ፤ ልጆቻቸውን ብቻ ይዘው ቤት ውስጥ ለሚቀመጡ ወላጆች፤ በማረሚያ ቤት ውስጥ ልጆቻቸው ላሉ (በረጅም ጊዜ በማቆየት) ሁሉን ሊያቅፍ በሚችል መልኩ መመሪያው መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

ዳይሬክተሩ ልጆቻቸው በማቆያ ከሆኑ ወላጆቻቸው ገቢ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ጭምር ጎን ለጎን እያሰቡ መመሪያው መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

የእርሶስ ትዝብት ምንድን ነው?

@tikvahethmagazine