Get Mystery Box with random crypto!

=> አድዋ እና ሰበቡ በሲራክ ወንድሙ ... ክፍል ፩ ....... ይህ ፅሁፍ ኅብረ ኢትዮጵያ | ታሪካችንን እንወቅ

=> አድዋ እና ሰበቡ
በሲራክ ወንድሙ
... ክፍል ፩
....... ይህ ፅሁፍ ኅብረ ኢትዮጵያ በሚል ርዕስ በቴዎድሮስ በየነ በ2008 ዓ.ም ከታተመው የታሪክ መፅሀፍ ውስጥ የአድዋ ድል ከሚለው ምዕራፍ ላይ ለአንባቢ እንዲበጅ (እንዲገባ) በሌላ ቅንፍ በትንሹ እውቀቷን ለማስጨበጥ በሌላ ሌላ ቅንፍ ለመላው አፍሪካ የነፃነት በዓል ምክኒያት በማድረግ ከ ፌስቡክ ሆይሆይታ ና ሆያሆዬ ባሻገር ጦርነቱ ላይ በምናብ በመገኘት ለመዘካከር ነውና ሳትሰለቹ አንብቧት።

መጀመሪያ ላይ ስለአድዋ ጦርነት መንስኤ ሲነሳ የውጫሌው ውል አንቀፅ አስራ ሰባት እንደሆነ በሰፊው ሲነሳ እንሰማለን
ውሉ ችግሩ ምንድነው? መቼ ተፈራረሙ? ውጫሌ የት ነው?

....ውጫሌ በወሎ ወረኢሉ ውስጥ የምትገኝ መንደር ስትሆን ይህን ውል የኢጣልያ መንግስት እና የኢትዮጵያ መንግስት በሚያዚያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም በውሉ አስተርጓሚ በግራዝማች ዮሴፍ ንጉሴ የተከናወነ ውል ነው።
ውሉ ጠቅላላ 20 አንቀፅ ሲኖረው ለጦርነቱ መነሻ የሆነው አንቀፅ 17 ነው።

እስኪ አንቀፁን በሁለቱም ትርጉም እንመልከተውና ለጥቀን ሌላውን እንቀጥል:-
#በአማረኛ_የተፃፈው
"የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ከአውሮፓ ነገስታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ የኢጣሊያ መንግስት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል።"

.... ይላል።
#በኢጣሊያኛ_የተፃፈው_ደግሞ
"የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ አገር መንግስታት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግስት አማካኝነት ማድረግ ይገባቸዋል።"
...የሚል ነበር።

ጣሊያኖች ይህን ውል ከተዋዋሉ በኃላ ለ12 የአውሮፓ መንግስታትና ለዩናይትድስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ጭምር October 11 ቀን 1889 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ #ኢትዮጵያ_በኢጣሊያ_ስር_ነች እያሉ አሳወቁ።
በትምህርት ቤት መማሪያ ደብተሮችም ላይ ሁሉ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ጥገኝነት ስር ናት የሚል ታተመ።

ይህ ለአድዋ ጦርነት መነሳት ምክኒያት ና ዋነኛ መንስኤ የሆነው ጉዳይ ሊታወቅ የቻለው አለቃ አፅመ ጊዮርጊስ የተባሉ ቋንቋ አዋቂ አፄ ምሊኒክ በሰጧቸው ትዕዛዝ መሰረት የውሉን ሰነድ በመመርመር የውሉ 17ኛው አንቀፅ የያዘውን ትርጉም መዛባት በመግለፅ ጉዳዩ ኢትዮጵያ የምትጎዳበት ስለመሆኑ ጭምር በማስረዳት በሰጡት ቃል ነው።

............. ይህን ያህል ስለ17ኛው ውል መሳሳት አቅጣጫ ከያዝንና ካየን የትርጉሙ መጭበርበር እንዴት ከአለቃ አፅመ ጊዮርጊስ ለአፄ ምሊኒክ እንደደረሰ እንቃኝ።
አለቃ አፅመ ጊዮርጊስ ባልታተመ (ይህ የወንድማችን ቅፅ አንድ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ) መፅሀፋቸው እንደገለፁት ለአፄ ለምሊኒክ እንዲህ ሲሉ በደብዳቤ አመለከቱ :-
<< የተፃፈው ውል ኢጣሊያ አገር የሚሄደው ማለፊያ ነው።
ብቻ 17ኛውን ክፍል ይመልከቱት።ዛሬ በሚዛን ብትመዘን የብር ተመን አትሆንም ካንድ ዓመት በኃላ ግን ከሺህ ቶን ፈረሱላ እርሳስ ይልቅ ትከብዳለች። >>

... ይህ ደብዳቤ እንደ ደረሳቸው ምኒሊክ አንቶኔን አስጠርተው እንደገና ጠየቁት።
አሁንም ግልፅ ባልሆነ አነጋገር አጭበረበራቸው። እንዲህም አለ << ታዲያ ይህ ምን ክፋት አለበት (17ኛው ክፍል) እኛ የርስዎ አሽከርዎ ፖስተኛ መሆናችን ነው እንጂ።>>... | አለቃ አፅመ ጊዮርጊስ የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ (ያልታተመ)|

