Get Mystery Box with random crypto!

“የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ለተሰጠን ጸጋ በማመስገን ለኢትዮጵያ ከፍታ መትጋት እንዳለብን የሚያሳ | ስልጤ ዞን ኮሚዩኒኬሽን - SILTIE ZONE COMMUNICATION

“የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ለተሰጠን ጸጋ በማመስገን ለኢትዮጵያ ከፍታ መትጋት እንዳለብን የሚያሳይ ነው” - ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ
**********************************************

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስተላለፉት መልዕክት ከደረሰብን መከራና ፈተና ይልቅ ለተሰጠን ጸጋ በማመስገን ለኢትዮጵያ ከፍታ መትጋት እንዳለብን የሚያሳይ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ዛሬም እንደ ትናንቱ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን፣ እጃችንን ለምስጋና እንዘረጋለን!!" በሚል የምስጋና መልዕክት አስተላለፈዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በሚኒስትር ማእረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ፤የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ እንድታሸንፍ ላደረጓት ፈጣሪና ህዝቧ ምስጋናን የሚቸር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሀገር ሆና እንዳትቀጥል በርካታ የውጭና የውስጥ ፈተናዎች ቢያጋጥሟትም በዜጎች አንድነትና ጥንካሬ እንዲሁም በፈጣሪ ኃይል መሻገሯን ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

መልዕክታቸው በዜጎች ዘንድ የአመስጋኝነት ስነልቦና እና ባህል እንዲዳብር ጥሪ የተላለፈበት መሆኑንም ዶ/ር ቢቂላ አብራርተዋል።

ከአማራሪነትና ከተሸናፊነት ይልቅ አመስጋኝና ብሩህ ተስፋ ሰናቂ መሆን እንደሚገባ ጠቃሚ መልእክት የተላለፈበት ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በእነዚሁ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ነጻነት እና ግጭት ማስተናገዷን ጠቅሰው፤ በቁርጥ ቀን ልጆቿና በፈጣሪ ቸርነት ፈተናዎችን መሻገር መቻሏንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌትክስ ሻምፒዮና ያስመዘገበው አኩሪ ድል ከተባበርን በድል አድራጊነታችን እንደምንቀጥልና መሰናክሎችን ሁሉ እንደምንሻገራቸው ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

አትሌቶቻችን በዓለም አደባባይ በፈፀሙት ጀግንነት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ከፍ እንዲልና ክብሯ እንዲወሳ አድርገዋል ብለዋል።

በዚህም መንግሥት ለአትሌቲክስ ቡድኑ የጀግና አቀባበል እንደሚዲያደርግ ገልጸው፤ኢትዮጵያ ታመስግን የሚል መርሃ ግብርም በነገው ዕለት እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።

መርሐ-ግብሩ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ተቋማት ሠራተኞችና አመራሮች ከቀኑ 9፡00 ላይ ቀኝ እጃቸውን በግራ ደረታቸው ላይ በማሳረፍ ለአንድ ደቂቃ በፅሞና ቀና ብለው በምስጋና ልቦና የሚቆዩበት ስነ ስርዓትም ይከናወናል።

ቀጥሎም ሁሉም ኢትየጵያውያን ለአንድ ደቂቃ በእልልታና በጭብጨባ ፈጣሪን፣ ዜጎችንና መሪዎቿን የሚያመሰግኑ ይሆናል።

ምንጭ፦ብልጽግና ፓርቲ