Get Mystery Box with random crypto!

በነገሌ ቦረና ሞቷል ተብሎ የተለቀሰለት ግለሰብ ከ32 ዓመት በኋላ በሕይወት ተገኘ ይህ የሆነው በኢ | Tesfaab Teshome

በነገሌ ቦረና ሞቷል ተብሎ የተለቀሰለት ግለሰብ ከ32 ዓመት በኋላ በሕይወት ተገኘ
ይህ የሆነው በኢትዮጵያ፣ ነገሌ ቦረና፣ ጎብቻ ቀበሌ ውስጥ ነው።

ከ32 ዓመት በፊት ሞቷል ተብሎ ወዳጅ ዘመድ እርሙን ያወጣለት ሰው፣ 'አለሁ' ብሎ የቤተሰቦቹን ደጃፍ አንኳኳ።

ሞቷል ብለው በሐዘን እንባ የተራጩለት ልጃቸውን ያገኙ ቤተሰቦች፣ በደስታ አነቡ።

በሕይወት መኖሩን የሰሙ የጎብቻ ቀበሌ ነዋሪዎች ሁሉ የዜናውን እውነትነት ለማረጋገጥ ወደ ቤተሰቦቹ ቤት እየጎረፉ ነው።

ዲማ ዶዮ ቦሩ ይባላል። በነገሌ ቦረና ነው ነዋሪነቱ።

በ1982 ዓ.ም. በወቅቱ አገሪቱን ያስተዳድር የነበረው መንግሥት ለብሔራዊ ውትድርና በግዳጅ ተወሰደ።

ዲማ በአካባቢው ታጣቂዎች ተይዞ ሲወሰድ ቤተሰቦቹ በሐዘን ክፉኛ ተሰበሩ።

ዲማ፣ በወቅቱ አብረውት ከ100 የማያንሱ ወጣቶች ለጦርነት መወሰዳቸውን ያስታውሳል።

ከዚያም ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ከዘመተ በኋላ ቤተሰቦቹ የሰሙት ወሬ በሐዘን ማቅ እንዲለብሱ አደረጋቸው።

ወላጆቹ በነበረው ጦርነት ላይ ከእርሱ ጋር አብረው የዘመቱ መሞታቸውን፣ ዲማ ደግሞ መቁሰሉን ነበር የሰሙት።

በእርግጥ ልጃቸው ስለመሞቱ ከማንም ምንም ዓይነት ማረጋገጫ አላገኙም።

ዲማ በወታደርነት በግዳጅ እንዲዘምት ሲደረግ አላገባም፤ አልወለደም ነበር።

እናት የልጃቸውን ልጆች አለመሳማቸው ያንገበግባቸዋል።

ለዓመታት ድምፁ የጠፋው ዲማ ያፈራቸውን ንብረቶች፣ ከብቶች ቤተሰቡ ተከፋፈለ።

ይህ ሁሉ ከሆነ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ዲማ ቤተሰቦቹን ፈልጎ መጣ።

የእርሱ ወደ ቤተሰቡ መቀላቀል በብዙዎች ዘንድ እንደ ተዓምር ተቆጥሯል።

ወደ ዲማ ቤተሰቦች ዘንድ እየመጡ እንኳን ለቤትህ አበቃህ የሚሉ የቤተሰቡን ደስታ ከመጋራት ባሻገር ጥያቄም አላቸው።

ከ32 ዓመት በፊት አብረውት ዘምተው የነበሩ የአካባቢው ወጣቶች፣ ዛሬም በሕይወት ካሉ ለማረጋገጥ የሚፈልጉ መኖራቸውን የዲማ የወንድም ልጅ፣ ታሪ ካሀና ዶዮ ለቢቢሲ ተናግሯል።

"በየዕለቱ ሰዎች እየመጡ ስለቤተሰቦቻቸው ይጠይቁታል። አንዳንዱ 'ከአንተ ጋር ታፍሶ የተወሰደው ወንድሜን አይተኸዋል?' ይላል ሌላው ደግሞ ስለልጁ ይጠይቃል። በርካታ ሰው ነው በየዕለቱ የሚጎበኘው።"

