Get Mystery Box with random crypto!

#የዊላዳው_ጎህ በይፋው መቀነት በጋሃዱ ዓለም፣ የደከመ ጉልበት የራፈቀ አቅም፣ ከልቡ አይስቅም፣ | ትዳር እና ጥበባዊ ቃላቶች

#የዊላዳው_ጎህ

በይፋው መቀነት በጋሃዱ ዓለም፣
የደከመ ጉልበት የራፈቀ አቅም፣
ከልቡ አይስቅም፣
ጦሀን ያልወደደ በቀጣዩ ዓለም ዘውድ አይታጠቅም።


ደግሞ በኛው ዘመን...
በዚህ ሰበህለላ በዓለመ-ምጸት፣
በድቅድቅ ጨለማ ደግሞ በኛ ቁጭት፣
የዘይኔ ዊላዳ ሰንደቅ ባይተክልበት፣
የህይወት ሙናዋን እድሜ የሚፈትት፣
የዝሆን ማርጣ ነው ዘቅዝቆ ሚገትት።

ያኔ ድሮ
በዚያኛው ጎህ ደግሞ በጥንቱ ሰመመን፣
ከዕልፍ አመት በፊት በዚያ ቋያ ዘመን፣
በሸውቅ አስወገዱት የምድርን ዳረመን።


የሰይዲን አንገት ቢያዘልቀው ዊላዳው፣
ማራኪው ጠረኑ ዓለምን አወደው፣
ሚስክንም غሊያ
ሽቶ የተባለን ጠራርጎ ወሰደው።


የኔው ወገን ደግሞ በሸውቅ የሰከረው፣
መውደዱ መዲና ሊነዳው ሞከረው፣
ወራትን ሰንቆ ዙል ሂጃን ሲጠብቅ፣
አያየው ነጎደ ስንቁን ሲያጠባብቅ፣
ያኔ ከድሮው ሸንቁጦት ኖሮ፣ የፍቅሩ ለበቅ፣
ለትቶ ጅስሙ ቢበን እንደብቅ፣
ሰከን አረገው የዊላዳው ጎህ ተራ እንዲጠብቅ።


ከዚያ ከዚያማ ቡኋላ
አይቶት ያንን አወራ በህልሙ ጋሞራ፣
ያ ውቡ ከንፈሩ ተላውሶ ሲያወራ፣
እንኳን ያዳመጠው ሙትን ሲያንሰራራ፣
በትንፋሹ ዓለም አብቦ ጎመራ፣
የመውሊዱ ሎሌ ታጥቆ ተሰማራ።


ስንቱ ወዳጅ ነበር...
ስንቱ ወዳጅ ነበር በፍቅር ያጓራ፣
እጅግ ሲዘረጋ ሲረበብ ሲጣራ፣
እስትንፋሱ በሮ ከንፎ እንዳሞራ፣
በዊላዳው ሽታ ከሞት አንሰራራ።


ባይሆን ነው 'ሚደንቀው...
ለእዝነት ተልከው ለሰውም ለጅኑ፣
በመውሊዱ ለሊት ክህደቶች ቀጠኑ፣
እልፍ አዕላፍ ወልጋዶች በነቢ ተቃኑ።

ስለዚህም አሁን...
ህይወት ያለወትሮው በጌጥ አሸብርቋል፣
ዓለም ደሟ ባርቋል፣
ጽልመት ያለበሳት ዳመናው ተገልጧል
የዘይኔ ዊላዳ የብርሃን ጎህ ቀዷል።
ከኔ አንጻር እንኳን፣
ዓይሼ ተቀላጥፏል በመውሊዱ ድንኳን።
ለነገሩ...
የራምሳቸው ሆታ የበርዘንጁ እጣን፣
እንኳን ደርዘኛውን ያድነው የለ እንዴ
መረን የወጣውን።


ከፊሉ ሰው ደግሞ...
ጥንት የጎሰመው የፍቅሩ ቃሬዛ፣
ሙሐቻ አስመስሎት ህይወት እንደዋዛ፣
መውሊዱ ቢመጣ ነቁን እያወዛ፣
ቆቤ ቅል ይመስል እያደር ወረዛ።

እናማ ወዳጆቼ...
አርምሞ ሞልቶቦት ጥንት አቅም ላጣው፣
ለዚህ የክት ዓለም ለክህደት ባላንጣው፣
የዘይኔ መውሊድ ነው ቅናቻን ያመጣው።


ገጣሚ አንዋር ዩሱፍ







#የቃልት_መፍቺያ(ካስፈለገ)

የራፈቀ=አቅም አጣ፣ደከመ
የሚፈትት=የሚቆረሰ፣የሚገመስ
ሙና=ብላቴና፣ህጻን
የዝሆን ማርጣ= የዝሆን ጭራ
ቋያ=ሰደድ
ዳረመን=እከክ፣ፎከት
ለበቅ=ልምጭ፣አርጩሜ
ለትቶ=ደከሞ፣ዝሎ
ሲረበብ=ሲዘረጋ
መረን=ባለጌ፣ስድ
አርምሞ=ጸጥታ፣ዝምታ
ነቅ=የፈካ መሬት(የተሰነጣጠቀ)
ሙሐቻ= የማይጠራ የሊጥ ማቡኪያ