Get Mystery Box with random crypto!

' ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ ትራክተኖችና ማሽነሪዎችን እንዳናስገባ ተከልክለናል ' - አስመጪዎች ከባ | TIKVAH-ETHIOPIA

" ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ ትራክተኖችና ማሽነሪዎችን እንዳናስገባ ተከልክለናል " - አስመጪዎች

ከባድ ተሽከርካሪዎችን ፣ ትራክተሮችን እና ማሽነሪዎችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ አስመጪዎች ፣ መንግሥት ምንም ዓይነት መመርያ ሳያወጣ ማስገባት አትችሉም በመባላቸው በሥራቸው ላይ እንቅፋት መፈጠሩን ተናገሩ።

አስመጪዎቹ ይህን የተናገሩት ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃል ነው።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያለ ምንም በቂ ምክንያት " የመኪና ማስገቢያ ፈቃድ አልሰጣችሁም " እንዳላቸው ገልጸው ጉዳዩን ፦ 
- ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣
- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣
- ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለጉምሩክ ኮሚሽን በአካል ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ከዚህ በፊት በነዳጅ የሚሠሩ አውቶሞቢሎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መከልከሉን መስማታቸውን ያስታወሱት አስመጪዎቹ፣ አውቶሞቢሎች እንዳይገቡ የተከለከለበት ዋነኛ ምክንያት እንደ አማራጭ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሸከርካሪዎችን ማስገባት እንደሚቻል በማመን ነው ብለዋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከባድ ተሸከርካሪዎችንና ትራክተሮችን ማስገባት አትችሉም ካለ ከሳምንት በላይ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ቅሬታቸውን በአካል ሲያስረዱ፣ ተቋማቱም እንዲህ ዓይነት መመርያ አለመኖሩን እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።

ስለጉዳዩ ዝርዝር መረጃም የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤትን ጠይቁ መባላቸውን አመልክተዋል።

ክልከላው ሥራ ላይ እንቅፋት እንደፈጠረባቸውና የተለያዩ ተሽከርካሪዎችንም ሆነ ትራክተሮችን የሚሸጡ ነጋዴዎች ዋጋ ጨምረው በመሸጥ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

አስመጪዎቹ ፥ ከባድ ተሽከርካሪዎችና ትራክተሮችን ጨምሮ ሌሎች ተሽከርካሪዎች እንደ አውቶሞቢሎች በኤሌክትሪክ እንደማይሠሩ ተናግረው  " ችግሩን መንግሥት በአፋጣኝ በመረዳት ክልከላው ሊያነሳልን ይገባል  " ብለዋል፡፡

መንግሥት ከባድ ተሽከርካሪዎች ሆነ ትራክተሮች በመመርያ ቢከለክል በአገር የመጣ ጉዳይ መሆኑን በማመን ሌላ አማራጭ እንደሚፈልጉ የገለጹት አስመጪዎቹ ችግሩን የፈጠረው አንድ የመንግሥት ተቋም መሆኑ ሁኔታውን የተወሳሰበ እንዲሆን አድርጎታል በማለት አስረድተዋል።

ሪፖርተር ጋዜጣ ፥ ጉዳዩን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን በስልክ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ሳይሳካ እንደቀረ አመልክቷል። #ሪፖርተርጋዜጣ

@tikvahethiopia