Get Mystery Box with random crypto!

ሰበር ዜና ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የተደረገው ህዝበ ውሳኔ በድጋሚ እንዲካሄድ ወሰነ የኢትዮጵ | Skyline media

ሰበር ዜና
ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የተደረገው ህዝበ ውሳኔ በድጋሚ እንዲካሄድ ወሰነ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የተደረገው ህዝበ ውሳኔ ምርጫ እና የመራጮች ምዝገባ ውድቅ ተደርጎ ድጋሚ እንዲካሄድ ወሰነ፡፡ ቦርዱ በዞኑ የተካሄደውን የህዝበ ውሳኔ ምርጫ ውድቅ ያደረገው፤ “መጠነ ሰፊ” ጥሰቶች በመፈጸማቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው፤  የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ህዝበ ውሳኔን አስመልክቶ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 22፤ 2015 በሰጠው መግለጫ ነው፡፡ በዚሁ መግለጫ ላይ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፤ አጠቃላይ የህዝበ ውሳኔውን ሂደት እና በወላይታ ዞን የነበረውን ጥሰት በተመለከተ የተሰጠውን ውሳኔ በንባብ አሰምተዋል።

ቦርዱ በዛሬ መግለጫው በወላይታ ዞን የተፈጸመው ጥሰት “የምርጫ ሂደቱን ተዓማኒነት እና እውነተኝነት ያሳጣ እና አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱንም የሚያዛባ” መሆኑን ገልጿል። አቶ ውብሸት “የወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ውድቅ እንዲደረግ እና የመራጮች ምዝገባ እና ድምጽ አሰጣጡም በድጋሚ እንዲደረግ ቦርዱ ወስኗል” ሲሉ የወላይታ ዞን የህዝበ ውሳኔ ሂደትን በተመለከተ የቦርዱን ውሳኔ ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል። 

ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ “ጥሰቶቹን ያስፈጸሙ፣ የፈጸሙ እና የተባበሩ” ያላቸውን አካላት በመለየት ምርመራ እንዲያከናውን እና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት እንዲያደርግ ለፌደራል ፖሊስ ደብዳቤ እንዲጻፍ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)