Get Mystery Box with random crypto!

✥ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ✥ የቅዱስ ኤፍሬም ሀገረ ውላዱ ከዋክብትን ከሚያመልኩ ሰዎች መካከል | መንግስተሰማይ ቀርባለች እና ንሰሀ ግቡ🙏 ተዋህዶ ሀይማኖቴ

✥ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ✥



የቅዱስ ኤፍሬም ሀገረ ውላዱ ከዋክብትን ከሚያመልኩ ሰዎች መካከል ነው፡፡ አባቱም ክርስትናን የሚጠላ ካህነ ጣዖት ነበር፡፡ አንዳንድ ምንጮች ከቅዱስ ኤፍሬም ሕይወት በመነሳት ወላጆቹ ክርስቲያኖች እንደነበሩ ዘግበዋል የሐምሌ አስራ አምስት ስንክሳር ግን የአባቱን ካህነ ጣዖትነት ያረጋግጣል ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው  በ306 ዓ.ም ገደማ “በሜሶፖታሚያ” ውስጥ በምትገኝ “ንጽቢን” እንደሆነ ይታመናል። (ንጽቢን   በደቡባዊ ቱርክ እና በምዕራባዊ ሶርያ መካከል የምትገኝ ቦታ ናት፡፡) ይህቺም ቦታ ከ318ቱ ሊቃውንት አንዱ የነበረው የቅዱስ ያዕቆብ ሀገረ ሰብከቱ የነበረች ናት፡፡

ይህንን ታላቅ አባታችንን የእግዚአብሔር መንፈስ አመላክቶት ወደ ቅዱስ ያዕቆብ ሄዶ ትምህርተ ክርስትናን ተምሮ የተጠመቀ ሲሆን ከወላጆቹ ጋር የኖረው እስከ አሥር ዓመቱ ብቻ ነው፡፡ በትምህርተ ክርስትና አምኖ ከተጠመቀ በኋላ ግን በቅዱስ ያዕቆብ ዘንድ በብሕትውና ተወስኖ በመማርና በማስተማር በንጽቢን ለሚገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሓላፊ እስክመሆን ደርሶ ነበር፡፡
በ393 ዓ.ም የንጽቢን ከተማ  በወራሪዎች እጅ ስትወድቅ ቅዱስ ኤፍሬም ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በመሆን የሮም ግዛት ወደነበረችው ኤዴሳ (ታናሽ እስያ፣ዑር) ተሰደደ፡፡ ይህቸ ቦታ ቅዱስ ኤፍሬም ከመናፍቃን ጋር የተጋደለባት፣ በቤተክርስቲያን ትምህርት ላይ ያላቸውን አብዛኞቹን የክህደት ትምህርቶች የሞገተባትና  መጻሕፍቱን ያዘጋጀባት ናት፡፡አብዛኛዎቹን ትምህርቶቹንና መጻሕፍቱን ያዘጋጀው በዚች በኤዴሳ በሚገኘው ትምህርት ቤት ነው፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም ከመምህሩ ከቅዱስ ያዕቆብ ጋር በመሆን በአርዮስ ምክንያት በተካሄደው  የኒቅያው ጉባኤ ( 325 ዓ.ም ) ላይ ተገኝቷል፡፡ በዚህም የአርዮስን ክህደትና ምክንያተ ውግዘት ተገንዝቧል፡፡ ከኒቅያ ጉባኤ መልስ መንፈሰ እግዚአብሔር በራዕይ በገለፀለት መሠረት ቅዱስ ኤፍሬም ከቅዱስ ባስልዮስ (ቁጥሩ ከ318ቱ ሊቃውንት ወገን ነው) ዘንድ ለመገናኘት ወደ ቂሣርያ ሄዷል፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም የዲቁና ክህነት ሠጥቶ ከሀገረ ስብከቱ ከፍሎ እንዲያስተምር ወስኖ በእርሱ ዘንድ አኑሮታል፡፤ በዚያም ቦታ ብዙ ተአምራትን አድርጓል መጻሕፍትንም ጽፏል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በትውፊት እንደሚታወቀው ምንኩስናን በገቢር ገለጣት እንጂ ሥርዓተ ምንኩስናን መፈጸሙን በግልጽ የሚመለክት ማስረጃ አልተገኘም፡፡

እንዲያውም በሶርያውያን ክርስቲያኖች የሚዘወተረውን ራስን በአንድ ስፍራ ወስኖ በብሕትውናና በመምህርነት ቤተክርስቲያንን የማገልገል (Proto monasticism) ሕይወት ይኖር እንደነበር ይታመናል፡፡ በትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱስ ባስልዮስን ለመጎብኘት ወደ ቀጰዶቅያ እንዲሁም አባ ቢሾይን ለመጎብኘት ወደ ግብጽ እንደተጓዘ የሚነገረውም ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው ፍጹም በሆነ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቱ ምሳሌ በሚሆነው ትምህርቱና የምናንኔ ሕይወቱ የሚታወቀው ቅዱስ ኤፍሬም ሐምሌ አስራ አምስት ቀን በ 370 ዓ.ም አርፏል፡፡በዚህ ሁሉ ትጋቱም ሶርያውያን ክርስቲያኖች ‹ጥዑመ ልሳን›፣ ‹መምህረ ዓለም›፣ ‹ዓምደ ቤተ ክርስቲያን› በማለት ይጠሩታል፣ያወድሱታል፣ያመሰግኑታል የቅዱስ አባታችን ረድኤትና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን!


__



@Tewahido_Haymanote_1
@TewahidooHaymanote_1
@Tewahido_Haymanote_1
Join