Get Mystery Box with random crypto!

' እውቀቱ ሳይኖራቸው ቤተክርስቲያንን ወክሎ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ማስተላለፍ አይገባም ' - ብፁዕ | TIKVAH-ETHIOPIA

" እውቀቱ ሳይኖራቸው ቤተክርስቲያንን ወክሎ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ማስተላለፍ አይገባም " - ብፁዕ አቡነ አብርሃም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፥ የዲጀታል ሚዲያ እና ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ የራሷን ሕግና መመሪያ እንደምታዘጋጅ አሳወቀች።

ይህ የተሰማው " ኦርቶዶክሳውያን ብዙኃን መገናኛ ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን " በሚል በቤተክርስቲያኗ የሕዝብ ግንኙነት መመሪያ በተዘጋጀ ሥልጠና ላይ ነው።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፥ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት እና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሐሰተኛ ወሬ ባለመቀበል እና ባለማስተላለፍ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

" ቤተክርስቲያንን ሳያውቁ ተገቢው ሙያና እውቀት ሳይኖራቸው የሃይማኖት አስተምህሮ ለማስተላለፍ እና በየማኅበራዊ ሚዲያው እና ዲጂታል ሚዲያው ለመንቀሳቀስ የሚሞክሩ አሉ " ሲሉ የጠቆሙት ብፁዕነታቸው " እውቀቱ ሳይኖራቸው ቤተክርስቲያንን ወክሎ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ማስተላለፍ አይገባም " ሲሉ አሳስበዋል።

" ማኅበራዊ ሚዲያውና ዲጀታል ሚዲያው  ከቤተክርስቲያን ይልቅ ለግለሰቦች እና ለቡድን ፍላጎቶች የመቆም ዝንባሌ በሰፊው ይታያል " ያሉ ሲሆን " ቅድሚያ ለቤተክርስቲያን መስጠት ይገባል ፤ ገንዘብ መስብሰብን ዓላማ ያደረገ የዲጂታል ሚዲያ እና ማኅበራዊ ሚዲያ ሥራ በመንፈሳዊ ቅኝት ያልተቃኘ በመሆኑ እርምት የሚሻ ነው " ሲሉ ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው በዲጂታል ሚዲያ እና ማኅበራዊ ሚዲያ የሚያገለግሉ እና የሚገለግሉ የቤተክርስቲኒቱ ልጆች ለቤተክርስቲያን ከማይጠቅሙ አጀንዳዎች ራሳቸውን እንዲያርቁ መክረዋል።

በዲጂታል ሚዲያና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በሕሙማን እና በቤተክርስቲያን ስም የሚከናወኑ ልመናዎች ለተባለው ዓላማ ስለመዋላቸው ማረጋገጥ ከእያንዳንዱ እርዳታ ሰጪ ይጠበቃል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በጣስ መልኩ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን እና ሥርዓተ አምልኮ በዲጂታል ሚዲያ የሚያስተላልፉ አገልጋዮች እና ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አስጠንቅቀዋል።

" በቀጣይ የዲጀታል ሚዲያና ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ የቤተክርስቲያኗ የራሷን ሕግና መመሪያ እንዲዘጋጅ ይደረጋል " ሲሉ አሳውቀዋል።

@tikvahethiopia