Get Mystery Box with random crypto!

#Update “ ከታገቱ ሚያዚያ 19/2016 ዓ/ም ሰባት ወራት ይሆናቸዋል። እንደቀላል ነገር በወ | TIKVAH-ETHIOPIA

#Update

“ ከታገቱ ሚያዚያ 19/2016 ዓ/ም ሰባት ወራት ይሆናቸዋል። እንደቀላል ነገር በወጡበት ቀሩ ” - የታጋች ባለቤት

ከ6 ወራት በፊት ወደ ባቱ (ዝዋይ) ለስራ ጉዳይ እየተጓዙ በታጣቂዎች ታገቱ ከተባሉ 6 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኞች መካከል 3ቱ ቢለቀቁም 3ቱ ግን እንዳልተለቀቁ ቤተሰቦቻቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም የሚችለውን ሁሉ እንደሞከረ ከ2 ሳምንታት በፊት ገልጾልን ነበር።

በወቅቱ #እንባ እየተናነቃቸው ቃላቸውን የሰጡን የአንዱ ታጋች እህት ፣ “ በስልክ እንኳን ‘አለሁ በሕይወት’ እንዲለን ድምጹን ያሰሙን። 2.8 ሚሊዮን ብር ተከፍሎ 3ቱ ሠራተኞች ግን ከእገታ አልተለቀቁም ” ማለታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጠው ቃል፣ “ ሠራተኞቹ የአገር ልማት ሥራ ላይ ሲደክሙ ነው ይሄ ችግር የደረሰባቸው። ግለሰቦቹን በማገት የሚመጣ ለውጥ የለም። በሰላም እንዲለቋቸው የሚል ጥሪ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ ” ነበር ያለው።

አሁንስ ምን አዲስ ነገር አለ ?

ከ3ቱ ታጋቾች መካከል የሁለት ልጆቻቸው አባት የታገተባቸው ወ/ሮ ቤተልሄም ገዛኸኝ ፥ ታጋቾቹ አሁንም እንዳልተለቀቁ ገልጸዋል።

ከባለቤታቸው በተጨማሪ አንድ የሁለት ልጃቸው እናት የሞቱባቸው አባትና አንድ ሁለት ቤተሰቦቹን የሚያስተምር ሠራተኞች እንደሚገኙበትና ከታገቱ ከ6 ወራት በላይ ቢያስቆጥሩም ፣ አሁንም ያሉበት እንደማይታወቅ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

በንግግራቸው መሀል #የሚያለቅሱት ወይዘሮ ቤተልሄም በሰጡት ቃል ፣ “ በሕይወቱ ስለመኖሩም እየተጠራጠርኩ ነው። ሁለቱ ልጆቹ በትምህርታቸው ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ደርሶባቸዋል። አንዷ ተመራቂ፣ አንዱ ማትሪክ ተፈታኝ ናቸው። እኔም የስኳርና የደም ግፊት ሕመምተኛ ነኝ ” ብለዋል።

ለመንግሥት ጭምር ባስተላለፉት መልዕክትም፣ “ ሞቷልም፣ አለም ቢባል እኮ አንድ ነገር ነው። እንዲህ አድርጉ የሚሉን ነገር ካለም ቢጠቁሙን መፍትሄ ነው” ብለው፣ “እንደ ቀላል ነገር በሀገራቸው ላይ ታግተው በወጡበት ቅርት ሲሉ ዝም ማለት በጣም ይከብዳልና ሁሉም ርብርብ ያድርጉልን ” ሲሉ ጠይቀዋል።

“ ከታገቱ ሚያዚያ 19 ቀን 2016 ዓ/ም 7 ወራት ይሆናቸዋል። እንደቀላል ነገር በወጡበት ቀሩ። እቃ እንኳን ሲጠፋ ዝም አይባልም እንኳን ሰው። እንደ ሰው ትኩረት ይሰጣቸው ” ሲሉም አክለው አሳስበዋል።

“ እንዲያው በእግዚአብሔር፣ በሁሉም ልጆች ባሏቸው አባቶች፣ እህት፣ ወንድም ባላቸው ሰዎች ሁሉ ስም ሁሉም ሰዎች እንደራሳቸው አይተው የሚችሉትን ነገር ሁሉ ይተባበሩን። ያጣሩ። ከእግዚአብሔር በታች ሰዎችን ነው የምለምነው ” ነው ያሉት።

#ThikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia