Get Mystery Box with random crypto!

#እንኳን_ለብርሃነ_ዕርገቱ_አደረሰን ✥ ✥ ✥ “ እስከ ቢታንያም አወጣቸው። እጆቹንም አንስቶ ባረካ | ✥መ/ር ምህረተአብ አሰፋ ፔጅ✣

#እንኳን_ለብርሃነ_ዕርገቱ_አደረሰን ✥ ✥ ✥
“ እስከ ቢታንያም አወጣቸው። እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው:: ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ፡፡ #ወደ_ሰማይም_ዐረገ :: እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ....”(ሉቃ.፳፬፡፵፰-፶፩ )


ምስባክ፦
ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ፤
ወእግዚእነ በቃለ ቀርን፤
ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ።

ዕርገት ማለት ወደ ላይ ከፍ ከፍ ማለት ሲሆን የመሬትን የስበት ኃይል የሚያሸንፍ ከፍታ ነው፡፡ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ያረገው የመሬት የስበት ኃይል ሳይገድበው ነው፡፡ የክርስቶስ ዕርገት ቀድሞ በትንቢት የተነገረ፤ በሚያምኑት ዘንድ በናፍቆት ሲጠበቅ የቆየ እና በራሱ በጌታችን የተሰበከ ነው፡፡
ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ ለሰላሳ ዘጠኝ ቀናት ያህል ለሐዋርያቱ በተለያየ ጊዜ እየተገለጠ ለአገልግሎት ሲያዘጋጃቸው እና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር እያስተማራቸው ከቆየ በኋላ በ፵ኛው ቀን በሐዋርያቱ ፊት ዐርጎል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው የጌታችንን ዓበይት በዓላት አንዱ ዕርገት ነው።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተነሣ በ፵ኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ ያረገበትም ቦታ ቢታንያ አጠገብ የሚገኘው ደብረ ዘይት የሚባለው ተራራ ነው። አሥራ አንዱ ሐዋርያትን እዚያ ድረስ ከወሰዳቸው በኋላ ባርኳቸው እያዩት ዐረገ። ደመና ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቀደመ ክብሩ፤ በመለኮታዊ ክብሩ ወደ ሰማይ ዐርጎ በአባቱ ቀኝ ተቀምጧል። ጌታችን ያረገውም በለበሰው ሥጋ በመሆኑ እና ለሁለተኛ ጊዜ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ ይህን ክብር እኛም እንድናገኝ ምሳሌ ሲሆነን ነው። "በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።" (ኤፌ . ፪፡፮)

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዕርገቱ አስመልክቶ ከተናገራቸው ሦስት ነገሮች ውስጥ፦
✥ የመጀመሪያው፤ "እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።" (ዮሐ .፲፪፡፴፪)
✥ ሁለተኛው ደግሞ፤ "ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።"(ዮሐ.፲፬፡፲፰)
✥ ሶስተኛው፤ "እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።" (ዮሐ .፲፮፡፯)

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ለእኛ ትልቅ ተስፋ ነው ስለዚህም ሐዋርያት ጌታችን ሲያርግ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ይመለከቱት እንደነበር እኛም በታላቅ ተስፋ የጌታን ነገር ልናስብ ይገባል። ነቢዩ ዳንኤል ስለ ጌታችን ዕርገት እና በአብ ቀኝ ስለመቀመጡ እንዲህ ሲል በትንቢት ተናግሮ ነበር፤ "በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።" (ዳን.፯፡፲፫ - ፲፬) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ በአብ ቀኝ ተቀመጠ ስንል ጌታ ከአብ ጋር እኩል ነው ማለታችን ነው።
ከ፬ቱ ወንጌላውያን ውስጥ ይህን የዕርገቱን ታሪክ የመዘገቡት ቅዱስ ማርቆስ እና ቅዱስ ሉቃስ ናቸው።
"ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን ማልዶ በተነሣ ጊዜ፥ አስቀድሞ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለመግደላዊት ማርያም ታየ።እርስዋ ሄዳ ከእርሱ ጋር ሆነው ለነበሩት ሲያዝኑና ሲያለቅሱ ሳሉ አወራችላቸው፤ እነርሱም ሕያው እንደ ሆነ ለእርስዋም እንደታያት ሲሰሙ አላመኑም። ከዚህም በኋላ ከእነርሱ ለሁለቱ ወደ ባላገር ሲሄዱ በመንገድ በሌላ መልክ ተገለጠ፤ እነርሱም ሄደው ለሌሎቹ አወሩ፤ እነዚያንም ደግሞ አላመኑአቸውም። ኋላም በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ለአሥራ አንዱ ተገለጠ፥ ተነሥቶም ያዩትን ስላላመኑአቸው አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቀፈ። እንዲህም አላቸው። ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፥ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ። ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ።" (ማር.፲፮፡፱-፲፱)

"እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ። እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ።" (ሉቃ.፳፬፡፵፰-፶፩)
ቅዱስ ሉቃስ የሐዋርያት ሥራን ሲጽፍ ስለ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት አብራርቶ ጽፎታል። እንዲህ ሲል፦
"ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው። ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን። ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ። እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለውጠየቁት። እርሱም አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ። ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም። የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።" (ሐዋ.፩፡፫-፲፩)

ክርስቲያኖች በሰማያት ስፍራ ከጌታችን ከመድሃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረው እንደሚቀመጡ የእርሱ ዕርገት ያረጋግጥልናል። ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ጌታችን እርገት እንዲህ ሲል ይመክረናል፤ " እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ። በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና። ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበትጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ።" (ቆላ. ፫፡፩-፬)



ወስብሐት ለእግዚአብሔር


https://t.me/tewahido_ortho