Get Mystery Box with random crypto!

'፮ኛ ኮርስ 'የቤተ ስርስቲያን ሥርዓትና ምጢራት' #በስመ_አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ_አሐዱ_አም | የተዋህዶ ቤተሰቦች✝ ኮርስ መስጫ

"፮ኛ ኮርስ "የቤተ ስርስቲያን ሥርዓትና ምጢራት"

#በስመ_አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ_አሐዱ_አምላክ_አሜን

►►►►►►►►►►►►►►►►►►►►►►
፫.፭, #ምሥጢረ_ንስሐ
፫.፭.፫,
#የንስሐ_አጀማመር
የሰው ልጅ ሁሉ አባት የሆነው አዳም ምክረ እግዚአብሔርን ዘንግቶ በምክረ ከይሲ ዲያቢሎስ ተታልሎ ሕግ ባፈረሰ ጊዜ ጸጋው ተገፎና ባሕርይው ተጎሳቅሎ ነበር።
ነገር ግን እንደወደቀ ሳይቀር እንባውን እያፈሰሰ በሐዲስ ተፈጥሮ እንዲያድሰው ወደ ወጣበት ርስት መልሶ እንዲያገባው ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
እግዚአብሔርም ልመናውን ሰምቶ ከመከራው አድኖ ተስፋ ድኅነት ሰጥቶታል።
የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜም አንድያ ልጁን ልኮ አድኖታል። (ገላ 4፥4)


በብሉይ ኪዳን የመጀመሪያው ተነሳሒ አባታችን አዳም ነው። እርሱን አብነት አድርገው ልጆቹ ቢበድሉም በሕገ ልቦና ኋላም በሕገ ኦሪት የኖሩ አበው ንስሐን ገንዘብ አድርገው ይኖሩ ነበር።

ይሁን እንጂ በምድር በሥጋ መከራው ቢቀልላቸውም ዞሮ ዞሮ ከሞት ማምለጥ/ከሲኦል መሰወር ግን አይቻላቸውም ነበር።

ነቢዩ ኢሳይያስ "ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሁነናል ጽድቃችንም እንደ መርገም ጨርቅ ነው።" (ኢሳ 64፥6) ብሎ መናገሩ በብሉይ ኪዳን የነበረው ንስሐ ሰውን ፍጹም ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ስላልቻለ ነው።

ምንም እንኳን ነቢያት በየዘመናቱ ከደረሰውና ከሚደርሰው መከራ በምክራቸውና በትምህርታቸው ሕዝቡን ወደ ንስሐ ቢመልሱም፤ በጸሎትና በምልጃቸው ሕዝቡን ከመዓት፣ ከቁጣና ከሞት ቢያድኑም (መዝ 105፥23) ይህ ሁሉ ተጋድሎአቸው ግን የሰውን ልጅ በንስሐ ከሲኦል ወደ ገነት ሊመልስ አልቻለም። ሁሉም በጥንተ አብሶ ባለእዳ ነበሩና። (መዝ 63፥5)


ሐዲስ ኪዳን በሐዲስ ኪዳን መሥዋዕቱ በፍጡር ባለመሆኑና ሞት የማያሸንፈው በመሆኑ ንስሐ ፍጹም ሆኗል። ማንም ሊከፍለው ያልቻለውን የአዳምን የበደል ዕዳ እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሆኖ ከፈለልን።

እኛ በበደልን እርሱ ፍጹም ካሣን ክሦልን ዐፅመ አዳም ባረፈበት በጎለጎታ ተሰቅሎ የሞትን መውጊያ ሰበረልን።
የመቃብርንም ኃይል ሻረው። ርቀን የነበርነውን አቅርቦ ልጆቼ አለን። (ማቴ 27፥33 ፤ 1ኛ ቆሮ 15፥56) በበደሉ አዝኖና ተክዞ በንስሐ የሚመለስ ሰው ሁሉ ለርስት መንግስተ ሰማያት ተካፋይ እንደሚሆንም ተስፋ ሰጠው።

በሐዋርያት አባቶቻችን ዘመን ንስሐ ከ"እምየት" ጋር የተያያዘ ነበር። ምክኒያቱም ተነሳሕያኑ ከቤተ አይሁድ አልያም ከአሕዛብ ወገን ስለነበሩ አስቀድመው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለመፈለግ ከቤተልሔም ዋሻ እስከ ቀራኒዮ ጎለጎታ ያለፈበትን የማዳን ጉዞና የፈጸመውን የቤዛነት ሥራ ተምረውና በባሕርይ አምላክነቱ አምነው ንስሐ ይገቡ ነበር። (የሐዋ 2፥28)

እንዲያውም በመጀመሪያዎቹ የሐዲስ ኪዳን ዓመታት ንስሐ በአደባባይ በሕዝብ ፊት ነበር የሚፈጸመው። (ሐዋ 19፥18 ፤ 1ኛ ቆሮ 7፥11 ፤ ያዕ 5፥16) በኋላ ግን የአንዱን ኃጢአት ሌላው ሰምቶ እንዳይሰናከል በማሰብ በምሥጢር ሆነ። በተነሳሒው፣ በመምህረ ንስሐውና በእግዚአብሔር መካከል የሚቀር ምሥጢረ ንስሐ ነው።
◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄◄

@Tewahdo_Haymanotie
#ቀጣይ_ትምህርታችን-->በንስሐ የሚገኙ ጸጋዎች
#ወስብሀት_ለእግዚአብሔር_ወለወላዲቱ_ድንግል_ወለመስቀሉ_ክቡር_ይቆየን!!

ገፅ ➒❽