Get Mystery Box with random crypto!

ሴትነትን ሴቶቹ ሲጥሉት 'እውነቴን ነው የምልሽ ወንድ ልጅ ቤት ስትቀመጪለት ይንቅሻል። ከ እጁ ስት | Sumeya sultan

ሴትነትን ሴቶቹ ሲጥሉት
"እውነቴን ነው የምልሽ ወንድ ልጅ ቤት ስትቀመጪለት ይንቅሻል። ከ እጁ ስትጠብቂ ከ ጫማው ዝቅ አድርጎ ነው የሚገምትሽ። አንቺ እቤቴን እቤቴን ብለሽ ጠግቦ እንዲያድር ስትንደፋደፊ እሱ ቢሮው ያለችውን በ ሽንኩርት መላጥ ብዛት እጆቿ ያልጠቆረውን፣ ለጂም ጊዜ ስላላት የሰውነት ቅርፇ ያልከዳትን ፣ ከ አስቤዛ ጎደለ አልጎደለ ብላ ለፋሽን መቀያየር የማትሳቀቀን በ አይኑ ያንደፋድፍልሻል። ይሀው እኔ ልሙት! ስንቷ መሰለችሽ ልጄን በራሴው እጅ ስርዓት አስይዤ ላሳድግ ብላ ቤቷ ችሏት በተቀመጠች ባሏን ለ ውጪ የገበረች። ቤተሰብነትን ብቻዋን ትሰራው መስሏት ብቻዋን ቤቴ ቤቴ ስትል እሱ የውጭ ነገር ብቻ እንዲሰማው ያደረገች። እውነቴን ነው የምልሽ ቤት ከመቀመጥ ፏ! ብለሽ ወጥተሽ መንደር ለመንደር መንከልከል ይሻላል።" ትላለች። በአንድ ካፌ ላይ ከኋላዬ ከተቀመጡት 4 ሴቶች አንዷ።
"ልክ ብለሻል። ሴት ልጅ ከ ወንድ እኩል መሆን አለባት መማር ከባሏ አገዛዝ ሊያወጣት ይገባል። ግን ደግሞ እንድትማሪ አይፈልጉም። እናስተምራታለን ብለው በመሃላ ከቤተሰቦቿ ይለያትና በ አመቱ ልጅ አስታቅፎ ቤተሰቦቿን ልትጠይቅ ስትሄድ ታያታለሽ። " የትምህርትሽስ ነገር?"ብለሽ ስትጠይቂያት "አይ አሁንማ እስቲ ልጄ ከፍ ትበል" ትልሻለች። ከፍ እስኪልላት የ አዲስ ልጅ ነገር ሆኖባት እቤት ውስጥ ትቀመጥለታለች። ከዛ በሚቀጥለው በአል ቤታቸው ሌላ አዲስ ሕፃን ተቀላቅላ የ እናትዬዋን የ እስር ጊዜ መርዘሙን ታበስራለች። ወጥቼ ልስራ ያለች እንደሁ "ምን ጎደለሽ? ልጆቹን አሳድጊ!" ብሎ የ ቤቱ ስራ እንደሚቀል ያህል በቀላል ዓረፍተ ነገር ነገሩን ይዘጋዋል። እስቲ ደግሞ ሌላ አንድ ነጋዴ ሂጂ እና "ሚስትህ ጠበቃ ብትሆን ምን ይሰማሃል?" ብለሽ ጠይቂው "ንዝር" ሲለው ትመለከቻለሽ። መበለጥን አይቀበሉማ። እንደ ድሮው እነሱ ብቻ አዛዥ መሆንን ነው የሚሹት"
አለች። የመጀመሪያዋ ተናጋሪ አሟሟቂ።
"አንቺ እሱን ትያለሽ። መማርማ ቅንጦት ነው። ኩሺና ቦታሽ እንደሆነ የሚያስብ ስንት አባወራ በየቤቱ አለ መሰለሽ። ውጪ ላይ ግን እንደ ሴት አክባሪ ራሱን የሚያይ። ምግብ መስራትሽ የ ሴትነት ግዴታሽ እንጂ እንደ ውዴታ የማያይ፤ እንደ እናቱ ቡና እያፈሉ አባወራን መጠበቅ የትዳር ደንብ የሚመስለው፤ ብቻ ወንድነትን በ አባቱ ልክ የሚመዝን፤ ሚስትነትን በ ሃላፊነት ብዛት የሚያጥር። እስቲ ዛሬ ሂጂ እና "ደክሞኝ እራት አልሰራሁም።"በይው። " እኔ ውጪ ደክሞኝ መጥቼ ምናምን የሚል ዜና ያነብልሻል። የሚሰራውን ስራ እንደ ውለታ እንድታመሰግኚው ይዘረዝርልሻል። የ እውነት ግቢ እና ዛሬ ምግብ መስራት እንዳልቻልሽ ንገሪው። እንደውም "ስለደበረኝ" በይው! ወይም ደግሞ "ከፈለግክ ራስህ ስራ!" በይው እና መልሱን ታይዋለሽ።" አለች 3ተኛዋ። ሲመስለኝ ይሄ ሁሉ ምክር "እሺም" "እምቢም" ሳትል ዝም ብላ ለምታዳምጠው ጉደኛቸው ነበር። "እሺ "አለቻቸው መጨረሻ ላይ። ወሬያቸውን እንደዘጉ "የኔ ቆንጆ እጅሽ ግን ለምንድነው የጠቆረው?" ብለው የነሱን ለስላሳ እጅ ከሷ ስራ ያደከመው እጅ ጋር አነጻሰሩት። "ደግሞ ምንድነው? እንደ በፊቱ አትዘንጪም፣ ከኛ ጋር አትዝናኚም፣ ስራም ሆነ ክላስ አትሄጂም" ብለው ቤቴን ብላ የተቀመጠችን ሴት፤የሆነ ሰውዬን ሚስት በነገር ወጉ።
"አሁን ያቺ ሴት ቤት ስትገባ ስራ ላይ የደከመ ባልን ቤት ስታገኘውና እራት ሲጠይቃት የምትመልሰው፤ ልቡ ሲቀየማት፤ በልቧ ባሏ እንደ ድሮ አባወራ እንደሆነ እና ኋላ ቀር እንደሆነ ሲሰማት፤ ቃላት ሲወራወሩ፤ ግጭት ሲነሳ እና " ድሮም ቤቴን ቤቴን ስል..."በሚል ውለታ ስታሸማቅቀው፤ ባል ጠዋት መልካም ውሎ ተመኝቶላት የወጣውን ሚስቱ አካሏን መልሰው ፍቅሩን እዛው ነጥቀውት የሚጨነቀውን መጨነቅ በአይነ ህሊናዬ እየሳልኩት የምጠብቀው ስልክ ተደውሎልኝ ትቻቸው ወጣሁ። ሴትነትን አንስተው ሲያፈርጡ፤ ወርቅ ሊያለብሱት አልማዙን ጠቆርክ ብለው ሲነቅሉ፤ በንፅፅር ራሳቸውን ባነሰ ሚዛን ላይ ሲያቆሙ ታዝቤ ወጣሁ። ለአድማጭየውም ትዳርም እየጸለይሁ።"
@sumeyasu