....... የውሉ ዋና ፀሀፊ ፒዬትሮ አንቶኔሊ ከአፄ ምሊኒክ ከእቴጌ ጣይቱና ከመኳንንቱ ፊት ቀርቦ ይህን የውጫሌ ውል እምቢ ካሉ ጦርነት መነሳቱን እንዲያውቁት ያስፈልጋል ብሎ ሲደነፋ እቴጌ ጣይቱ ደግሞ እጥፍ ጊዜ ቱግ ብለው ተቆጡና፤
" የዛሬ ሳምንት አድርገው። በዚህ የሚደነግጥልህ የለም ሂድ የፎከርክበትን አድርግ። እኛም የመጣውን እናነሰዋለን። እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የማያድን ሰው በዚህ የሌለ አይምሰልህ።
የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ አገሩ መሞት ጌጥ ነው እንጂ ሞት አይባልም። አሁንም ሂድ አይምሽብህ የፎከርክበትን በፈቀደህ ጊዜ አድርገው። እኛም እዚህ እንቆይሃለን።.....
እኛ ለራሳችን እንበቃለን የሀገራችንንም ክብር እንጠብቃለን። አንፈራችሁም! በፈቀድነው ጊዜ ከመሬታችን ከሀገራችን ተራራ እንደ ድንጋይ እንፈነቅላችኃለን።" አሉት።

እርሱም ከአዳራሹ ሊወጣ ከሞከረ በኃላ እንደገና መለስ ብሎ
"የምንገጥመውኮ ጦርነት ነው፤ ወንዶቹስ በሆነላቸው እንኳን ሴቲቱ" አላቸው።
"የእኔ ሴትነትና ያንተ ወንድነት የሚለካው እዚያው ጦር ሜዳ ነውና እንዳትቀር።"ብለው መለሱለት።
እንግዲህ የአጭቤው(አጭበርባሪው)አንቶኔሊ አንቶዬ(ስምህን ቄስ ይጥራው አንተ ሰላቢ ለነገሩ.... )
በንቀት እና በወኔ ሙላት የተመላለሱትን ቃለ ምልልስ አይተናል።

የጣይቱን ፉከራ በጦርነቱ ውስጥ በሰራችው ገድል የምናውቀው ነው መቼስ።
ያው ዘመን እየመጣ ዘመን በሄደ ቁጥር እነእቴጌን መሰል ሴቶችን ማጣት የሀገር ህመም ነው። መቼስ ዘንድሮ እንደሆነ ፎክረውና ብልሃት ምሰው ከሚያሸንፉ ይልቅ ቁራጭ ጨርቅ በላያቸው ላይ ለጥፈው ወንዱን እያፈዘዙ አንዴ ከቆመ ዛፍና መኪና ጋር እያጋጩ አንዴ ቦይ ውስጥ እየከተቱ ሆኗል ብልሃቱ። (ቱ ደሞኮ እኛኑ ነው )
እኔስ ስንቴ ነው አንገቴን እስኪያመኝ እየሾፍኩ ቆሎ በትኜ ጣቢያ ያደርኩት " መገን" አለ ወሎ።

የአንቶኔሊን ንቀት ታክል በዘመኔ ላይ መማረር ቢኖርብኝም ይሁን ይመቻቸው ብያለሁ።
የዚህችን ክፍል መዝጊያ ከመፅሀፉ ውስጥ ባገኘዋት ፈገግ በምታስብል ገጠመኝ ልዝጋና በቀጣዩ ቀን በሌላ ክፍል ልመለስ....

...... አንቶኔሊ ከስብሰባው ሲወጣ ምኒልክ ለጋሲዮን ድረስ የሚሄድበት በቅሎ ስጡት ብለው ተሰጠው። አንቶኔሊ በቅሎ ለሰጠው አሽከር አንድ መቶ ብር ሰጠ።
አሽከሩም የተሰጠውን ብር ይዞ አዳራሽ ገብቶ ለምኒልክ ነገረ።
ራስ መኮንን ነበሩና " ጉርሻ ከሆነ ይበዛል። ጃንሆይ ለሰጡት በቅሎ ከሆነም ያንሳልና ይመለስ!" አሉ። ምኒልክም ስቀው ለአሽከሩ "ጉርሻ ነውና ውሰደው" አሉት።

........... ዛሬ የአድዋን ድል መዳረሻ ቀናት አስመልክቼ በቅንጭብ ያቀረብኩት ክፍል ይህን ይመስላል በቀጣይ አንዳንድ የጦርነቱን ነጥቦች እናያለን ሀሳብ አስታየታችሁን ፃፉልኝ።
የተሳሳትኩትም ካለ አርሙኝ ያጠፋሁትም ካለ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

ለዚህ ፅሁፌ በዋነኝነት ኃብረ ኢትዮጵያ በሚል ርዕስ በ2008 ዓ.ም በቴዎድሮስ በየነ የታተመውን ቅፅ አንድን ተጠቅሜያለሁ።
ቸር ቆይታ!!!
- ለማድብን እጅጉ ( ቃሲም )
- ለበፍቃዱ አረጋ
#እና
- ለቃለአብ ሲሳይ (ናታኒም)
ምስጋናዬ ይድረስልኝ
#ሲራክ ወንድሙ @siraaq
@tarikacheninenwoke
@tarikacheninenwoke