ታሪ ዲማ ወደ ውትድርና ሲወሰድ ገና አልተወለደም ነበር።

"አባቴ የስምንት ዓመት ልጅ እያለ ነው እርሱ ወደ ጦር ሜዳ የዘመተው። አሁን እኔ 18 ዓመቴ ነው። ልክ እንደ ሁለተኛ አባቴ የማየው አጎቴን ስላገኘሁ ደስተኛ ነኝ። ይህ ተዓምር ነው። ለእኔም ለቤተሰቡም ተዓምር ነው።"

የዲማ እናት ሞቶ አፈር ያላለበሱትን ልጅ ሞቷል ብለው እርማቸውን ለማውጣት ተቸግረው ነበር።

"ሁሉም በቃ ሞቷል የእርሱን ነገር እርሺው ሲሉኝ እሺ አላልኩም ነበር። እንደ ሞተ አይሰማኝም ነበር፤ ይመጣል ብዬ አስብ ነበር" ይላሉ የዲማ ዶዮ እናት።

የዲማ እናት እርጅና ተጭኗቸዋል። ነገር ግን ልጃቸው ወደ ጦርነት የተወሰደ ዕለት የነበረውን ሁኔታ በትክክል ያስታውሳሉ።

"ስንት ዓመቱ እንደነበር አላስታውስም። ነገር ግን እድሜው ለሥራ ደርሶ ነበር። አብረን እየሄድን እያለ ነው መጥተው በጉልበት ነጥቀውኝ የወሰዱት።"

ከዚያ በኋላ ግን ከልጃቸው ቃል አልሰሙም። ይኸው ከ32 ዓመት በኋላ በራቸውን አንኳኩቶ መጣ።

"በጣም ደስተኞች ነን፤ እርሱ የመጣ ዕለት በደስታ ራሴን ስቼ ነበር። እንደ ዐይናችን ብሌን የምንሳሳለት ልጅ ነበር።"

ዲማ ለ32 ዓመታት የት ነበር?
ዲማ በአካባቢው ታጣቂዎች በ1982 ዓ.ም. ታፍሶ ከተወሰደ በኋላ ወደ ባሕር ዳር መላኩን ይናገራል።

ባሕር ዳር የተወሰደው ከተያዘ ከ18 ቀናት በኋላ እንደነበርም አይዘነጋም።

በተመደበበት ጦርነት ላይ በርካቶች ከፊቱ ሲረግፉ ተመልክቷል። ሌሎች ደግሞ እግራቸው በመራቸው ሸሽተዋል።

በጦርነቱ ላይ ዓመት ያህል ከተሳተፈ በኋላ፣ በመቁሰሉ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወሰደ።

"ሕክምና ተደርጎልኝ ከሆስፒታል ስወጣ ማንንም አላውቅም ነበር። እዚያ የነበሩ ሰዎች ከየት እንደመጣሁ ጠየቁኝ። ከነገርኳቸው በኋላ፣ በእረኝነት እንዳገለግል ወሰዱኝ" ይላል።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ሌላ ሰው ወደ ቤንች ማጂ ወስዶት በቤቱ እንዲያገለግል እንዳደረገው ያስረዳል።

ወደ ቤንች ማጂ በቤቱ አንዲያገለግል የወሰደው ግለሰብ፣ ቤተሰቦቹ የሉም በሚል ከማንም ጋር እንዳይገናኝ እንዳደረገው ይገልጻል።

"ደጋግመው 'ቤተሰቦችህ እዚያ የሉም። ተመልሰህ የምትገባበት የለም። ስለዚህ ወዴት ትሄዳለህ?' ይሉኝ ነበር።"

"እኔም ደጋግሜ 'ምንም እንኳ የምገባበት ቤተሰብ ባይኖረኝ የተወለድኩበት ስፍራ ሄጄ እዚያ ልኑር እላቸው ነበር" ሲል ለቢቢሲ አስረድቷል።

የዲማ ጩኸት ግን ሰሚ ጆሮ ሳያገኝ ቆየ።

"ማንም የተረዳኝ አልነበረም፤ ብቻ 'የሚሄድበት የለውም፤ ተኝቶ የእኛን ገንዘብ መብላት ብቻ' ይሉኝ ነበር።"

ዲማ በቤንች ማጂ ያሳለፈውን የብቸኝነት፣ ፍቅር ማጣት እና በሐዘን ያሳለፈውን ጊዜ ያስታውሳል።

"ቤተሰብ አልመሰረትኩም። እዚያ ትዳር መመስረት በባህሉ ምክንያት ለእኔ ከባድ ነበር" ይላል።

ዲማ በዘመድ አዝማድ ረሃብ፣ በወገን እጦት በተቆራመደባት ቤንች ማጂ በአንድ ፋብሪካ በጥበቃነት ተቀጥሮ መሥራት ቢጀምርም ወርሃዊ ደመወዝ እንደማይከፈለው ይናገራል።

"ምንም ክፍያ አላገኝም። እንዳልሞት ብቻ የዕለት ምግቤን ይሰጡኛል" ይላል።
ወደ ቤተሰቦቹ እንዴት ሊመጣ ቻለ?
ዲማ በፋብሪካ ዘበኝነት እየሰራ ያገኘው ጓደኛው ጋር የነበረው ንግግር ዛሬ ቤተሰቦቹን ለማግኘት እንዳበቃው ይመሰክራል።

ጓደኛው ሹፌር ሲሆን በተደጋጋሚም ወደ ቦረና ያቤሎ ለስራ ይንቀሳቀሳል።

"አንድ ቀን ዲማ የትውልድ ስፍራህ የት ነው? ብሎ ጠየቀኝ። የትውልድ ስፍራዬን እና የቤተሰቦቼን መኖርያ አካባቢ ስነግረው 'ያቤሎ ጓደኛ ስላለኝ እጠይቅልሃለሁ' አለኝ" ይላል።

ከዚያ በኋላ የሆነው ሁሉ ለዲማም ለቤተሰቦቹም ተዓምር ነው።

ያቤሎ ካለው የሹፌር ጓደኛው ወዳጅ፣ በስልክ ሁለት ሶስቴ ካወራ በኋላ፣ በነገሌ ቦረና የሚገኙ ቤተሰቦቹን አፈላልጎ አገናኘው።

"በፈጣሪ እርዳታ የቤተሰቦቼን ስልክ ቁጥር አገኘሁ" የሚለው ዲማ ተወልዶ ካደገበት ቀዬ ሲወጣ ወንድሙ ዲድ ዶዮ ሕጻን እንደነበር ያስታውሳል።

ዲድ እና ቀሪው ቤተሰብ ወንድማችሁ በሕይወት አለ የሚለውን ወሬ ሲሰሙ የደስታ ማእበል አጥለቀለቃቸው።

ነገር ግን ሽራፊ ጥርጣሬም ቢሆን አላጣቸውም

ስለዚህ የቤተሰቦቹን ስም እንዲሁም ሌሎች የሚያስታውሳቸውን ነገሮች እንዲዘረዝር ጠየቁት።

ዲማም የቤተሰቡን እና የጎሳውን ስም እንዲሁም ሌሎች የጋራ ትዝታዎቻቸውን ዘረዘረ።

ቤተሰቦቹ ካፈሯቸው ሰባት ልጆች መካከል ሶስተኛ የሆነው ዲማ በሕይወት መኖሩ በዚህ መልኩ ተረጋገጠ።

ከዚያ በኋላም ሹፌር ጓደኛው ይዞት አዲስ አበባ፣ ከዚያም ወደ ነገሌ ቦረና ወስዶ ከቤተሰቦቹ ጋር ቀላቀለው።

ዲድ ወንድሙ ዲማ በመንደራቸው የደረሰ እለት የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።

ሁሉም ፊቱ በእንባ ታጥቦ ነበር የሚለው ዲድ፣ ወላጆቹ ብቻ ሳይሆኑ ልጆቻቸው በደርግ ታፍሰው የተወሰዱባቸው እና እርማቸውን ያላወጡ ተሰባስበው ሊያዩት መጥተው ነበር ይላል።

ዲማ ደግሞ ተወልዶ ጥርስ የነቀለባት መንደር ተቀይራ ጠብቃዋለች።

"ያኔ ወደ ጦር ሜዳ ስሄድ ከብቶቻችን ብዙ ነበሩ። ከቤተሰቦቼ እና ዘመዶቼ ውጪ ልጅ ሆነን አብረን እንጫወት ከነበሩ መካከል አንዳቸውንም አላገኘሁም" ይላል።

ዲማ ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ አባቱ በሕይወት ነበሩ። ታላቅ ወንድሙ ቦሩ ዶዮም ወደ አስመራ ለጦርነት ተወስዶ ሞቷል መባሉን ያስታውሳል።