Get Mystery Box with random crypto!

+ ጌታ የተወለደው የት ነው? + የገና ዋዜማ የት ልትሔድ አሰብህ? ምሽቱንስ የት ልታሳልፍ ነው? | ጥበብ በእርስው

+ ጌታ የተወለደው የት ነው? +

የገና ዋዜማ የት ልትሔድ አሰብህ? ምሽቱንስ የት ልታሳልፍ ነው? የትኛው ሆቴል? የትኛው የሙዚቃ ድግስ? "የገናን በዓል አስመልክቶ የተዘጋጀ ልዩ የሙዚቃ ድግስ" ላይ ጌታ የለም:: ባለ ልደቱ ጌታ የት ነው ያለው? አድራሻው ከጠፋብህ የተወለደ ዕለት የሆነውን ልንገርህ!

የተወለደውን ክርስቶስ ለማየት ብዙ ሀገራትን አልፈው ተጉዘው የመጡት ሰብአ ሰገል በኮከብ ተመርተው ነበር::
ለእስራኤላውያን እረኞች በታሪካቸው ውስጥ በሚያውቁአቸውና በለመዱአቸው መላእክት ልደቱን የገለጠው አምላክ ኮከብ ሲቆጥሩና ሲጠነቁሉ ለኖሩት ሰብአ ሰገል ደግሞ በሚያውቁት ኮከብ መራቸው::
ሕጻኑ ክርስቶስ ገና ከመወለዱ ብዙ እንደ ጣዖት የሚመለኩ ነገሮችን ድል አድራጊ መሆኑን አሳየ::

በሲና በረሃ እስራኤል ጥጃን አምላክ ብለው በወርቅ ጣዖት ሠርተው ነበር:: በቤተልሔም ጥጃ  ትንፋሹን ለክርስቶስ በመገበር አምላኬ እርሱ ነው ሲል መሰከረለት:: በሬም ገዢውን አወቀ ሕዝቤ ግን አላወቀኝም የሚለው ተፈጸመ:: ከዋክብትንና ፀሐይን ያመልኩ የነበሩን የዞረዳሸት (ዞራስትራኒዝም) ፍልስፍናን የሚያምኑ ሰብአ ሰገልም በሚያመልኩት ኮከብ ፈጣሪያቸውን አገኙ:: ቅዱስ ኤፍሬም እንዳለው "የሚያመልኳት ፀሐይም በሰብአ ሰገል ጉልበት ለፈጣሪዋ ሰገደች"

ኮከብ የሚወጣበት ጊዜ በዚያን ቀን የሰውን ዕጣ ፈንታ ይወስናል ብለው የሚያምኑም ብዙዎች ናቸው:: ይህ የሆነው በኮከቤ ምክንያት ነው! ኮከባችን አይገጥምም የሚባባሉ ብዙዎች ናቸው:: ይህ ሁሉ ባዕድ አምልኮ ነው::  ኤሳውና ያዕቆብ መንትዮች ናቸው:: የተወለዱት በአንድ ቀን ነው:: እነርሱ በተወለዱ ቀን የወጣው ኮከብም አንድ ነው:: "ኮከባቸው" አንድ ሆኖ ሳለ ምነው ነገራቸው ሁሉ አልገጥም አለ? ኮከባቸው ይገጥማል ምነው እነርሱ አልገጠሙም? ስለዚህ ሐሰት ነው::

የተወለደው ንጉሥ ግን ኮከቡ ዕጣ ፈንታውን የሚወስነው ሳይሆን ከዋክብትን በየስማቸው የሚጠራቸው በቁጥር የሚያውቃቸው ጌታ ነው:: እንደ ዮሴፍ 11 ከዋክብት ሐዋርያቱ ከይሁዳ በቀር የሰገዱለት እናቱ ማርያምም እንደ ያዕቆብ በልብዋ እያሰበች የተደነቀችበት የከዋክብት ጌታ የጨረቃ ንጉሥ የፀሐዮች ሁሉ ፀሐይ ነው እርሱ::

ሰብአ ሰገል መሪያቸው የነበረውን ኮከብ ሲያጡት ወደ ሔሮድስ መጡና "የተወለደው ንጉሥ ወዴት ነው?" አሉ::
እውነትም ጠቢባን ናቸው:: መንገድ ከጠፋብን : መሪ ኮከብ ካጣን ልደቱን የፈለግንበት እናክብር አላሉም:: የተወለደው ወዴት ነው? ብለው ቤተ መንግሥት ሔደው ጠየቁ:: ጥሩ በዓል ለማክበር ከቤተ መንግሥት የተሻለ ሥፍራ የለም:: በቤተ መንግሥት ራት እየበሉ ጮማ እየቆረጡ በዘፈን ታጅበው በዓሉን ማክበር ይችላሉ:: እነርሱ ግን የትም ቢሆን ንጉሡን ሳናገኝ አንቆይም:: እሱ የሌለበት ቦታ ቤተ መንግሥትም ቢሆን ልደቱን አናከብርም:: አይ ሰብአ ሰገል! ይህንን ዘመን መጥተው ቢያዩ ምን ይላሉ?

ወዳጄ አንተ የጌታን ልደት የት ታከብራለህ? መቼም
ልደት የሚከበረው ባለ ልደቱ ባለበት ሥፍራ ነው:: በእውነት የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በጭፈራ ቤት ነውን? በመጠጥ ቤት ነውን? የት ነው ያለው ብለህ ጠይቀሃል?

"የሚመራኝ ኮከብ የለም" ትል ይሆናል:: ምንም ቢሆን ግን ሕፃኑ በሌለበት ልደቱን ለማክበር መወሰን የለብህም:: ምንም ያሸበረቁ ሥፍራዎች ቢኖሩም እንዳትታለል:: የሔሮድስ ቤተመንግሥት ውበት የግብዣው ስፋት አታልሎህ የተወለደውን ንጉሥ እንዳያስረሳህ ተጠንቀቅ:: እሱ ከሌለበት ያማረ ሥፍራ ይልቅ እሱ ያለበት በረት ይሻልሃል:: እሱ ያልመረጠውን ሥፍራ መርጠህ ከመንገድ አትቅር:: "የተወለደው የአይሁድ ወዴት ነው" ብለህ ጠይቅ::

እሱ ደሃ ሆኖ ባለጠጋ የሚያደርግህን ንጉሥ በሚያልፍ ደስታ አትጣው:: በስካር በዝሙት በጭፈራ በሔሮድስ ቤተ መንግሥት ቀልጠህ ቀርተህ የተወለደውን ሕፃን ሳታየው አትቅር:: እሱ በተወለደባት ሌሊት አንተ ስትሞት አትደር:: እመነኝ የተወለደው ይሻልሃል ከሞቱት ጋር ጊዜህን አታጥፋ::

ሰብአ ሰገል "የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?" ብለው ለአይሁድ ንጉሥ ሔሮድስ ጠየቁት:: የአህያ ውኃ ጠጪው ሔሮድስ ክው ብሎ ቢደነግጥም ፈገግ ብሎ ላጣራላችሁ ቆይ ብሎ አቆያቸው:: መጽሐፍ አዋቂዎቹን ጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠሩ:: እነ ሊቄ መለሱ:: "እንደተነገረው ትንቢት ከሆነማ" አሉ ኩፍፍፍስ ብለው
"በይሁዳ ቤተልሔም ነው" ብለው የተወለደውን ንጉሥ አድራሻ ተናገሩ:: ሔሮድስ ከነተንኮሉ ለሰብአ ሰገል መልእክቱን አደረሰ:: ሰብአ ሰገልም ሔደው ለንጉሡ ሰግደው እጅ መንሻ አቀረቡ::

ሔሮድስን ትተን እስቲ የጸሐፍቱን ነገር ትንሽ እናስተውለው:: የተወለደውን ጌታ አድራሻ ጠቁመው ለሰብአ ሰገል መንገድ የመሩ እነርሱ ግን መንገድና እውነት ሕይወትም የሆነው ጌታ የተሰወረባቸውን የታወሩ መሪዎች   በሽተኛ ሐኪሞች የተራቡ መጋቢዎችን እስቲ ልብ እንበላቸው:: "ጥሩምባ ነፊ ቀብር አይገኝም" ማለትስ አይሁድ ናቸው::

ሌላውን ወደ ጌታ እየመራ እርሱ ከጌታው የራቀ : የእርሱን ቃል ሰምተው ሰዎች ሲድኑ እርሱ በኃጢአት ቁስል የተወረሰ ስንት አይሁድ እለ? ቅዱስ አምብሮስ እንዳለው የኖህ መርከብ ሲሠራ ሚስማርና መዶሻ እያቀበለ የሠራ ነገር ግን ከጥፋት ውኃ ያልዳነ ስንት በየቤቱ አለ::

እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል ማለት ቀላል ነው:: እንደተጻፈው መኖር ግን ከባድ ነው:: ከመጽሐፍ ጥቅስ ማውጣት ቀላል ነው የሚጠቀስ ሕይወት መኖር ግን ከባድ ነው:: ወዳጄ ለብዙ ሰብአ ሰገሎች ስለተወለደው ንጉሥ ነግረሃል:: በአንተ ሕይወት ውስጥስ "የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?" ወይስ በአንተ ሕይወት ገና አልተወለደም? ወይስ እንደ እንግዶች ማደሪያ ቦታ የለም ብለህ መልሰኸዋል? ኸረ እኔ እንኩዋን የቆሸሸ ሕይወት ነው ያለኝ እሱ በእኔ አያድርም አትበል? እንደ በረት ብትሸት እንደ እንስሳ እየኖርህ ቢሆንም አትፍራ እርሱ አይጠየፍህም? ወደ ልብህ መለስ ብለህ እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ "በእኔ ሕይወት ውስጥ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?"

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 27 2012 ዓ ም