Get Mystery Box with random crypto!

በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ የሚፈጸም ማዋከብ ሊቆም እንደሚገባ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳሰበ!! | ስልጤ ዞን ኮሚዩኒኬሽን - SILTIE ZONE COMMUNICATION

በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ የሚፈጸም ማዋከብ ሊቆም እንደሚገባ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳሰበ!!

መገናኛ ብዙሃን በሚያከናውኗቸው የምርመራ ጋዜጠኝነት ስራዎች ላይ በማንኛውም አካል የሚፈጸም ማዋከብ ሊቆም እንደሚገባ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳሰበ።

ባለስልጣኑ በተለይ የምርመራ ጋዜጠኝነት ስራ አጋዥ ተዋናይ መሆን የሚጠበቅባቸው የህፍሕ አካላት ለዚህ ስራ ተባባሪ እንጂ እክል እንዳይሆኑም ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዛሬ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ለመገናኛ ብዙሃን ስራ አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር በህግ የተጣለበትን ሃላፊነቱን ከመወጣት አንጻር የምርመራ ዘገባ በሚያከናውኑ ባለሙያዎችና ተቋማት ላይ የሚፈጸም ማዋከብ መቆም እንዳለበት አሳስቧል።

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29 እና በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 48 መሰረት መገናኛ ብዙሃን የህዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው ያመለከተው መግለጫው የምርመራ ጋዜጠኝነትን ከማበረታታ አንጻርም እንደ መንግስት አቅጣጫ ተይዞ እንዲሰራ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማሳሰቢያ መሰጠቱን ጠቅሷል።

በመርህ ደረጃ የዜጎች መብት የተረጋገጠበት የዴሞክራሲ ባህል የሚጎለብትበትና ተጠያቂነት የሚሰፍንበት ስርዓት ለመገንባት የፍትህ አካላት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር መስራታቸው ጠቃሚ መሆኑን ገልጿል።

ይህ ሊረጋገጥ የሚችለው መገናኛ ብዙሃን ያለምንም መታወክና እንቅፋት ብቁ የምርመራ ጋዜጠኝነት ስራ እንዲሰሩ መረጃ የማግኘት የመሰብሰብና የማሰራጨት መብታቸው ከማንም በላይ በፍትሕ አካላት ሲረጋገጥና ጥበቃ ሲደረግለት እንደሆነም አስታውቋል።

ከዚህ በተቃረነ አግባብ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የምርመራ ጋዜጠኝነት ስራ ላይ በማንኛውም መንገድ እክል መፍጠር የዜጎች መብትን መደፍጠጥ፣የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠር እንዲሁም ተጠያቂነት እንዳይሰፍን ከአጥፊዎች ጋር እንደመተባበር ይቆጠራል ሲል በመግለጫው አስታውቋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የምርመራ ጋዜጠኝነት ስራዎች እንዲቆሙ ትዕዛዝ የመስጠት አዝማሚያ እየተስተዋለ መጥቷል ያለው መግለጫው በማንኛውም አካል የሚፈጸም ማዋከብ ሊቆም እንደሚገባ አሳስቧል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።